በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ውስጥ በምትገኘው በደብረ ታቦር ከተማ ላይ በተፈጸመ የከባድ መሣሪያ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸው ነዋሪዎችና የአካባቢው አስተዳዳሪ ለቢቢሲ ገለጹ።

የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ቀለመወርቅ ምህረቴ “ሐሙስ ዕለት ከሰዓት በኋላ የህወሓት አማጺያን ፈጸሙት” ባሉት የከባድ መሣሪያ ጥቃት የአምስት ንጹሃን ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ አንድ ህጻንን ጨምሮ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል። በጥቃቱ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች የአንድ ቤተሰብ አባል መሆናቸውንም አስተዳዳሪው ተናግረው “የመቁሰል አደጋ ያጋጠማቸው አባት እና አንዲት የጎረቤት ህጻን ልጅ ናቸው” ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪ አቶ ጥጋቡ ታምሩ ደግሞ በከባድ መሣሪያው ጥቃት በዞኑ አስተዳዳሪ ተገድለዋል ከተባሉት የአንድ ቤተሰብ አባል ከሆኑ 5 ሰዎች በተጨማሪ በቤቱ ውስጥ የነበረ የአንድ እንግዳ ግለሰብ ሕይወት ማለፉን ገልጸዋል። ነዋሪው ሐሙስ ዕለት የደብረ ታቦር ኢየሱስ የሚከበርበት በዓል በመሆኑ ጥቃቱ ሲፈጸም ቤተ ክርስቲያን እንደነበሩ ጠቅሰው፤ በከተማው ላይ ጥቃቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ ከርቀት የከባድ መሣሪያ ተኩስ ይሰማ እንደነበር ተናግረዋል።

“ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኘው ተራራ ላይ ነው። በዕለቱ ከተማው ውስጥ በተከታታይ አራት የከባድ መሣሪያ ፍንዳታ ሰማሁ። አንደኛው የወደቀበት ቦታ አቧራ ሲጨስ ተመልክቻለሁ” ብለዋል አቶ ጥጋቡ። በከባድ መሣሪያው የተመቱት መኖሪያ ቤቶች የሚገኙበትና መድሃኒዓለም ተብሎ የሚጠራው አካባቢ ከእርሳቸው መኖሪያ ብዙም ሩቅ እንዳልሆነ የገለጹት ነዋሪው፤ በጥቃቱ በመኖሪያ ቤቶች እንዲሁም በሌሎች ንብረቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ በከተማዋ ላይ የተፈጸመው ከቀኑ ሰባት ሰዓት ገደማ ሲሆን አርሴማ፣ ተፈናቃይ ሠፈር፣ መድሃኒዓለም ቤተክርስቲያን ጀርባ እና ደብረ ታቦር ሪፈራል ሆስፒታል አካባቢዎች የተተኮሱት ከባድ መሣሪያዎች መውደቃቸውን የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ገልጸዋል። ጥቃቱ የተፈጸመበትን ቦታ በቅርበት የሚያውቁት ነዋሪው አቶ ጥጋቡ በአካባቢው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና ቤተክርስቲያን መኖሩን ጠቅሰው “ተኩሱ ምንን ዒላማ እንዳደረገ አላውቅም” ብለዋል።

አስተዳዳሪው አቶ ቀለመወርቅ አማጺያኑ በተከታታይ አራት ከባድ መሣሪያዎችን ወደ ከተማዋ እንደተኮሱ በመግለጽ ሆስፒታል፣ የባንክ ተቋማት ባሉበት አካባቢ እንዲሁም በግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ላይ ማረፉን ተናግረዋል። “በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ የወደቀው ከባድ መሣሪያ ግን አገር ሰላም ብለው በቤታቸው ውስጥ የነበሩ ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል” ሲሉ አስረድተዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ጊዜ በከተማው ነዋሪ ዘንድ ድንጋጤ ተፈጥሮ ነበር ያሉት አቶ ቀለመወርቅ፤ “አሁን ግን ይህ ጥቃት ለምን እንደተፈፀመ ሕብረተሰቡ ተገንዝቦ ተረጋግቶ አካባቢውን እየጠበቀ ነው” ሲሉ አክለዋል። ከደብረታቦር ከተማ በተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ “ወራሪ” ካሏቸው አማጺያን ጋር ውጊያ መኖሩን አስተዳዳሪው ገልጸው፤ ወደ ከተማዋ የተተኮሰው ከባድ መሣሪያ “ከጉና ተራራ አካባቢ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተሰየመው ህወሓት በደብረ ታቦር ከተማ ላይ ሐሙስ ዕለት ስለተፈጸመው የከባድ መሣሪያ ጥቃት ያለው ነገር የለም። ለወራት በትግራይ ክልል ውስጥ ከህወሓት አማጺያን ጋር ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ለማስቆም የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከክልሉ ካስወጣ በኋላ ጦርነቱ ወደ አጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች ተዛምቷል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ለቢቢሲ ባለፈው ሳምንት እንደተናገሩት ጦርነቱ የአማራ ክልል ከትግራይ ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች በሙሉ እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ ዘልቆ በመግባት እየተካሄደ ነው። ከዚህ ቀደምም የአማራ ክልል መንግሥት የህወሓት አማጺያን የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ዋና ከተማ በሆነችው ወልዲያ ላይ ከባድ መሳሪያ መተኮሳቸውን እና በንፁሃን ላይ ጉዳት መድረሱን ማሳወቁ ይታወሳል።

በተመሳሳይ ከጥቂት ሳምንታት በፊት አማጺው ህወሓት አፋር ክልል ውስጥ ጋሊኮማ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በተፈናቃዮች ላይ በከባድ መሣሪያ በፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎችን ገድሏል ተብሎ ቢከሰስም ድርጊቱን አለመፈጸሙን በመግለጽ አስተባብሏል። የሕወሓት ኃይሎች በአማራ ክልል ላይ ባደረሱት ጥቃት ታሪካዊቷን ላሊበላን ከተማ ጨምሮ ሌሎች የሰሜን ወሎ ቦታዎችን መያዛቸውን በተደጋጋሚ ይገልጻሉ።

ምንጭ – ቢቢሲ