በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል እየተስፋፋ የመጣውን ጦርነት በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሰሜን ወሎ አካባቢዎች ወደ ደሴ ከተማ መግባታቸውን የደሴ ከተማ ከንቲባ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ቀደም ብሎ ከ4 አስከ 5 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ከሰሜን ወሎ የተለያዩ አካባቢዎች ወደ ደሴ ከተማ ገብተው እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባው፤ ከትናንት ጀምሮ ግን በርካታ ተፈናቃዮች ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆኑን ከንቲባው አቶ አበበ ገ/መስቀል ተናግረዋል። “ከመርሳ፣ ከወልዲያ እና ከውርጌሳ አካባቢ በርካታ ሰው በስፋት እየመጣ ነው፤ እሱን እየለየን ወደ ማረፊያ ቦታ እየገቡ ነው። ትክክለኛውን ቁጥር ለጊዜ ባላውቀውም ከ10 አስከ 15ሺህ የሚገመት ሕዝብ እየገባ ነው ያለው” ሲሉ ከንቲባው ተናግረዋል።
የህወሓት ኃይሎች በአጎራባች የአማራ ክልል በተለይም የሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ሳምንታት የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው በመስጋት ወደ ደሴ ከተማ እየገቡ መሆናቸውን ቢቢሲ ያናገራቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል። ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ መምህር ከሰባት የቤተሰብ አባሎቻቸው ጋር ከወልዲያ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ እንደሚገኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
መምህሩ እንደሚሉት ቀድመው ቤተሰቦቻቸውን ከወልዲያ ወደ ደሴ ከላኩ በኋላ እርሳቸውም ባለፈው ቅዳሜ ከወልዲያ ወደ ደሴ መግባታቸውን ይናገራሉ። “ያው ጦርነቱን ሽሽት ነው የወጣነው” የሚሉት እኚህ መምህር አሁን ከነመላ ቤተሰባቸው ዘመድ ቤት ተጠልለው እንደሚገኙ ተናግረዋል። “ደሴ ከአቅሟ በላይ ነው ሰው የያዘችው። ወልዲያ ተገልብጦ ደሴ ነው ያለው ማለት ይቻላል” በማለት በከተማዋ በርካታ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች መግባታቸውን ያስረዳሉ።
ከጥቂት ሰዎች ጋር ከወልዲያ ተነስተው እስከ ውጫሌ ድረስ በእግር እና በባለ ሦስት እግር ተሸርከርካሪ ከተጓዙ በኋላ ከውጫሌ በሚኒባስ ተሳፍረው ደሴ መግባታቸውን መምህሩ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የደሴ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ገ/መስቀል በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ ወደ ደሴ እየገባ በመሆኑ በሕዝቡ ጥያቄ መሠረት የሰዓት እላፊ መታወጁን ጨምረው ተናግረዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ፍቃድ ከተሰጣቸው የጸጥታ አካላት ውጪ የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ ከምሽቱ 2 ሰዓት ጀምሮ ማድረግ መከልከሉን አመልክተዋል። ጨምረውም ሥርዓት አልበኞች የባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪዎችን ተጠቅመው ዓላማቸውን ሊያሳኩ ስለሚችሉ፤ የእነዚህ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ብቻ እንዲሆን መወሰኑን አስረድተዋል።
ከሰሞኑ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ግጭት በመሸሽ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከሰሜን ወሎ አካባቢዎች ወደ ደሴ ተፈናቅሎ እየመጣ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። ከንቲባው “በክልሉ ሰሜናዊ ክፍል በሚካሄደው ጦርነት ምክንያት ነው ሕዝቡ እየመጣ ያለው። ጦርነቱን በመሸሸ ነው ወደ ደሴ የገቡት” ያሉ ሲሆን ለተፈናቃዮች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ ትምህርት ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ተፈናቃዮች በተለያዩ ስድስት ትምህርት ቤቶች እንዲያርፉ መደረጉን አቶ አበበ ተናግረዋል። “የአደጋ መከላከል እና ዝግጁነት አለ። የሰሜን ወሎ አመራርም አለ። ድጋፍ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው” ያሉ ሲሆን የአካባቢው ማኅብረሰብ እና ሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም ተናግረዋል።
መንግሥት ከረቡዕ ጀምሮ ተፈናቅለው ወደ ከተማዋ ለገቡት ሰዎች የተለያየ ድጋፍ ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ ተፈናቃዮችን የሚያስተናግድ በቀበሌ እና በክፍለ ከተማ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ አስፈላጊውን እያደረገ መሆኑን ከንቲባው ገልጸዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ