በትግራይ እና በአማራ ክልሎች እየተደረገ ካለው ውጊያ ጋር ተያይዞ ባህርዳርና ጎንደርን ጨምሮ የተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የሰዓት እላፊ አውጀዋል።

የሰዓት እላፊ ካወጁት መካከል የባህርዳር፣ የጎንደር፣ የደብረማርቆስ፣ የደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች ይገኙባቸዋል። የከተማ አስተዳደሮቹ እነዚህን የእንቅስቃሴ ገደቦች በማያከብሩ ግሰለቦችም ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

ባህርዳር

በባህር ዳር ከተማ እና አካባቢዋ ስምሪት ከተሰጠው የፀጥታ ኃይሎች ውጭ ህዝቡ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችለው ከጥዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 2፡00 ብቻ ነው። ከነሐሴ 8፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላም የእንቅስቃሴ ገደብ መቀመጡንም የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት ማሳወቁን ከአስተዳደሩ የማህበራዊ ገፅ መረዳት ተችሏል።

የተለየ ድንገተኛ ችግር ካጋጠመ ለአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች በማሳወቅ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ውጭ የተገኘ ግለሰብም እርምጃ እንደሚወሰድበት ማስጠንቀቂያ ተላልፏል። “የተለየ ድንገተኛ ችግር በገጠመ ጊዜ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት አካላት በማሳወቅ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ውጭ የተገኘ አካል ካለ የጠላት ተባባሪ ተደርጐ እርምጃ እንደሚወሰድበት አምኖ ሁሉም ህዝብና ባለ ድርሻ አካላት ተባባሪ እንዲሆን እናሰገነዝባለን።” ብሏል።

በከተማዋ የሚገኙ የንግድ እንቅስቃሴዎችም መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት መዝናኛ ክበቦችም የሰዓት እላፊውን ተግባራዊ እንደሚደረግባቸውም ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ለፀጥታ ስራ ከተሰማሩ ተሽከርካሪዎች ውጭ በከተማው ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም ተሽከርካሪ መንቀሳቀስ የሚቻለው ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 2፡00 ነው።

በከተማው ውስጥ መንቀሳቀስ እንዲችሉ የተፈቀደላቸው 120 ባጃጅ ብቻ መሆኑን አስታውቆ ከተፈቀደላቸው ባጃጆች ውጭ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ማንኛውም ተሽከርካሪ በፀጥታ አካላት ተይዞ እርምጃ እንዲወሰድበት መታዘዙም ተገልጿል።

በግልፅ ስምሪት ከተሰጣቸው የፀጥታ አካላት ውጭ በባህርዳር ከተማ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም ትዕዛዝ ተሰጥቷል። በደስታም ይሁን በሃዘን ምክንያት ጥይት መተኮስ ከነሐሴ 8 ጀምሮ ክልክል ነው ብሏል። ይህንን ውሳኔ ተላልፎ በተገኘ ማንኛውም አካል ላይ መሳሪያን የማስፈታት እርምጃ እንዲወሰድ ታዟል።

መላው የከተማው ህዝብ ተደራጅቶ አካባቢውን እንዲጠብቅ መልዕክት የተላለፈ ሲሆን “አካባቢውን ከሰርጎገብ ጠላቶች ሁሉም በቀን ፖትሮል ቅኝት እና በሌሊት ሮንድ እንዲጠብቅ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፏል።” ብሏል።

ጎንደር

የጎንደር ከተማ አስተዳደርም ከትናንትናው ዕለት ነሐሴ 8 ጀምሮ ከፀጥታ ኃይሎች በስተቀር እንቅስቃሴ ማድረግ የሚቻለው ከጥዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 3፡00 ብቻ እንደሆነ ውሳኔ አስተላልፏል። እንደ ባህርዳር በጎንደርም ድንገተኛ ችግር ያጋጠማቸው ሰዎች ለፀጥታ አካላት በማሳወቅ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ውጭ ሲንቀሳቀስ የተገኘ ግለሰብ እርምጃ እንደሚወሰድበት ማስጠንቀቂያ ተላልፏል።

የተለየ ድንገተኛ የጤና ዕክል የገጠመው ግለሰብ ከጎንደር ቀይ መስቀል በተጨማሪ 10 የጎንደር ሆስፒታል የጤና ጣቢያዎች አምቡላንሶች መዘጋጀታቸው ተጠቁሞ የስልክ አድራሻም በቅርቡ ይፋ ይሆናል ተብሏል። በከተማው የመደራጀትና የማንቃት ስራ እየተሰራ እንደሆነ ያስታወቀው መግለጫ መላው ህዝ በብሎክ ቀጠና እና 1 ለ10 እየተደራጀ በቀን ፓትሮል ቅኝት እና በሌሎእ ሮንድ እንዲጠብቅ ጥብቅ መመሪያ መተላለፉንም አስፍሯል።

“ህዝቡም ለየትኛውም ግዳጅ ተነስ ሲባል በተደራጀ መንገድ እንዲነሳ ማድረግ እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ ይደረግ” ብሏል። ከፀጥታ ስራ ውጭ ያሉ ተሽከርካሪዎች መንቀሳሰቀስ የሚችሉት ከጥዋቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ አንድ ሰዓት ነው።

ከምሽቱ 1 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት በጎንደር ከተማ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ስቲከር፣ አንፀባራቂ እንዲሁም ለአሽከርካሪካሪዎች ባጅ ተዘጋጅቶላቸው ከአዘዞ እስከ ወለቃ መስመር እንዲንቀሳሰቀሱ የተፈቀደላቸው 120 ባጃጆች ናቸው። ይህንን ውሳኔ ጥሰው ሲንቀሳቀሱ በሚገኙ አሽከርካሪዎች ላይ በፀጥታ አካላት እርምጃ እንዲወሰድ ውሳኔ ተላልፏል።

በጎንደርም ከነሐሴ 8 ጀምሮ ከፀጥታ አካላት ውጭ በከተማው ውስጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስም ሆነ በባህሉ እንደሚደረገው በሰርግም፣ በለቅሶና በቀብር ጥይት መተኮስ ፈፅሞ የተከለከለ ነው ብሏል። አስተዳደሩ ህዝቡ ከሰርጎ ገቦችና ከፀጉረ ልውጦች ራሱን እንዲጠብቅና የእንዲተባበርም ጥሪ ቀርቧል።

ህዝብን የሚያሸብርና ጠላት ላሉት አካላት መረጃ የሚያቀብል “በየትኛውም አካባቢ ፀጉረ-ልውጥ ሃይል መኖሩን አውቆ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከመቸውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እና በማጣራት እነዚህን ተግባራት ሲፈፅም የተገኘና የተላከ ማንኛውም ሃይል እውነተኛ ጠላት መሆኑን ሲረጋገጥ የፀጥታ አካላት ተይዞ ወደ ህግ እንዲቀርብ እንድታደርጉ” በማለት አሳስቧል።

ከዚህም በተጨማሪ በጎንደር ከተማ ውስጥ የጥበቃ ቦታዎች እና ኬላዎች ከፍተኛ ፍተሻ እንዲሁም በግል ሆቴሎችና ፔንሲዮኖችም ፍተሻና ክትል ይደረጋል ተብሏል።

ደብረ ማርቆስ

በደብረ ማርቆስ ከተማም ከነሐሴ 7፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ነዋሪዎችም ሆነ አሽከርካሪዎች ከጥዋቱ 12፡00 እስከ ምሽቱ 2 ሰዓት ብቻ ብቻ ነው መንቀሳቀስ የሚችሉት ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ በአካካቢው ፀጉረ-ልውጥ ብለው የጠሩት ኃይል በገጠርም በከተማም ስለሚኖር የህብረተሰብ ክፍል አስፈላጊውን ክትትል እንዲያደርግም ብሎ አሳስቧል።

ኮምቦልቻና ደሴ

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደርም እንዲሁ ከነሐሴ 5 ጀምሮ ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ከተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት ውጭ የትኛውም እንቅስቃሴ ክልክል መሆኑን አሳውቋል። ለወቅታዊ ሰራ ከተፈቀደላቸው የፀጥታ ተቋማትና የጤና ተቋማት ተሽከርካሪዎች ውጭ ከምሽቱ 2:00 ሰዓት ጀምሮ እንቅስቃሴያቸው እንዲገደብ መወሰኑን የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር አስታውቋል።

የባጃጆችም እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 1 ሰዓት ብቻ ነው ተብሏል። የደሴ ከተማ አስተዳደርም በተመሳሳይ መልኩ ከምሽቱ 2 ሰዓት በኋላ የህዝብም ሆነ የተሽከርካሪዎች ምንም አይነት እንቅስቃሴ ከነሐሴ 4፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ መገደቡን አስታውቆ የባጆጆችም እንቅስቃሴ እሰከ ምሽቱ 12 ሰዓት እንደሆነ ውሳኔ አስተላልፏል።

ከዘጠኝ ወራት በፊት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት ወደ አጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልል የተዛመተ ሲሆን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል። በትግራይ ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች፣ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የክልሉ ሕዝብ የህይወት አድን እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 400 ሺህ የሚሆነው ህዝብ በረሃብ አፋፍ ላይ ነው።

በአፋርና በአማራ ክልሎችም የሰብዓዊ እርዳታን የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ተብሏል።

ምንጭ – ቢቢሲ