በምዕራብ ኦሮሚያ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ምክንያት የትራንፖርት እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን ነዋሪዎች እና የአካባቢው አስተዳዳሪዎች ለቢቢሲ ገለፁ።

በቄለም ወለጋ እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ምክንያት ዋና መንገዶች በመዘጋታቸው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ሲናገሩ የአካባቢዎቹ ባለሥልጣናት ደግሞ ችግሩ የተፈጠረው በስጋት ምክንያት ነው ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ከዚህ በፊት አጋጥሞ በማያውቅ ሁኔታ ከግምቢ ነጆ፣ ከግምቢ ደምቢ ዶሎ፣ ከጊዳሚ አሶሳ የሚወስዱ መንገዶች መዘጋታቸውን ተናግረዋል። መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጀው የሸኔ ጦር አዛዥ ኩምሳ ድሪባ ሰሞኑን ለቢቢሲ እንደተናገረው በምዕራብ ኦሮሚያ በርካታ የገጠር አካባቢ እና ትንንሽ ከተሞችን በእጃቸው ማስገባታቸውን ተናግሯል።

የምዕራብ ወለጋ እና የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው የተዘጋ መንገድም ሆነ በአማጺያኑ ቁጥጥር ስር የገባ ስፍራ የለም ሲሉ አስተባብለዋል። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሁለቱ ዞኖች አስተዳዳሪዎች የትራንስፖርት መስተጓጎል የተፈጠረው ታጣቂዎች በኃይል ከሾፌሮች ላይ ቁልፍ እየተቀበሉ ተሽከርካሪዎችን እየወሰዱ ስለሆነ ነው ይላሉ። የምዕራብ ወለጋ አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ ኡመታ ባለፉት ቀናት የሸኔ ታጣቂዎች ወደ ዋና መንገድ በመውጣት ከሾፌሮች ቁልፍ እየተቀበሉ መኪና ከቀሙ በኋላ ወደ ጫካ እየተመለሱ በመሆኑ በአንዳንድ አካባቢዎች የትራንስፖርት መስተጓጎሎች ተፈጠረ እንጂ መንገድ ሙሉ በሙሉ አልተዘጋም ብለዋል።

ቢቢሲ በሁለቱ የወለጋ ዞኖች የሚኖሩ ነዋሪዎችን ያነጋገረ ሲሆን፣ መንገድ ከመዘጋቱ ጋር ተያይዞ በወለጋ ዩኒቨርስቲ በሚካሄደው የተማሪዎች ምርቃት ላይ ለመገኘት አለመቻላቸውን ተናግረዋል። አቶ ኤልያስ ኡመታ “የተዘጋ መንገድ አናውቅም፤ በእኛ ትዕዛዝ የተዘጋ መንገድ የለም፤ አንዳንድ ቦታዎች የፀጥታ ችግር ስላለ ብቻ ይህንን መስመር ለማስያዝ የሚሰራ ሥራ ይኖራል እንጂ የተስተጓጎለ መንገድ የለም” ብለዋል።

አስተዳዳሪው አክለውም፣ ኦነግ ሸኔ የሚሏቸው ታጣቂዎች ኋላ ቀር መሳሪያዎችን እንዲሁም ባዶ እጃቸውን በመሆን ሹፌሮችን በማስፈራራት ቁልፍ እየተቀበሉ እነደነበር ገልጸዋል። በዚህ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው መኪኖች መኖር አለመኖራቸው ለጊዜው እንዳልተጣራ ተናግረዋል። በዚህ ሳምንት ውስጥ በቄለም እና በምዕራብ ወለጋ ዞኖች ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ሲካሄድ እንደነበር የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ ጉርሜሳ በበኩላቸው ዞኑን አቋርጦ በሚያልፈው መንገድ፤ ትራንስፖርት የተስተጓጎበትን ምክንያት ሲያስረዱ “እነዚህ ታጣቂዎች ከሾፌሮች ቁልፍ እየተቀበሉ መኪኖችን እየወሰዱ ትራንስፖርት እንዲስተጓጎል ስላደረጉ እንጂ እንደ ከዚህ ቀደሙ መንገድ ተዘግቶ አይደለም” ብለዋል።

ከሁለት ቀናት በፊት በሃዋ ገላን ወረዳ በተለምዶ የሱሲ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ታጣቂዎች ከሾፌሮች ቁልፍ በመንጠቅ ሦስት መኪኖችን እንደወሰዱ አቶ ገመቹ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል። በዞኑ አንዳንድ ወረዳዎችም በድንጋይና በእንጨት መንገድ ለመዝጋት ተሞክሯል የሚሉት አስተዳዳሪው፣ ይህ ሙከራም በፍጥነት እንደከሸፈ እና በዚህ መልኩም የተዘጋ መንገድ እንደተከፈተም ገልጸዋል።

የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ኤልያስ “በአሁኑ ወቅት የእነዚህን ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ለማስቆም መፈተሽ ያለበት ስፍራ ተፍሾ፣ መታየት ያለበት ቦታ ታይቶ የኅብረተሰቡ እንቅሰቃሴ ወደ ቀድሞው ተመልሷል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። አንድ ቢቢሲ ያነጋገረው እና ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ነዋሪ በሳምንቱ መጨረሻ፣ ዘመድ ጥየቃ ከጊዳሚ ወደ ጊምቢ መምጣቱንና መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ወደ ቀየው ለመመለስ እንደተቸገረ ይናገራል።

መንግሥት አሸባሪ በማለት የፈረጀውና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር በማለት የሚጠራው አማጺ ቡድን ምዕራብ ወለጋ ዞን የሚገኙ አውራ መንገዶችን መቆጣጠሩን ማክሰኞ ነሐሴ 10/2013 ዓ.ም በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ አስፍሯል።

የአማጺያኑ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ ኦዳ ተርቢ ከግምቢ ነጆ፣ ከግምቢ ደምቢ ዶሎ፣ ከነቀምቴ ባሕር ዳር እና ከግዳሚ አሶሳ የሚወስዱ መንገዶች በቁጥጥራቸው ስር መግባቱን አስፍሮ ነበር። ከነቀምት ባሕር ዳር ከሚወስደው መንገድ በስተቀር ሌሎቹ በእነዚህ ታጣቂዎች ቁጥጥር ስር መግባቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በእነዚህ ሁለት ዞኖች ውስጥ የተለየ ጦርነት አለ?

ሁለቱ የወለጋ ዞኖች ውስጥ እንደከዚህ ቀደሙ ከአማፂያኑ ጋር ግጭት መኖሩን የሁለቱ ዞኖች አስተዳዳሪዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል። መንግሥት አሸባሪ በማለት የፈረጀው ሸኔ፣ በቅርቡ ለገሰ ወጊ በሚል ስም የጥቃት ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን እና ትልልቅ መንገዶች፣ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ካምፖችን እና አንዳንድ አካባቢዎችን መያዙን እየገለጸ ይገኛል።

ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር በማለት የሚጠራው አማጺ አዛዥ፣ ኩምሳ ድሪባ ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ባለፉት ቀናት በምዕራብ እና ደቡብ ኦሮሚያ መጠነ ሰፊ የጥቃት ዘመቻ መክፈታቸውን ተናግሯል። “የኦሮሞ ነጻነት ጦር አንድም ቀን ጦርነት አቋርጦ አያውቅም፤ የአሁኑን ለየት የሚያደርገው በራሳችን በሦስት አቅጣጫ ጦርነት ከፍተን ነው ያለነው።”

አክሎም በምዕራብ ኦሮሚያ ብዙ የገጠር አካባቢ እና ትንንሽ ከተሞች አማጺ ቡድኑ፣ ከዚህ ቀደምም በእጁ አስገብቶ እንዳለ ተናግሯል። በተጨማሪም “በአገሪቱ ሰሜን አቅጣጫ ትልቅ ጦርነት ስላለ የእኛ እንቅስቃሴ ትኩረት አልተሰጠውም እንጂ ብዙ ቦታዎችን ተቆጣጥረን ነው ያለነው” ሲል አክሏል። ይሁን እንጂ የቄለም እና የምዕራብ ወለጋ ዞኖች አስተዳዳሪዎች የሸኔ ታጣቂ ቡድኖች ቀበሌን እና ወረዳን ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም የላቸውም ሲሉ ይናገራሉ።

ቦታዎችን በቁጥጥራችን ስር አውለናል የሚሉት “ውሸት ነው” ሲሉም አጣጥለውታል። አቶ ኤልያስ ጥቂት ኃይሎች የፀጥታ ችግርን ከመፍጠር ባለፈ፣ ቀበሌን እና ወረዳን ለመቆጣጠር የሚችል ኃይል በዞናችን ውስጥ የለም ሲሉ ይናገራሉ። የቄለም ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ገመቹ፣ የእነዚህ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ አልፎ አልፎ አንዳንድ ወረዳ ውስጥ ይታያል ግን ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ እንቅስቃሴ የለም ሲሉ ያስረዳሉ።

“ጦርነት የሚካሄድበት እና ገፍተው የሚወጡበት ስፍራን በሙሉ ተቆጣጥረናል ይላሉ እንጂ የተቆጣጠሩት አንድም ቀበሌ እና ወረዳ የለም። አይቻልምም” ይላሉ አቶ ገመቹ። በቅርቡ መንግሥት በሽብርተኛ ቡድንነት የፈረጃቸው ህወሓትና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት አንጻር በወታደራዊ መስክ ለመተባበር መስማማታቸውን ይፋ አድርገዋል።

ኦነግ-ሸኔ በሚል መንግሥት የሚጠራው ቡድንን ቀደም ሲል በምዕራብ ኃይል አዛዥ የነበረውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአጠቃላዩ የኦሮሞ ነጻነት ጦር መሪ እንደሆነ የሚነገረው ኩምሳ ድሪባ ወይም መሮ ለቢቢሲ “ሁለቱም ቡድኖች የጋራ ጠላት ስላለን በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ለመደጋገፍ ከስምምነት ላይ ደርሰናል” ብሏል።