የጦርነት ብዥታ (ዋር ፎግ) አብዛኛውን ጊዜ በጦር ሜዳ ላይ ያለውን ግራ መጋባትን ለመተንተን የሚያገለግል አገላለፅ ነው።
ነገር ግን በኢትየጵያ ውስጥ በትግራይ አማጽያንና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ክፉኛ እየተባባሰ በመጣው የመረጃ ጦርነት ላይ በቀላሉ ሊተገበር ይችላል። ቢቢሲ በቅርቡ ለትግራይ አማጽያን ሲዋጉ ተያዙ ከተባሉ ታዳጊዎች ጋር ቃለ ምልልስ እንዲያደርግ ጥያቄ ሲቀርብለትም ሁኔታውን በጥንቃቄ ነው የተቀበልነው። በትግራይ አዋሳኝ በምትገኘው አፋር ክልል ተያዘ የተባለው የ17 ዓመት ታዳጊ በስልክ “እኔ በትግራይ ተዋጊዎች በአስገዳጅ ሁኔታ የተመለመልኩት ከጓደኞቼ ጋር ኳስ እየተጫወትኩ በነበርኩበት ወቅት ነው” አለ።
ጦርነቱ ጥቅምት መጨረሻ ላይ በትግራይ የተጀመረ ቢሆን በቅርቡ ደግሞ ወደ አጎራባቾቹ የአፋርና የአማራ ክልልሎች ተዛምቷል። ህወሓት በቅርቡ በውቅር አብያተ ክርስቲያናት ስመ ጥር የሆነችውን የላሊበላ ከተማን ተቆጣጥሯል። በትግራይ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ መሆኑን የሚናገረው ሌላው ታዳጊ “ወደ ጦር ግንባር የተወሰድኩት በኃይል ነው። ቤተሰቦቼ ለሕይወታቸው ፈርተው ስለነበር ምንም ማለት አልቻሉም” ብሏል።
ሌላ የ19 ዓመት ሴት ደግሞ “ምንም ዓይነት ወታደራዊ ሥልጠና አላገኘንም፣ ወደ አፋር ወሰዱን፣ ትግሉን ካልተቀላቀልን ቤተሰባችንን እንገድላለን ብለው ዛቱብን” ብላለች። ታዳጊዎች እንደሚናገሩት የፌደራሉ መንግሥት አጋር በሆነው የአፋር ክልል ኃይሎች በቁጥጥር ከመዋላቸው በፊት በክልሉ መዲና መቀለ አቅራቢያ ወደ 50 የሚጠጉ ታዳጊ ወንዶችና ሴቶች ያለፈቃዳቸው ትግሉን እንደተቀላቀሉ ነው።

በዚህ ቃለ መጠይቅ ላይ ትክክል ያልሆነ ነገር እንዳለ የመጀመሪያው ምልክት የአፋር ክልል ባለስልጣናት ቃለ መጠይቁን በታዳጊዎቹ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትግርኛ ሳይሆን በአማርኛ እንዲሆን ጫና ማሳረፋቸው ነው። ከዚያም የቀረጽነውን የታዳጊዎቹን ቃለ መጠይቅ በጥንቃቄ መለስ ብለን ስናዳምጥ የጠረጠርነው ጉዳይ ተረጋገጠ። የአፋር ክልል ባለሥልጣን ቃለ አቀባይ ለታዳጊዎቹ ምን ማለት እንዳለባቸው ሲናገርም ይሰማ ነበር።
ተመሳሳይ ቃለ መጠይቆችም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲተላለፉ ታይቷል። የተሰላቹ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚመስሉ ታዳጊዎችን በካሜራዎቻቸው ቀርፀው አሳይተዋቸዋል። አንዳንዶቹም በጦርነቱ ላይ ጉዳት የደረሰባቸው ይመስላል። ጠቅላይ ሚንስትሩ በጀመሩት የለውጥ እርመጃዎች ምክንያት በአንድ ወቅት የፖለቲካ አጋሮችና በአንድ ግንባር የነበሩት ዐቢይ አሕመድና ህወሓት መቃቃር ለወራት ያህል ሻክሮ ቆይቶ በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ጦርነቱ ተጀመረ።
ኤርትራ ወታደሮችም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጎን ተሰልፈው ወደ ግጭቱ ገቡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህወሓት ወደ “አሸባሪ” ድርጅትነት ተቀይሯል በማለት የሚከሱ ሲሆን ህወሓት በበኩሉ ሕጋዊው የትግራይ መንግሥት ነኝ በማለት ይከራከራል። የትግራይ ኃይሎች መቀለን እንደገና ከተቆጣጠሩበት ወቅት አንስቶ የኢትዮጵያ መንግሥት ህጻናትን ወታደሮችን ያሰልፋሉ በማለት ሲከሳቸው ይሰማል።
የመንግሥት ወታደሮች ከተቆጣጠሩት ከስምንት ወራት በኋላ ወሳኝ ነጥብ በሆነው የመቀለን እንደገና መያዝ አስመልክቶ ኒውዮርክ ታይምስ በሰራው ዘገባ የትግራይን ተዋጊዎች ፎቶዎችን አሳይቷል። ከነዚህም መካከል የተወሰኑት ዕድሜያቸው ያልደረሱ ይመስላል። ጋዜጣው “መጠነ ሰፊ ግድያዎች፣ የዘር ማፅዳት የመሳሰሉ አሰቃቂ ጭፍጨፋዎች መለያ በሆኑበት ይህ ጦርነት” ምክንያት የሆናቸው “ከፍተኛ ተነሳሽነት ያላቸው ታዳጊ ምልምሎች” እንደሆኑ ገልጿል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የማኅበራዊ ሚዲያ ደጋፊ ሠራዊታቸው የትግራይ ኃይሎች ሕፃናት ወታደሮችን በግዳጅ በመመልመል፣ በአደንዛዥ ዕጽ በማስከር ወደ ጦር ግንባር እየገፏቸው ነው እያሉ ይወነጅሏቸዋል። የህወሓት ቃለ አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው ከቢበሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ማንንም ታዳጊ የትግራይን ኃይል እንዲቀላቀል አናስገድድም ብለዋል።

“እውነቱ ከታዳጊዎች ጋር ተያይዞ ዋነኛው ችግር ዕድሜያቸው 17፣ 18፣ 19 የሆኑ ታዳጊዎች ኃይላችንን መቀላቀል ይፈልጋሉ። ምንም እንኳን 18 ዓመት የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ሕጋዊ ዕድሜ መሆኑንም ማስታወስ ያስፈልጋል። ታዳጊዎቹ በኤርትራ በዐቢይ ኃይሎችና በአማራ ተስፋፊዎች ቤተሰቦቻቸው ላይ በደረሰባቸው ባልተነገረ አሰቃቂ ሁኔታ አማካኝነት የትግራይን ኃይል መቀላቀል ይፈልጋሉ። ነገር ግን እኛ የህፃናት ወታደሮች የሉንም” ብለዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በአፋር ጤና ጣቢያ ላይ በከባድ መሳሪያ ጥቃት መድረሱ ተዘግቧል። ይህንንም ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከ100 በላይ ሰዎች በትግራይ ተዋጊዎች ተገድለዋል እንዲሁም የአፋር ጭፍጨፋ የሚሉ ሃሽታጎች በማኅበራዊው መገናኛ መድረክ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰራጭቷል።
ቢቢሲ ያናገረው የአካባቢው ዶክተር ወደ ሆስፒታሉ የመጡ 12 ሰዎች በደረሰባቸው ጉዳት እንደሞቱ ቢገልፅም የሟቾችን ኦፊሴላዊ ቁጥር የትኛውም አካል ቢሆን ሊሰጠን አልቻለም። የትግራይ ተዋጊዎች ጥቃቱን አላደረስንም በማለት ምርመራ እንዲካሄድ ጠይቀዋል። በጦርነቱ ውስጥ የሚነሱ ማንኛውም ጉዳዮች፣ መግለጫዎች፣ ምላሾችና አፀፋዊ ምላሾች በመንግሥት፣ በህወሓት እና በኢትዮጵያ ውስጥና በውጭ አገር ባሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ደጋፊ ሠራዊታቸው በትዊተርና በፌስቡክ ሲንሸራሸር ይውላል።
በአሁኑ ወቅት በመላው ትግራይ ለሁለት ወራት ያህል የስልክ እና የኢንተርኔት መገናኛ ዘዴዎች በመቋረጣቸው መረጃ ፈፅሞ ማግኘት አዳጋች አድርጎታል። የፌደራሉ መንግሥት የትግራይ አማጺያን የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጁን እስካልተቀበሉ ድረስ የመገናኛ ዘዴዎች እንደማይመለሱ አስታውቋል። የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው እገዳው ተነስቶ የጠላት ኃይሎች ክልሉን ለቀው እስካልወጡ ድረስ የተኩስ አቁሙን አንቀበልም ብለዋል።
“የፌደራል መንግሥቱ ዓላማው መረጃን መቆጣጠር ሲሆን የትግራይ መሪዎችም ፕሮፓጋንዳን ከመጠቀም ወደኋላ አይሉም። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች እና ሲቪል ማኅበራት ማን ምን እየሰራ እንደሆና ለማጋለጥ በአንፃራዊነት ደካማ ናቸው” በማለት የሚናገረው ቀውስን የሚያጠናው የዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ከፍተኛ ተንታኝ ዊልያም ዴቪሰን ነው።
አክለውም “ለዚህ ጦርነት የተወሳሰበ ለመሆኑ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ በርካታ ምክንያቶች አሉ” ይላል። በባለሙያዎች ዘንድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ለአስከፊ ረሃብ ተጋልጠዋል በሚባልበት ሁኔታ እርዳታ ወደ ትግራይ የመድረሱ ሁኔታ ሌላኛው የመረጃ የጦር ሜዳ ሆኗል። ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ ለማድረስ ቁልፍ መስመር የሆነውና ወደ ምዕራብ ትግራይ መድረስ ከሚቻልባቸው ጥቂት መንገዶች የሆነው ተከዜ ድልድይ ሰኔ 24/2013 ዓ.ም ሲፈነዳ የፌደራል መንግሥቱ ህወሓትን ተጠያቂ አድርጓል።
ነገር ግን ዊልያም ዴቪሰን ክርክሩ ውሃ እንደማይቋጥር ይናገራል። “የፌደራል ኃይሉ መሸሹን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች እያጠቁ ነበር። ምዕራብ ትግራይንም መልሶ በመቆጣጠር የእርዳታ፣ የንግድ እና አስፈላጊ አገልግሎቶችን መድረስ የሚቻልበትን መንገድ ይፈልጉ ነበር። ወሳኝ የሆነውን የወንዝ መሸጋገሪያቸውን ለምን ያወድማሉ?” በማለት ይጠይቃል።
“የአማራና የፌዴራል ኃይሎች ግን ወደኋላ ካፈገፈጉ በኋላ ትግራይን ለመቁረጥና ምዕራባዊ ትግራይንም ላለመልቀቅ ስለፈለጉ ድልድዩን ለማፍረስ በቂ ምክንያት ነበራቸው” ይላል። በትግራይ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል። የጦርነቱ ተሳታፊ አካላት በሙሉ የሰብዓዊ ጥሰትን በማድረስ ተከሰዋል።
በቅርቡ ህወሓት የተለያዩ ግዛቶችን መቆጣጠሩን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ “ሁሉም ዕድሜው የደረሰና አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ በሙሉ” ከአማጺያኑ ጋር የሚደረገውን ውጊያ እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ውይይት ሩቅ ይመስላል። የመረጃው ጦርነትም በተመሳሳይ መልኩ የመቀዛቀዝ ምልክትም እያሳየ አይደለም።
ምንጭ – ቢቢሲ