በህወሓትና በፌደራል መንግሥቱ መካከል የተነሳው ጦርነት ከዘጠኝ ወራት በላይ አስቆጥሯል፤ በዚህም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ዜጎችና ተዋጊዎች ተገድለዋል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸው ተነግሯል።
በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረው ጦርነት ወደ አጎራባቾቹ አፋርና አማራ ክልሎች ተዛምቶም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል። ህወሓት ጦርነቱን ለምን ማስፋት ፈለገና ሌሎች ወቅታዊ ጥያቄዎችን በተመለከተ የቢቢሲዋ ካትሪን ቢያሩንጋ ለህወሓት ቃለ አቀባይ ጌታቸው ረዳ ጥያቄ አቅርባላቸዋለች?
ቢቢሲ፡ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዕድሜ እና አቅም የሚፈቅድለት በሙሉ የፌደራሉንና የክልሉን ኃይሎች እንዲቀላቀሉና የትግራይን ኃይሎች እንዲዋጉ ጥሪ አቅርበዋል።ለዚህ ምላሽዎ ምንድን ነው?
አቶ ጌታቸው፡ አዎ አይቸዋለሁ። ዐቢይ አህመድ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በትግራይ ላይ በሚያደርገው የዘር ጭፍጨፋ ዘመቻው እንዲሳተፉ ጥሪ እያቀረበ ነው። ሁሉንም አይነት የጦር መሳሪያ እንዲሁም ኃይል እየላከ ነው። የክልል ሚሊሻዎችና ልዩ ኃይሎች በትግራይ የሚደረገው ጦርነት በጣም ቀላል ነው ተብሎ የተነገራቸው። ሠራዊቱ ሁለት ጊዜ ተደምስሷል። ከዚህም በተጨማሪ በርካታዎቹን ሚሊሻዎች ወደመጡበት በመመለስ ተሳክቶልናል።
እነዚህ ሚሊሻዎች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍል የመጡ ስልጠናም ሆነ መሳሪያ የሌላቸው ናቸው። በአሁኑ ወቅትም በርካታ ቁጥር የሌላቸው ምናልባትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ትርጉም በሌለው ጦርነት እንዲገደሉ ይፈልጋል። እንደ ዐቢይ ያሉ ግለሰቦች ስልጣን ላይ እንዲቆዩ ለማድረግ የኢትዮጵያንም እጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ እየከተታት ነው። በጣም ነው የሚያሳዝነው። እስካሁንም ድረስ የተናጠል ተኩስ አቁም ላይ እንደሆነ እየተናገረ ነው። ነገር እስካሁን ድረስ ውጊያ ላይ ነው።
በአሁኑ ወቅት ከሰሜን እና ደቡብ ዕዝ የተመለመሉ ወታደሮች እየመጡ ሲሆን በርካቶቹም በአማራና በአፋር ክልል እየተያዙ እንዲሁም እጃቸውን እየሰጡ ነው፤ እየተንከባከብናቸውም ነው። ለቀረው ኢትዮጵያዊ ደግሞ የመዋጋት ዕድል እንዳለም ይናገራል። የበለጠ ግድያ ይፈልጋል። በስልጣን ላይ ለመቆየትም የበለጠ ደም መቃባት እንዲኖር ይፈልጋል። ይሄንን ብቻ ነው ማለት የምችለው።
ቢቢሲ፡ መንግሥት የሚያደርገውን ዘመቻ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ነው እያሉት ነው?
አቶ ጌታቸው፡ አዎ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ነው።
ቢቢሲ፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ትግሉ (ውጊያው) ከትግራይ ሕዝብ ጋር አይደለም፤ ከህወሓት ጋር ነው እያለ ነው? ለዚህ ምን ምላሽ አለዎት?
አቶ ጌታቸው፡ አንቺ እንደጠቀሽው ከህወሓት ጋር የሚደረገው ትግል ከወራት በፊት ነበር መቋጨት የነበረበት። የትግራይን ሕዝብ ለማንበርከክ ዐቢይ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። እንደ ኢሳያስ አፈወርቂና ሌሎች ኃይሎችን በመጋበዝ በትግራይ ሕዝብ ላይም ያልተነገረ ስቃይ አድርሰዋል። የአማራ ኃይሎች የዚህ ዘር ማጥፋት ዘመቻ አካል ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በርካታ የትግራይን ግዛት እንደገና በቁጥጥር ስር አድርገናል። በተወሰነ መልኩ የኤርትራን ኃይል እንዲሁም የአማራ ኃይሎችንና የመከላከያ ሠራዊትን ማስወጣት ችለናል። ነገር ግን ዐቢይ አሁንም የትግራይን ከበባ ቀጥሏል። ትግራይን እየተዋጋ ያለውም ሁሉንም በመዝጋት ነው።
የስልክ አገልግሎት፣ የመብራት አገልግሎት፣ እንዲሁም በረሃብ ለተጎዱ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ አቋርጧል። እንዲህ ሁሉ ነገር በተዘጋበት ሁኔታ ሁሉም ቀላል ሆኖ እንዲሆን ነው የጠበቀው። የሚችለውንም ሁሉ አድርጓል። እኛም ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠን ይሄ በትግራይ ላይ የተደረገው ከበባ እስኪነሳ ድረስ እንታገላለን አልን።
ቢቢሲ፡ ጥያቄው ግን ጦርነቱን ወደ አማራና አፋር ክልል ማስፋት፤ በአማራ ክልል እስከ ላሊበላ ድረስ ዘልቃችኋል፤ እንዲሁም ዉጊያው ወልዲያ ደርሷል።
አቶ ጌታቸው፡ ወልዲያ በቁጥጥራችን ስር ናት።
ቢቢሲ፡ ጦርነቱን ማስፋት እንዴት ነው ከበባውን የሚያቆመው?
አቶ ጌታቸው፡ ተመልከች እያደረግን ያለነው የጠላት ጦር የመዋጋት ኃይሉን እያዳከምን ነው ያለነው። የዐቢይ አህመድ ኃይሎችና የአማራ ኃይሎች ናቸው በትግራይ ሕዝባችን ላይ ያልተነገረ ስቃይ እያደረሱ ያሉት። እኛም አፈሙዛቸው እንዳይተኩስ ማድረግ አለብን። አፈሙዛቸውን በብቸኝነት ፀጥ ማሰኘት የምንችለውም በሚሄዱበት በመከተል ነው። ሁሉንም ነገር በማድረግም አፈሙዛቸውን ፀጥ ማለቱን ማረጋገጥ ነው።
አማራ ክልልም ሆነ አፋር ወይም አዲስ አበባ የትም ቦታ ሆነ በልጆቼ ላይ፣ እህቶቼ፣ አባቶቼና እናቶቼ ላይ የሚያነጣጥሩት ጥይት እንደሌላቸው ማረጋገጥ አለብን። የዚህ ሁሉ አላማውም እሱ ነው። እኛ የግዛት ፍላጎት የለንም። ጦርነቱንም የማስፋት ጉዳይ አይደለም። ዐብይ አህመድ ነው ጦርነቱን ለማስፋት እየሞከረ ያለው። ሁሉም ብሔሮች የሚሳተፉበት አይነት ጦርነት በሚፈጠርበትም መልኩና በትግራይ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፊያ ዘመቻውንም እንዲቀላቀሉ እያሰለፈ ነው ያለው። ለኢትዮጵያ ሕዝብም የምንነግረው ለዐቢይ አይነት ግለሰብ ፍላጎት መሞት የለባችሁም ነው እያልን ያለነው። አፈሙዛቸው ፀጥ ሳይልም የትም ቦታ ላይ አናቆምም።
ቢቢሲ፡ ይሄንን ግጭት የት ድረስ ነው የምትወስዱት? እስከ መዲናዋ የመሄድ ሃሳብ አላችሁ?
አቶ ጌታቸው፡ ዐቢይ እስካሁን በትግራይ ያገኘነውን ለመቀልበስ እሞክራለሁ የሚል ቅዠት እስካለው ድረስ፤ በተወሰነ መልኩ የሕዝባችንን ደኅንነትና ፀጥታ ለማስጠበቅ ያገኘነውን፤ የትኛውንም ርቀት ለመጓዝ ዝግጁ ነን።
አሁንም የኤርትራ ኃይሎች የሕዝባችንን ደኅንነትና ፀጥታ ስጋት ላይ ጥለውታል። ሁሉም ነገር የሕዝባችንን ደኅንነትና ፀጥታን ማረጋገጥ ነው። ያስቀመጥናቸው ቅድመ ሁኔታዎችና በሕዝባችን ላይ የተጣለው ከበባ እስኪነሳ ድረስ፤ ያልተገደበና ያልተቆራረጠ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት፣ ሙሉ በሙሉ የራሳችንን ዕጣፈንታ በራሳችን መወሰንና የመሳሰሉት እስኪሟሉ ድረስ እንቀጥላለን። አሁንም ቢሆን ግዛቶችን መቆጣጠር ፍላጎታችን አይደለም።
ቢቢሲ፡ ይሄ ማለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ከስልጣን ማስወገድ ወይም መንግሥት መቀየር ያጠቃልላል ወይ?
አቶ ጌታቸው፡ በእውነቱ ይሄ የኛ እቅድ አይደለም። ነገር ግን ደጋግሜ የምናገረው ጉዳይ ቢኖር ኃይላችን አላማውን ለማሳካት በማንኛውም በሚያከናውነው ዘመቻ ዐቢይ ከስልጣን ቢወገድ ሁኔታው የበለጠ ጥሩ ይሆናል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ያለ ዐቢይ የተሻለ እንደሚሆን እናገራለሁ። ነገር ግን አሁንም የምናገረው ዐቢይን ከስልጣን ማስወገድ የኛ ኃላፊነት አይደለም። የሕዝባችንን ደኅንነትና ፀጥታ ለማረጋገጥ በምናደርገው የትኛውም ዘመቻ ዐቢይ የሚወገድ ከሆነ የበለጠ ጥሩ ይሆናል።
ቢቢሲ፡ ይሄ ጦርነት መስፋት ጋር ተያይዞ፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሰረት ከአማራና ከአፋር ክልል ከ250 ሺህ ሕዝብ በላይ ተፈናቅሏል። አሜሪካም የጦርነቱ መዛመት እያስከተለ ባለው የሰብዓዊ ተፅእኖ የትግራይ ኃይሎች ከአፋርና ከአማራ ክልል እንዲወጡ ጥሪ አቅርባለች።በእነዚህ ክልሎች ላይ የሲቪል ዜጎችን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ለምንድን ነው የማትንቀሳቀሱት?
አቶ ጌታቸው፡ ለእኛ ኃይላችን በተቆጣጠራባቸው አማራም ሆነ አፋር ክልሎች ለሚገኙ ሕዝቦች እርዳታ እንዲደርስ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አቅርበናል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ለአማራም ሆነ ለአፋር ሕዝቦች ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ።
የአማራን ሕዝብም በፍፁም ደኅንነቱንም ሆነ ፀጥታውን በሚነካ መልኩ የሰራነው ነገር የለም። ከአማራ ሕዝብም ጋር ፍላጎታቸውን እንዲያስጠብቁ አብረን እየሰራን ነው። አስተዳደራቸውን አላፈረስንም። ህይወትንም እንደነበረና በለመዱት መልኩ መቀጠል ይችላሉ። ትግላችን ከአማራ ሕዝብ ጋር አይደለም።
በሄድንበት ሁሉ የአማራ ሕዝብ ምን እንደሆነ አላማችንን ተረድተውታል። በሰላማዊ ዜጎችም ላይ ያነጣጠረ ምንም አላማ እንደሌለን ተረድተውታል። በመሰረተ ልማታቸው ላይ፣ በኑሯቸው፣ በሰላማቸው ላይ ተቃራኒ ሆነን አልቆምንም። የአማራና የአፋር ሕዝቦችን እንደ ወንድምና እህት ሕዝቦች ነው የምናያቸው። ከሕዝቡ ጋር በጭራሽ ችግር የለብንም።
ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ይሁን አሜሪካ ኃይላችን ከአፋርና ከአማራ ወጥተው ወደ ትግራይ ይመለሱ ብሎ ጥሪ ማቅረብ ዐቢይ የሰለጡኑም ሆነ ያልሰለጠኑና ወጣቶችና ህፃናት ወታደሮች እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች በመላክ እንዲማገዱ መፍቀድ ማለት ነው። ይሄ እንዲፈጠር አንፈልግም። የትግራይ ሕዝብ ከበባ እስኪያቆምና የሕዝባችን ሰላምና ደኅንነት እስኪረጋገጥ ድረስ ትግላችንን አናቆምም። ይሄም ለዘለቄታው መሆኑን ማረጋገጥ አለብን።
ቢቢሲ፡ የኢትዮጵያ መንግሥት እያለ ያለው የትግራይ ኃይሎች ትግራይን እስከተቆጣጠሩ ድረስ እርዳታ ማድረስ ያለባችሁ እንዲሁም አገልግሎት መስጠት ያለባችሁ እናንተ ናችሁ ነው። እናንተ ከሆናችሁ ትግራይን እያስተዳደራችሁ ያላችሁት እንዴት ነው የማዕከላዊው መንግሥት ከበባ ያደረገው ወይም አገልግሎትን የዘጋው?
አቶ ጌታቸው፡ ምሳሌ ልስጥሽ፤ የቴሌኮምን፣ ኢንተርኔት፣ የባንክ፣ ትራንስፖርት አገልግሎት ለመዝጋት ውሳኔ ላይ የተደረሰው አዲስ አበባ ላይ ነው። የሚያስፈልገው ጉዳይ ቢኖር እነዚህን አገልግሎቶች ለማቋረጥ የተጠቀሙበትን ቁልፍ እንደገና ለመቀጠል መጫን ብቻ ነው። ሌላ መሰረተ ልማት አያስፈልገውም። ሌላ የፖለቲካ ቁርጠኝነትም አያስፈልገውም። የፌደራሉ መንግሥት በአካል መምጣት አይጠበቅባቸውም።
በዐቢይ አህመድ የተቋረጠውን የባንክም ሆነ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት እንዲቀጠል ከተወሰነ ይቀጠላል። ህወሓትም ሆነ የትግራይ መንግሥት ይህንን ማድረግ አይችሉም። ምንም ሆነ ምን የፌዴሬሽኑ አካል ነን። እስከማውቀው ድረስ የፌዴሬሽኑ አካል ነን። የኢትዮጵያ ግዛቶች ሌላ መልክ ይኑራቸውም ከተባለ የትግራይ ሕዝብ ተገቢውን ውሳኔ ከወሰነ በኋላ ነው፤ ከዚህ ውጭ የፌዴሬሽኑ አካል ነን።
እንደ ፌዴሬሽን አባልነታችንም ማንኛውንም አገልግሎት የማግኘት መብትም አለን በጀትን ጨምሮ። በጀቱም በፌዴራል መንግሥቱ ተቆርጧል። ለእኛ አገልግሎትንም ሆነ ማንኛውንም ጉዳይ ራሳችሁ ናችሁ ማየት ያለባችሁ መባል ይሄ ከፍተኛ የሆነ ችግር ነው።
ቢቢሲ፡ በህወሓት ላይ ሌላኛው ክስ የሚቀርበው የህፃናት ወታደሮችን በጦርነት ላይ መጠቀም ነው። በቢቢሲ የሚገኙ የሥራ ባልደረቦቼም ከ17-19 ዕድሜያቸው የሚሆኑ ሦስት ወታደሮችን አናግረዋል። እናም ሦስቱም የሚሉት በመቀለ ነዋሪ እንደሆኑና የትግራይን ኃይሎች ለመቀላቀል እንደተገደዱ ነው። ወደ ጦርነቱም ከመቀላቀላቸው በፊት የሦስት ቀን ስልጠና እንደተሰጣቸው ነው። ታዳጊዎች በተዋጊነት እንዲገቡ ተገደዋል የሚለውን ይቀበሉታል ወይ?
አቶ ጌታቸው፡ ማንንም ታዳጊ የትግራይን ኃይል እንዲቀላቀል አናስገድድም። እውነቱ ከታዳጊዎች ጋር ተያይዞ ዋነኛው ችግር ዕድሜያቸው 17፣ 18፣ 19 የሆኑ ታዳጊዎች ኃይላችንን መቀላቀል ይፈልጋሉ። ምንም እንኳን 18 ዓመት የጦር ሠራዊቱን ለመቀላቀል ሕጋዊ ዕድሜ መሆኑንም ማስታወስ ያስፈልጋል። ታዳጊዎቹ በደረሰባቸው ባልተነገረ አሰቃቂ ሁኔታ አማካኝነት የትግራይን ኃይል መቀላቀል ይፈልጋሉ። በርካታ ታዳጊዎች የትግራይን ኃይል መቀላቀል ይፈልጋሉ እኛ ግን አንቀበላቸውም። እኛ ኃላፊነታችንን እንረዳለን።
እኛ የትግራይን ሕዝብ አናስገድድም፤ የትግራይ ሕዝብ በከፍተኛ ሁኔታ ነው ተሞ የወጣው የዐቢይን ጦር፣ የአማራ ኃይሎችን ለመዋጋት ምክንያቱም ባለፉት ዘጠኝ ወራትና ከዚያ በኋላም ስቃይና የዘር ማጥፋት ተጠቂ ናቸው፤ የትግራይ ሕዝብ ኢላማ ነበር።
እኛ ጦርነቱን የሚቀላቀል የሕዝብ ዕጥረት የለብንም። እኛ ታዳጊዎችን ለሦስት ቀን አሰልጥነንም የምናስገድድበት ሆነ ወደ ጦርነት የምንልክበት ምንም ምክንያት የለንም። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መዋጋት የሚፈልግ ሕዝብ አለን። እመኚኝ ይሄ ጥያቄ ውስጥ ራሱ የሚገባ አይደለም።
ቢቢሲ፡ 16፣ 17 ዓመት የሆናቸውና ኃይላችሁን መቀላቀል የሚፈልጉ ታዳጊዎች ስታገኙ ምን ታደርጋላችሁ?
አቶ ጌታቸው፡ በቂ የሆነና፣ በርካታ ቁጥር ያለው ተዋጊ አለን ብለን ወደቤታቸውም እንመልሳቸዋለን። በሚያሳዝን ሁኔታ አንዳንዶቹ ኃይሎቻችን ሰልፍ ሲያደርጉ ይቀላቀላሉ እናም ድጋፋቸውን ለማሳየት የጦር መሳሪያም ሆነ ማንኛውንም ነገር ይዘው ከታዩም አንድ ሰው ፎቶ ያነሳቸውና ህፃናት ወታደሮች ይባላል። የሚገርመው ነገር ህወሓትም ሆነ የትግራይ መንግሥት ላይ ህፃናት ወታደር ተጠቅመዋል ብለው የሚወነጅሉ ሰዎች ግፍ ፈፅመዋል።
እነዚህ ጦርነቱ ላይ መሳተፍ የሚፈልጉ ታዳጊዎችና ፈቃድ ያላገኙ ታዳጊዎች ቤተሰቦቻቸው ተገድለውባቸዋል፣ እናታቸው ተደፍራለች ወይም እህታቸው፤ በሆነ መንገድ በጠላት ኃይል ግፍ ተፈፅሞባቸዋል። እነዚህ ታዳጊዎች እንዋጋ ቢሉ አይገርመኝም። ትግሉን መቀላቀል የሚፈልጉ በርካታ ታዳጊዎች መኖራቸው አያስደንቀኝም ነገር ግን እኛ የህፃናት ወታደሮች የሉንም። ኃላፊነታችንንም በጥብቅ የምናይ ሰዎች ነን።
ቢቢሲ፡ ወደ ሰብዓዊ ሁኔታው እንመለስና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው። አሁን ያለው የእርዳታ ተደራሽነት ሁኔታ ምን ይመስላል። ነዋሪዎችስ ምግብም ሆነ ሌላ ሰብዓዊ እርዳታ እያገኙ ነው? በተለይም የትግራይን መዲና መቀለን ከተቆጣጠራችሁ በኋላ?
አቶ ጌታቸው፡ በመቀለ አቅራቢያ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ሰዎች በምግብ እጥረት ምክንያት እየሞቱ መሆናቸውን እየሰማን ነው። የተወሰኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ናቸው የሚሉ ተደጋጋሚ ሪፖርቶችን እያወጡ ነው።
መናገር የምፈልገው ስልክ የለም፣ መብራት ተቋርጧል፣ ባንክ ተቋርጧል፣ ይህ ማለት በየቀኑ ኑሯቸውን ለማሸነፍ በተለያየ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ ነዋሪዎች ተቸግረዋል፤ ገንዘባቸውን ከባንክ እንዳያወጡ ተደርገዋል፤ በችግርና በስቃይ ላይ ስላለው ሕዝባችን መረጃ ለማግኘት የተገደበና የተወሰነ ነው። በጣት የሚቆጠሩ የሳተላይት ስልኮች ብቻ ናቸው ያሉን።
ለረሃብ መጋለጥ የማይገባቸውና ሥራ ያላቸው ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል፤ እየተራቡ ነው ምክንያቱም የባንክ አካውንታቸው ተዘግቷል። ምንም አይነት መሰረታዊ አገልግሎት ከአዲስ አበባ ተቋርጧል። በትግራይ ያሉ ዓለም አቀፍ የረድኤት ሠራተኞች ገንዘብ ማግኘት አልቻሉም ምክንያቱም ዐቢይ ገንዘብ እንዲያገኙ አልፈቀደላቸውም። ችግሩ በጣም የተወሳሰበ ነው። ዐብይ መዋቅራዊ በሆነ መልኩ ነዋሪው ምግብ እንዳያገኝ መከልከል ብቻ ሳይሆን ምግብ ማግኘት የሚችሉ ነዋሪዎችም ምግብ እንዳያገኙ የማድረግ ሥራ ሰርቷል። በረሃብ አፋፍም ላይ ነው ያሉት። ሰው ሰራሽ ቀውስ ነው።
ዐቢይና አጋሮቹ አሁንም በትግራይ ላይ የሚያደርጉትን ማነቆ እያጠበቁ ነው፤ በትግራይ ላይ የሚያደርጉትንም ከበባ መቀጠል ይፈልጋሉ። ለዚያም ነው ይሄ ከበባ እስኪነሳ ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለን የምንለው። በሰላማዊ ሁኔታ የማይፈጠር ከሆነ በጠመንጃ አፈሙዝ ተግባራዊ እንዲሆን እናደርጋለን። በጣም የሚያሳዝን ነው ነገር ግን በዚያ መንገድ መቀጠል አለብን።
ቢቢሲ፡ እናንተ በምትቆጣጠሩባቸው አካባቢዎችስ የረድኤት ድርጅቶች መድረስ ችለዋል። የተባበሩት መንግሥታት የኤርትራ ስደተኛ ካምፖችን መድረስ እንዳልቻለ ሲያሳውቅ ነበር። ድርጅቶቹ በነፃነት መንቀሳቀስ ይችላሉ?
አቶ ጌታቸው፡ አዎ በነፃነት መንቀሳቀስ ይችላሉ። ውጊያ በሌለባቸው አካባቢዎች መንቀሳቀስ ይችላሉ። ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱና ተደራሽነት እንዲኖር የምናደርገው እኮ ለሕዝባችን ስንል ነው።
ቢቢሲ፡ በነዚህ የኤርትራ ስደተኛ ካምፖች ምን ተፈጠረ ታዲያ?
አቶ ጌታቸው፡ አንዳንድ የኤርትራ ስደተኛ ካምፖች በእኛ ቁጥጥር ስር አይደሉም። ለምሳሌ ማይፀብሪ፣ ማይአይኒና አደሃሩሽ የስደተኛ ካምፖች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ውጊያ በሚካሄድባቸው አካባቢ የሚገኙ ናቸው። ከዚያ ውጪ ግን እኛ በምንቆጣጠርባቸው አካባቢዎች የረድኤት ሠራተኞች በፈለጉበት መንገድ መድረስ ይችላሉ።
እነዚህ ስደተኞች እኮ ለባለፉት ሃያ ዓመታት አብረውን የነበሩ ናቸው። እነዚህ ስደተኞች በባለፉት ሃያ ዓመታት የትግራይ ሕዝብ ቤተሰብ አካል ሆነው ለቆዩ ስደተኞች እስካሁን ስናደርገው እንደነበረው አገልግሎት የማንሰጥበት ምንም ምክንያት የለም።
የኤርትራ ሠራዊት መጥቶ ጥቃት አደረሰባቸው ማለት ደግሞ የበለጠ አገልግሎት መስጠት አለብን ማለት እንጂ እርዳታ እንዳያገኙ መከልከል ማለት አይደለም። እኛ በምንቆጣጠርባቸው አካባቢዎች የትኛውም የረድኤት ድርጅት ተደራሽ አልሆኑም የሚል ችግር እስካሁን አልተናገሩም።
ምንጭ – ቢቢሲ