ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ በቅድመ ምርጫ፣ በምርጫ ዕለትና በድኅረ ምርጫ በተፈጠሩ ችግሮች በሦስቱም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች 74 ክሶች ቀርበው ውሳኔ ማግኘታቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዓርብ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ አደረገ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ እንደገለጹት፣ ከስድስተኛው አገራዊ የምርጫ ሒደት ጋር ተያይዞ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ፍርድ ቤት ለሚቀርቡ ጉዳዮች፣ አፋጣኝ ውሳኔ ለመስጠት በየደረጃው  24 ልዩ ችሎቶች ተደራጅተዋል፡፡  ለዳኞችም ሥልጠና ተሰጥቶ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል፡፡ የምርጫ ሒደቱ በይፋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት 21፣ በከፍተኛ ፍርድ ቤት 24 እና በጠቅላይ ፍርድ ቤት 29፣ በአጠቃላይ  ከምርጫ ጋር የተያያዙ 74 ጉዳዮች (ክሶች) ለፍርድ ቤት ቀርበው በነፃነትና በገለልተኝነት የዳኝነት ውሳኔ እንደተሰጠባቸው ተናግረዋል፡፡ ጉዳዮቹ 22 የወንጀል፣ 52 ደግሞ የፍትሐ ብሔር  መሆናቸውን አክለዋል፡፡

ክሶቹ ወይም ጉዳዮቹ የቀረቡት 57 በቅድመ ምርጫ፣ አራት በምርጫው ዕለትና ቀሪዎቹ 13 ጉዳዮች በድኅረ ምርጫ የቀረቡ መሆናቸውን ወ/ሮ መዓዛ ጠቁመዋል፡፡  ፕሬዚዳንቷ እንዳብራሩት የወንጀል ጉዳይ ሆነው ወደ ፍርድ ቤት የቀረቡት ክሶች የዕጩ ፖስተር መቅደድ፣ የምርጫ ማስታወቂያን መቅደድ (ማጥፋት)፣ ለማጭበርበር ሙከራ (ያለ ቦታ ድምፅ ለመስጠት ሙከራ)፣ ድምፅ በሚሰጥበት ቦታ ቅስቀሳ ማድረግ፣ በተከለከለ ክልል ውስጥ የጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት ናቸው፡፡

የፍትሐ ብሔር ክስ የቀረበባቸው ጉዳዮች ደግሞ ‹‹ምርጫ ይራዘም፣ የምርጫ ጣቢያዎች ይሰረዙልን፣ ዕጩ ተቀባይነት የለውም፣ አፈጻጸም፣ ፓርቲዎች ከምርጫ ይውጡልን፣ የቦርዱ ውሳኔ ውድቅ ይደረግልን፣ የመምረጥ መብት ይጠበቅ፣ በምርጫው እንወዳደር፣ የምርጫ ምዝገባ ይፈቀድልን፣ በድምፅ አሰጣጥ ሒደት ችግር የነበረባቸው የምርጫ ጣቢያዎች ውጤት ይሰረዝና ምርጫ እንደገና ይካሄድ›› የሚሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የሦስቱንም ፍርድ ቤቶች አፈጻጸምን በሚመለከት  ለ166,758 መዘግብት ዕልባት ለመስጠት ዕቀድ የያዙ ቢሆንም፣ ለ171,276 መዛግብት ዕልባት በመስጠት አፈጻጸማቸውን 102.7 መሆኑን አሳውቀዋል፡፡ ዕልባት ካገኙ መዛግብት መካከል 150,283  መዛግብት አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቁና 87.74 በመቶ መሆናቸውንም አክለዋል፡፡ የፍትሐ ብሔር ፍርድ አፈጻጸምን በሚመለከት ወ/ሮ መዓዛ እንዳብራሩት፣ በሦስቱም ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር የዳኝነት አገልግሎትን በሚመለከት ለአፈጻጸም የሚከፈቱ መዝገቦችን በመመርመር፣ የፍርድ ውሳኔ በማጣራት፣ ተንቀሳቃሽና ቋሚ ንብረቶችን በመገመትና በሐራጅ በመሸጥ፣ የአደራ ሒሳብ  621,260,000 ብር መሰባሰብ ተችሏል፡፡

ለፍርድ ባለመብትና ክፍያ ለሚገባቸው አካላት  673,233,396.89 ብር ክፍያ መፈጸሙን፣ ቀጥታ ካልሆነ ልዩ ልዩ ገቢዎች 491,845.20 ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡ ሦስቱም ፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከተፈቀደላቸው የተስተካከለ መደበኛ በጀት  680,498,257 ብር  ውስጥ  651,562,071.72 ብር መጠቀም መቻላቸውንና አፈጻጸሙም 96 በመቶ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ከሦስቱም ፍርድ ቤቶች ከዳኝነትና ከልዩ ልዩ  በአጠቃላይ 315,429,397.38 ብር ተሰብስቦ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ወ/ሮ መዓዛ በሪፖርቱ ግልጽ አድርገዋል፡፡

ቴክኖሎጂን በመጠቀም 46 የርቀት ችሎት ማዕከላትን በክልል ፍርድ ቤቶችና ማረሚያ ቤቶች በማስፋፋት 3,751  ባለጉዳዮች ጉዳዮቻቸውን በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲከታተሉ ተደራሽ ማድረግ መቻሉን፣ 6,620,000 ብር ማዳን እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡ በዘጠኝ ክልሎች የኢፋይሊንግ ማዕከላትን በመክፈት 1,737 የይግባኝና የሰበር መዛግብትን በማስተናገድ ከ5,000,000 ብር በላይ ማዳን መቻሉንና  በአጠቃላይ የዳኝነት አገልግሎቱን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በማስደገፍ ተገልጋዮች አዲስ አበባ በመምጣት ሊደርስባቸው የሚችለውን ድካም፣ እንግልትና ጊዜ ከመቀነስ ባሻገር ሊያወጡት የሚችሉትን  11,620,000 ብር ማዳን እንደተቻለ አክለዋል፡፡

በወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ ዜጎች በኢኮኖሚ አቅም ማነስ ምክንያት የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸው ፍትሕ እንዳይጓደል ለማድረግ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሥር የተከላካይ ጠበቆች ጽሕፈት ቤት ማሻሻያ ሥራዎችን በማከናወን ተከላካይ ጠበቆች በዳኞች አስተዳደር ጉባዔ እንዲሾሙ መደረጉን፣ ለ29,923 ባለጉዳዮች የሕግ ድጋፍ አገልግሎት የሰጠ መሆኑንና በማረሚያ ቤት ለሚገኙ ለ22,573  ታራሚዎችና በዋስትና ከማረሚያ ቤት ውጪ ሆነው ጉዳዮቻቸውን ለሚከታተሉ ተከሳሾች  የምክር አገልግሎት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በበጀት ዓመቱ ከ518  በላይ አቤቱታዎችን መቅረባቸውን፣ መመርመራቸውንና 18 መዝገቦች ትርጉም ያስፈልጋቸዋል በማለት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት መላካቸውን ገልጸው፣ 482 ጉዳዮች ደግሞ ተጣርተው የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደማያስፈልጋቸው ውሳኔ መሰጠቱን ወ/ሮ መዓዛ አስረድተዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *