ቢቢሲ ከአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቆይታ አድርጓል። ከሳምንት በፊት በተለይም የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ት ቤት “የጸጥታ ኃይሎች በህወሓት ላይ ርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ ተቀምጧል” የሚል መግለጫ ከመስጠቱ በፊት የተደረገ ቃለ መጠይቅ ነው።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን የተናገሩ ሲሆን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና መገናና ብዙኃንን በወገንተኝነት ከሰዋል። ሙሉ ቃለ መጠይቁ በዚህ መልኩ ቀርቧል።

ቢቢሲ፡ ጦርነቱ በስንት ግንባር ነው እየተካሄደ ያለው?

ዶ/ር ፋንታ፡ ጦርነቱ በሁሉም አማራ ክልል ከትግራይ ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች የሚደረግ ሲሆን በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ አማራ ክልል ውስጥ ዘልቆ በመግባት ነው እየተካሄደ ያለው። በሰሜን በኩል ከጠለምት ጀምሮ እስከ አፋር ድንበር ድረስ ይዘልቃል። በብዙ መቶ ኪሎ ሜትሮች የሚሸፍን ውጊያ ነው እየተደረገ ያለው።

ቢቢሲ፡ የጦርነቱን ሁኔታ እንዴት ይገልጹታል?

ዶ/ር ፋንታ፡ ህወሓት ሙሉ ወረራ ነው እያደረገብን ያለው። በሁሉም ግንባሮች ያልተገደበ ጥቃት ነው እየፈጸመ ያለው። የተናጠል ተኩስ አቁሙን በሚጻረር መልኩ ነው ጥቃቱን እየፈጸመ ያለው። ዜጎች በየቀኑ ከግጭቱና ከግድያው ለማምለጥ በገፍ እየተሰደዱ ነው።

ቢቢሲ፡ አሁን ውጊያ እንዳለ ነግረውናል እና ተኩስ አቁሙ አለ ማለት እንችላለን?

ዶ/ር ፋንታ፡ መጀመሪያ መንግሥት የተኩስ አቁሙን ያደረገው በተናጠል ነበር። ነገር ግን ህወሓት ያለማቋረጥ ጥቃት ሲፈጽም እና ጭፍጨፋ ሲፈጽም ማቆሚያው የት ነው? ዜጎች በጠራራ ፀሐይ እየተጨፈጨፉ ነው። ተኩስ አቁሙ መከበር ነበረበት። እናም መንግሥት የመከላከል ሥራ ነው እየሰራ ያለው። ዜጎቻችንን እየተከላከልን ነው ያለነው። ከዚያ ያነሰም ሆነ የገፋ ነገር እያደረግን አይደለም።

ቢቢሲ፡ ይህ አይነቱ አካሄድ ከቀጠለ የሚቀየር ነገር ይኖር ይሆን? ከህወሓት ጋር ለመደራደር?

ዶ/ር ፋንታ፡ ለውጡ እንዲመጣ የምንጠብቀው ከህወሓት በኩል ነው። የተኩስ አቁሙን ማክበር አለበት። ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ለመነጋርም ቢሆን መጀመሪያ የተኩስ አቁሙ ተከብሮ የሰላም ጊዜ መኖር አለበት። ሰዎች እየተገደሉ እና እየተጨፈጨፉ ግን ይህ ሊሆን አይችልም።

ቢቢሲ የማየት ፍላጎት ካለው በአሁኑ ወቅት እናቶች ዝናብ ላይ እየወለዱ ነው። እናም እንደሚገባኝ እንደእናንተ አይነት ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ድምጽ ላጡት ድምጽ መሆን ይገባቸዋል። ምክንያቱም አሁን ያንን እያየን አይደለምና። በእርግጥ እነዚህ ብዙኃን መገናኛዎች ድምጽ ለሚያሰሙት እና ለሚንጫጩት ብቻ ሆነዋል። ይህ ደግሞ በጣም የሚያሳዝን ድርጊት ነው።

አሁን እያወራን ባለበት ወቅት ዜጎች ያለማቋረጥ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ ነው። ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮችን እያስተናገድን ነው። አዲስ ባገረሸው ጦርነት ከ2 መቶ ሺህ በላይ ዜጎች ከራሳቸው የትውልድ አካባቢ ተፈናቅለዋል። ስለዚህ ውይይቱንም ቢሆን ለማድረግ የመጀመሪያውና ብቸኛው መንገድ የተጣለውን ተኩስ አቁም ማክበር ነው።

ቢቢሲ፡ ህወሓት ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ የተኩስ አቁም እንደማያደርግ ተናግሯል። እናንተ ለዚህ ምላሻችሁ ምንድን ነው?

ዶ/ር ፋንታ፡ የጠየቅከኝን ጥያቄ ራስህ መልሰኸዋል። ዜጎች እየተጨፈጨፉ እና እየተፈናቀሉ ዝም ብለን ተኩስ ማቆም እንዳለብን የምታስብ አይመስለኝም። ብቸኛው መንገድ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መጀመሪያ ተኩስ አቁሙን መቀበል አለባቸው።

ቢቢሲ፡ ከ200 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች እንዳሏችሁ ነግረውናል። ምን አይነት ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው አሁን?

ዶ/ር ፋንታ፡ ከሰብአዊ ኤጀንሲዎች ጋር እየተወያየን ነው። ለተፈናቃዮች የእርዳታ ድርጅቶች እኩል ትኩረት እየሰጡ አይደለም። ሳስተምረው ከነበረው እና ካለኝ እውቀት ጋር የሚጻረር በሰብአዊነት ላይ አድሏዊነት እያየሁ ነው።

የአማራ ክልል ተፈናቃዮች ተገቢው ሰብዓዊ እርዳታ እየደረሰላቸው አይደለም። እየቀረበ ያለው እርዳታ በቂ አይደለም። እርዳታ ከሚያቀርቡ ድርጅቶች ጋር ተነጋግረናል። ፍትሃዊ አቅርቦት አለመኖሩን አስረድተናል። ነገር ግን እስካሁን ምንም የተቀየረ ነገር የለም። ይህ እስከሚስተካከል እየጠበቅን ነው።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ፋንታ ማንደፍሮ (ዶ/ር)

ቢቢሲ፡በርካታ ወጣቶች የአማራ ልዩ ኃይልን ወይም መከላከያን እየተቀላቀሉ እንደሆነ እያየን ነው። በቁጥር ምን ያህል ወጣት ሊቀላቀል ይችላል? ይህ ሁኔታስ በጦርነቱ ቅርጽ ላይ ምን አይነት ለውጥ ያመጣል?

ዶ/ር ፋንታ፡ የጠራነው ራሱን/ራሷን እንዲከላከል/እንድትከላከል ሁሉንም ሕዝባችንን ነው። ይህ ጥሪ ለእያንዳንዱ ዜጋችን ራሱን እንዲከላከል የተደረገ ጥሪ ነው። ይህ በሌሎች ላይ የታወጀ ጦርነት አይደለም። ራስን የመከላከል ጥሪ ነው። ስለዚህ ጥሪውን ለእያንዳንዱ ዜጋ ስላደረግን ይህንን ያክል ብዬ በቁጥር ልገልጽልህ አልችልም። ምናልባትም በሚሊዮኖች ሊሆን ይችላል።

ቢቢሲ፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም ደግሞ የአሜሪካ መንግሥት የአማራ ልዩ ኃይል አማራና ትግራይ በይገባኛል በሚወዛገቡበት አካካቢ [ወልቃይትና አካባቢዎቹ] ይውጡ ብለዋል። የእናንተ ምላሽ ምንድን ነው?

ዶ/ር ፋንታ፡ በዚያ ቦታ የአማራ ኃይል የሚባል የለም። ያሉት የፌደራል መንግሥት መከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልልን ጨምሮ የሁሉም ክልሎች ልዩ ኃይሎች ናቸው። በሁሉም አካባቢዎች የተሰማራው ኃይል የሚመራው በፌደራል መንግሥት ዕዝ ስር ነው።

ቢቢሲ፡ ይህ ጦርነት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። በተለይም የተለያዩ ክሶች ይቀርባሉና በዚህ ጉዳይ ላይ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚሉት ነገር አለ?

ዶ/ር ፋንታ፡ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለኝ መልዕክት በየትኛውም ቦታ እና በማንነታቸው ሳይገደቡ የጦርነቱ አካል ላልሆኑ ነገር ግን በሂደቱ ለሚጎዱ ለሁሉም ንጹሃን ተጎጂ ዜጎች ፍትሃዊ እርዳታ ማቅረብ አለበት። የአንድን ወገን ጩኸት ብቻ በመስማት ነገሮችን ከማራገብ ይልቅ የሁሉንም አካላት ሃሳብ ማድመጥ ተገቢ ነው። የፌደራል መንግሥት፣ የአማራ ክልል መንግሥት ሊደመጡ ይገባል። ከግጭት የሚገኝ ትርፍ የለም። ስለዚህ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የግጭቱን አንድ አካል ብቻ በመያዝና በማድመጥ ኢትዮጵያን ሊያግዛት አይችልም። አማካዩን መያዝ አለባቸው። ድምጻቸው ለማይሰማው ወገኖች ድምጽ መሆን እጅግ አስፈላጊ ነው።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለማይካድራው ጭፍጨፋ ትንፍሽ አላለም። ይህ እንደ ሰው በጣም አሳዛኝ ነው። በህወሓት ጭፍጨፋ ሰለባ ሆነው ሳለ ዝም መባላቸው በጣም ያስከፋል። በሰሜን ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር፣ ዋግኽምራ እና አፋር ክልል ስለሚፈናቀሉት ዜጎች የሚሉት ነገር የለም። ይህ ምን ማለት ነው? በእውነት ለኢትዮጵያ የሚጨነቁ ከሆነ በሚሰጧቸው መግለጫዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው። አንዳንድ ጊዜ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የሚሰጡ መደማደሚያዎች እጅግ አሳዛኝ ናቸው። ምክንያቱም ምንም አይነት ማጣሪያ ሳያደርጉ የራሳቸውን ድምዳሜ ይሰጣሉ። ይህ ለተጎጅዎች ሌላ ጉዳት ነው።

ቢቢሲ፡ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተፈናቀሉት ከየት ከየት ነው?

ዶ/ር ፋንታ፡ በዘገባችሁ አካታችሁት እንደሆነ ባላውቅም ባለፈው መጋቢት እና ሚያዚያ በሰሜን ሸዋ ዞን እና ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ በምዕራብ እና ምሥራቅ ጎጃም፣ በደቡብ ጎንደር፣ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው ይገኛሉ። በጣም አሳዛኙ ነገር ደግሞ እንዳለመታደል ሆኖ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለእነዚህ ወገኖች ድምጽ ሆኖ አያውቅም። የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በዚህ ደረጃ ለተመረጡ ወገኖች ብቻ ድምጽ መሆኑ በጣም ያሳስበኛል። ይህ ከማውቀው እና እንደመርኅ መሆን ካለበት ሎጂክ አንጻር ያፈነገጠ በመሆኑ አስጨናቂ ነው።

ቢቢሲ፡ በወልቃይት አካባቢ የትግራይ ተወላጆች ተፈናቅለዋል፣ ጥቃትም ደርሶባቸዋል በተለይ ግድያ ተፈጽሞ አስከሬናቸው ተከዜ ወንዝ ላይ ተጥሏል በሚል ለሚቀርብው ክስ ምላሻችሁ ምንድን ነው?

ዶ/ር ፋንታ፡ በእንደዚህ አይነት ድራማ እና ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል የራሱን ዜጎች በመግደል ትህነግ በሚገባ የሚታወቅና የሰለጠነ ነው። እናም ይህ የድራማው እንድ አካል እንደሆነ እጠረጥራለሁ።

ቢቢሲ፡ ይህ ግጭት ከተጀመረ ዘጠኝ ወር እየሆነው ነው። እና በብዙ ዘርፎች ላይ ተጽዕኖ ነበረው። ግጭቱ በአጭር ጊዜ ሊቋጭ የሚችልበት መንገድ አለ ብለው ያምናሉ?

ዶ/ር ፋንታ፡ ለምን መፍትሔ አይኖርም? በዓለም ላይ የማይቻል ነገር የለም። የማይቻል የምናደርገው የግጭቱ ተዋንያን ነን። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ከሰራ እና ህወሓትን የሰላም አማራጮችን እንዲያማትር ከጠየቀ ችግሩን የማንፈታበት መንገድ ላይኖር አይችልም። ያ ግን ሊሆን የሚችለው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን መንግሥት ሲያግዝ እና በአቅማቸው ልክ ህወሓት ላይ ጫና መፍጠር ሲችሉ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ህወሓት በአማራ፣ በአፋር እና በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ ያወጀውን ጦርነት ማቆም አለበት። ይህንንም በይፋ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ምንም ነገር እናደርጋለን እያሉን ነው።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን ይህንን እየሰማ ዝምታን መርጧል። አሁን ለጊዜው የማላስታውሰው አንድ ዓለም አቀፍ ተቋም እውነታውን ሰሞኑን ተናግሯል። ይህ ጥሩ ጅምር ነው። ከችግሩ የመውጫ ትክክለኛ መንገዳችን እውነት ብቻ ነው።

ቢቢሲ፡ ህወሓት በቅርቡ የተኩስ አቁሙን ተቀብሎ ወደ ድርድር ይመጣል ያምናሉ?

ዶ/ር ፋንታ፡ በህወሓት ቦታ ሆኜ መናገር አልችልም። ህወሓት በየጊዜው ሃሳቡን ይቀያይራል። ይህ የራሳቸው ጉዳይ ነው።

ቢቢሲ፡ ህወሓት ጦርነቱን ቢቀጥል ምን ታደርጋላችሁ?

ዶ/ር ፋንታ፡ ሕዝባችንን ከታወጀበት ጦርነት መከላከላችንን እንቀጥላለን። ያለን ብቸኛው አማራጭ እሱ ነው። በእኛ ላይ ጦርነት ማወጁን ህወሓት በይፋ ግልጽ አድርጓል ምንም እንኳ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምንም ነገር ማለት ባይችልም። ህወሓት ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖል እንደሚሄድ ነግሮናል። ይህንን ዝም ብለን አንመለከትም። አንተስ እንደ ጋዜጠኛ በዚህ ደረጃ ሕዝባችን ላይ ጥቃት የሚፈጽምን፣ የሚያፈናቅልን እና ያልተገደበ የበቀል ፍላጎቱን ለማሟላት በደል የሚፈጽምን አካል ምን ልንለው እንድንችል ትጠይቀኛለህ? ይህንን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ይገነዘባል ግን ምንም አይልም።