በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት በቀጠለበትና ወደ አጎራባች አካባቢዎች በተስፋፋበት ሁኔታ በጣሙን አስፈላጊ የሆነውን የምግብ አቅርቦት በተመለከተ ስላለው ችግር መንግሥት በርካታ ጉዳዮችን ሲያነሳ ቆይቷል።
የቢቢሲ ‘ሪያሊቲ ቼክ’ በሚነሱ አንዳንድ ጉዳዮች ዙሪያ አስካሁን የሚታወቁ ነገሮች ላይ ማጣራት አድርጓል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት: ‘እርዳታ የሚያቀርቡ ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ እንዳይገቡ በህወሓት ተከልክለዋል’
በአሁኑ ጊዜ ይህንን ክስ በተመለከተ አስተማማኝ ደጋፊ ማስረጃ ማግኘት አልተቻለም። ህወሓት ለቢቢሲ እንደገለጸው ወደ ትግራይ የሚንቀሳቀሱ የእርዳታ አቅርቦቶችን ለማስተጓጎል መንግሥት “ሁሉንም አይነት ሰበቦችን እያቀረበ ነው” ብሏል። በአሁኑ ጊዜ ግጭቱ እየተባባሰ ከትግራይ ክልል ባሻገር እንደተዛመተ ይታወቃል፣ በአማራ ክልል በኩል ወደ ትግራይ የሚወስደው መንገድ ተዘግቷል።
ከአፋር ክልል ዋና ከተማ ከሰመራ ተነስቶ በስተሰሜን በማቅናት በአብአላ በኩል ወደ ትግራይ የሚያቀናው መስመርም በደኅንነት ስጋት ውስጥ ያለ ነው። በአማራ ክልል በኩል የሚያልፈው መንገድ በትግራይ ኃይሎች ሳይሆን የኢትዮጵያ መንግሥትን በሚደግፉ ሚሊሻዎች ተዘግቷል። የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ሐምሌ 21/2013 ዓ.ም በአፋር ክልል ውስጥ ሁለት የጭነት ተሽከርካሪዎች በሲቪሎች እንዲቆሙ ተደርገው የመዘረፋቸውን ክስተት ጠቅሷል።
ነገር ግን በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ የሆነው ማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፣ በተጨማሪም የትግራይ አማጺ ኃይሎች በወቅቱ በአካባቢው እንደነበሩ የታወቀ ነገር የለም። የተባበሩት መንግሥታት ጨምሮም በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ ለነበረው የአቅርቦት መዘግየት ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ማግኘትንና ወደ ትግራይ በሚወስደው መስመር በርካታ ኬላዎች መኖራቸውን ጨምሮ የተለያዩ ምክንያቶች እንደነበሩ አመልክቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ባለፈው ሳምንት ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት “በከፍተኛ ደረጃ ተሻሽሏል” በማለት አስከ 75 በመቶ አካባቢዎች ተደራሽ እንደሆኑ ገልጿል። ነገር ግን ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት “በቂ እንዳልሆነ” ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፈው ሳምንት “ነሐሴ 05/2013 ዓ.ም ወደ ትግራይ ክልል የምግብ እርዳታን ይዘው የገቡ የጭነት መኪኖች 277 ደርሷል” ብሏል። ቢቢሲ ይህንን ለማረጋገጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችን ቢጠይቅም ምላሽ ማግኘት አልቻለም።
ይህም ሆኖ ግን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በነሐሴ ወር ውስጥ በሳምንት ቢያንስ 6,000 ቶን የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልግና ይህንን ለማቅረብ ደግሞ በየቀኑ 100 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ወደ ትግራይ መድረስ ይኖርባቸዋል ብሏል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት: ‘ለሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ለሚደረጉ በረራዎች ፈቃድ ተሰጥቷል’
በሰኔ ወር ላይ ወደትግራይ የሚደረጉ የአውሮፕላን ጉዞዎች ከታገዱ በኋላ ከሐምሌ ወር መጀመሪያ አንስቶ እንደተፈቀደ የኢትዮጵያ መንግሥት አሳውቆ ነበር። የተባበሩት መንግሥታትም የእርዳታ ሠራተኞችን ወደ ትግራይ ለመውሰድ በሚያስችሉ የአውሮፕላን ጉዞዎች ቁጥር ላይ በቅርቡ መሻሻሎች እንዳሉ ለቢቢሲ ገልጿል።
ነገር ግን ከባለሥልጣናት በኩል ባለው ጥብቅ የፈቃድ አሰጣጥ ሂደት ምክንያት በሐምሌ ወር ከሁለት በረራዎች ውጪ ሌሎች በረራዎች አልተደረጉም። የመጀመሪያው የተባበሩት መንግሥታት መንገደኞች በረራ ሐምሌ 15/2013 ዓ.ም የተደረገ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት አዲሱ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ የተጓዙበት ነው።
በነሐሴ የመጀመሪያ ሁለት ሳምንታት ደግሞ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ አራት የሰብአዊ እርዳታ የበረራዎች ተደርገዋል። የጠቅላይ ሚኒስተሩ ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ቢልለኔ ስዩም ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከጉዞዎቹ ጋር በተያያዘ ከግንዛቤ የሚገቡ የደኅንነት ጉዳዮች እንዳሉ ለማመልከት “ለደኅንነት ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት ሂደቱ ቀላል እንዲሆን አስፈላጊው ጥረት ሁሉ ተደርጓል” ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ለሰብአዊ እርዳታ ሥራ በትግራይ ክልል የሚሰማሩ ሠራተኞችን ለማቀፈራረቅ ቢያንስ በሳምንት ሁለት በረራዎች ያስፈልጉታል።

የተባበሩት መንግሥታት: ‘ኤሌክትሪክና ኮምዩኒኬሽንን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች በትግራይ ክልል ውስጥ በፍጥነት ይጀመራሉ’
ይህ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ከተወያዩ በኋላ ጽህፈት ቤታቸው ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ላይ ነው። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስፈላጊ የሆኑት መሠረታዊ አገልግሎቶች በትግራይ ክልል ውስጥ በፍጥነት መልሰው ሥራ እንደሚጀምሩ መግለጻቸውን ዋና ጸሐፊው በበጎ ሁኔታ ተቀብለውታል” ብሎ ነበር መግለጫው።
ነገር ግን አስካሁን የተባሉት አገልግሎቶች ሥራ አለመጀመራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ስለዚህ ጉዳይ ቢቢሲ ሐምሌ 22/2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ መንግሥትን ጠይቆ እንደተነገረው “የእነዚህ አገልግሎቶች መልሶ መጀመር በዋነኝነት መሠረት የሚያደርገው በአማጺው ቡድን የተኩስ አቁሙን በመቀበል ላይ ነው።”
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰኔ ወር አንስቶ የተናጠል የተኩስ አቁም ያወጀ ሲሆን፤ አማጺያኑ ግን ያቀረቡት ቅድመ ሁኔታ ተሟልተው ተኩስ አቁሙ በድርድር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ይፈልጋሉ።
በዚህም ሳቢያ በአብዛኛው የትግራይ ክልል ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት፣ የስልክ እና የባንክ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል። አንዳንዶች ከጄኔሬተሮች የሚመነጭ የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ቢችሉም በክልሉ የነዳጅ አቅርቦት ችግር ያለ በመሆኑ ነዳጅ በተገኘ ጊዜ በውስን መጠን ነው ሊገኝ የሚችለው።
ሐምሌ 22 የመቀለ ዩኒቨርስቲ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሁፍ በስልክ፣ በኢንተርኔት፣ በኤሌክትሪክ ኃይል እና በባንክ አገልግሎቶች መቋረጥ ምን ያህል ችግር እንደገጠመው አመልክቷል።
የእርዳታ ድርጅቶችም የእነዚህ መሰረታዊ አገልግሎቶች መገደብ በክልሉ ውስጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴያቸውን እንዳስተጓጎለባቸው ይናገራሉ። መንግሥት እነዚህን አገልግሎቶች መልሶ ለማስጀመር ሥራዎችን ሲያከናውን እንደነበር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነገር ግን በህወሓት በሚደረገው ጦርነት ምክንያት “በስልክና በኢንተርኔት የፋይበር ኦፕቲክስ መስመሮችና በኃይል ማስተላላፊያ አውታሮች ላይ በሚፈጸም ውድመት . . . እንዲሁም በጥገና ሠራተኞች ላይ በሚደርስ ጥቃት” ሥራው አስቸጋሪ መሆኑን አመልክተዋል።