የተባበሩት መንግሥታት ቅርንጫፍ ድርጅቶችና የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቹ በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጦርነት ወገንተኛ የፖለቲካ አጀንዳዎችን ያራምዳሉ መባሉ እጅጉን እንዳሳሰበው ድርጅቱ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።
ይህም ሁኔታ በቅርቡ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃንና በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተንፀባረቀ መሆኑን መግለጫው አትቷል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ የረድዔት እርዳታ ድርጅቶች ሰብዓዊ እርዳታን ሲለግሱ አራት የሰብዓዊነት መርሆችን ተከትለው ነው ያለው መግለጫው እነዚህም ሰብዓዊነት፣ ገለልተኝነት፣ ነፃነት ከአድልዎ ነፃ በሆነ መልኩ ነው ብሏል።
እነዚህን መርሆዎች በማክበር እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በመቀናጀት ድርጅቱ እና አጋሮቹ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና የከተማ አስተዳደደሮች ለተቸገሩ ነዋሪዎች አስፈላጊውን እርዳታ እያደረገ እንደሚገኝ ተጠቅሷል። እርዳታውንም እያደረገ የሚገኘውም ተጎጂውን ህዝብ ማዕከል ባደረገ መልኩ ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ ነው ብሏል።
በተያያዘ ዜናም በጦርነቱ ከአማራ ክልል ለተፈናቀሉና በደባርቅና በደሴ ለሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ፣ ውሃና የንፅህና መጠበቂያዎችን እንዳከፋፈለ የተባበሩት መንግሥታት ህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በትዊተር ገፁ አስታውቋል።
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወደ 674 ሺህ 492 ዜጎች መኖራቸውንም ዩኒሴፍ ገልጿል። ከዚህ ቀደም የፌደራል መንግሥቱ ከሰብዓዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ፈቃደኛ ቢሆንም “አንዳንድ ዘገባዎች በስህተትም ይሁን በሌላ መንገድ ወደ ትግራይ የሚገቡ በረራዎችን መንግሥት እያስተጓጓለ ያለ ይመስል ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ የተሳሳተ መረጃ እየሰጡ ነው” ሲልም አንዳንድ ድርጅቶችን ከሷል።
ከዚህም ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ መንግሥት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አገሪቷ ከአውሮፓ 1986 ጀምሮ ከድርጅቱ ጋር ከገነባችው ፍሬያማ ግንኙነት ጋር የማይመጣጠኑ ተግባራትን እየፈፀመ ነው ሲልም ለተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ደብዳቤ መላኩም የሚታወስ ነው።
የፌደራል መንግሥቱ የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) የትግራይ ክልልን በተመለከተ “የተሳሳቱ ዘገባዎችና መግለጫዎችን” እያቀረበ እንደሆነና ይህም አጋዥና ገንቢ አይደለምም ሲል ወቅሷል።
ምንጭ – ቢቢሲ