የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን- ኢሰመኮ በአፋር ክልል፣ ጉሊኮማ ቀበሌ በሚገኙ ጤና ጣብያዎች እና ትምህርት ቤቶች የደረሰውን ጥቃት የሚያጣራ ቡድን ማሰማራቱን ገለጸ።

ኮሚሽኑ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ሕጻናት ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች መገደላቸው ሪፖርት ከተደረገ በኋላ ለተጎጂዎች እርዳታ በሚደረግባቸው አካባቢዎች የክትትል ቡድኑን እንዳሰማራ አስታውቋል። ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም በአፋር ክልል ዞን 4 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ጥቃት በርካታ ሰዎች ለሞትና ለጉዳት መዳረጋቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ማስታወቃቸው ይታወሳል።

ይህንንም ተከትሎ የጥቃቱን ሰለባዎች ለማሰብ በክልሉ የሦስት ቀናት ሀዘን ታውጇል። የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ኻሎይታ ይህን ጥቃት የፈጸሙት ‘የህወሓት አማጺያን ናቸው’ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች የተወሰዱበት የዱፕቲ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር መሐመድ የሱፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለሕክምና ወደ ሆስፒታሉ ከመጡት 40 ሰዎች 12ቱ ሕይወታቸው አልፏል።

ዶ/ር መሃመድ ሆስፒታል ሳይደርሱ የሞቱ እንዳሉም መስማታቸውን ተናግረዋል። በክልሉ ውስጥ ባጋጠመው ጦርነት ሳቢያ ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ተጠልለውበት በነበረው ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከ100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

በከባድ መሣሪያ በተፈፀመው ጥቃት የተገደሉትንና የተጎዱትን ሰዎች ለማሰብ የሦስት ቀናት ሀዘን መታወጁን የክልሉን መንግሥት ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አሚና ሶኮን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል። የሀዘን ቀኑ ከዛሬ የሚጀምር ሲሆን የክልሉ ሰንደቅ ዓላማ በክልሉ ውስጥ በሚገኙ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም ሆነ የግል ድርጅቶች ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ተወስኗል ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ በአፋር ክልል ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል መባሉ እጅጉን እንዳስደነገጠው መግለፁ የሚታወስ ነው። ድርጅቱ ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ ለጥቃቱ የመንግሥት ሠራዊትን ተጠያቂ በማድረግ፤ ቡድናቸው በክስተቱ ላይ ምርመራ ለማድረግ ከተገቢው አካል ጋር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ግጭት ባለባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ያለውን ሁኔታንም እየተከታተለ እንደሆነ ኢሰመኮ አስታውቋል። በግጭቱ አደጋ ውስጥ የወደቁ ንጹኃን ዜጎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ እና የሰብዓዊ እርዳታ ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ በመሆኑ አሳስቦኛል ብሏል። በመሆኑም በጦርነቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም አካላትና የጸጥታ ኃይሎች በአገራዊም ሆነ በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችና በጦርነት ሕግና መርሆች የተጣለባቸውን ግዴታ እንዲያከብሩ ኮሚሽኑ ጠይቋል።

ሲቪል ሰዎች፣ ታሪካዊ ቅርሶች እና ሲቪል መሰረተ ልማቶች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ኮሚሽኑ አሳስቧል።

ምንጭ – ቢቢሲ

 

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *