የኢትዮጵያ መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ህወሓትን ለመደምሰስ እርምጃ እንዲወስዱ አቅጣጫ መቀመጡን ገለጸ።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ “በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የተላለፈ መልዕክትና አገራዊ ጥሪ!” በሚል ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው የአገሪቱ ሠራዊትና የክልል ኃይሎች አማጺው ቡድንን “እንዲደመስሱ” አቅጣጫ መቀመጡን አመልክቷል። የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት ዛሬ ባወጣው በመግለጫ የህወሓት እንቅስቃሴን “ለመደምሰስ” እድሜ እና አቅሙ የሚፈቅድለት በሙሉ የፌደራሉንና የክልል ኃይሎችን እንዲቀላቀሉ ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ለስምንት ወራት በትግራይ ውስጥ ሲያካሂድ የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻ አቁሞ ከአንድ ወር በፊት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከክልሉ ቢወጣም ጦርነቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች መዛመቱ ይታወቃል። የህወሓት ኃይሎች የጥቃት አድማሳቸውን ወደ አጎራባች ክልሎች በማስፋት በአፋርና በአማራ ክልሎች ውስጥ ጥቃቶችን ሲያካሂዱ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በተኩስ አቁም ላይ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል።
አሁን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ በግልጽ የተናጠል ተኩስ አቁሙ እንዳበቃ ባይገልጽም አማጺው ኃይል እወሰደ ያለውን እርምጃና እያደረሰ ያለውን ጉዳት በመግለጽ የፌደራሉና የክልል ኃይሎች እርምጃ እንዲወስዱ ውሳኔ ላይ መድረሱን አመልክቷል። መግለጫው “የአገር መከላከያ ሠራዊታችን፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች፣ ይህንን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሣን የክህደት ኃይልና የውጭ እጆች ስውር ደባን ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳችሁን እንድታሳርፉ አቅጣጫ ተቀምጦላችኋል” ብሏል።
መንግሥት ከሰኔ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ እና በክረምቱ ወራት የግብርና ሥራ እንዲከናወን በሚል የተናጠል የተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ሠራዊቱን መስወጣቱን የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት መግለጫ አስታውሷል። ይሁን እንጂ የህወሓት ቡድን ይህን የተኩስ አቁም አዋጁን ሳይቀበል ቀርቶ በአጎራባች ክልሎች ላይ በፈጸማቸው ጥቃቶች በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳት አድርሷል ብሏል።
በዛሬው መግለጫ መንግሥት በትግራይ ያወጀው የተናጠል የተኩስ አቁም ስለመሰረዙ በቀጥታ ያለው ነገር ባይኖርም የመንግሥት የጸጥታ አካላት ግን በህወሓት ላይ ወታደራዊ እርምጃ የሚወስዱበት “አቅጣጫ” መቀመጡን አመልክቷል። “አገር በመከላከል ዘመቻው ለመሳተፍ እድሜያችሁና አቅማችሁ የሚፈቅድላችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመከላከያ ሠራዊቱን፣ ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመቀላቀል የአገር ዘብነታችሁ የምታሳዩበት ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የጸጥታ ኃይሎችን በቀጥታ ለመቀላቀል ያልተቻለው የኅብረተሰብ ክፍል “ወገቡን አስሮ በልማት ሥራዎች” እንዲሳተፍ የተጠየቀ ሲሆን፤ የመንግሥት ሠራተኛው “በሙሉ አቅሙ ያለ ቢሮክራሲ ሥራውን ያከናውን” ብሏል። መግለጫው ጨምሮም፤ አማጺው “ሰላማዊ ሰዎች አስመስሎ በየአካባቢው ያሠማራቸው ሰላዮችና የጥፋት ተላላኪዎችን ለመከታተልና ለማጋለጥ እንዲቻል፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ዓይንና ጆሮ በመሆን ከጸጥታ አካላት ጋር በቅርበት ሊሠራ ይገባል” ብሏል።
በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ግጭት ከተቀሰቀሰ ጊዜ ጀምሮ ምዕራባውያን አገራት ለህወሓት ወግነዋል ሲል የቆየው የፌደራሉ መንግሥት በዛሬው መግለጫው “ትግላችን . . . ከውጭ አገራት ጋር ጭምር ነው” ብሏል። “ትግላችን ከአሸባሪው ጁንታ ጀርባ ላይ ተፈናጥጠው አገራችንን ለማፈራረስና የኢትዮጵያን ህልውና ለማጨለም ከተነሡ የቅርብና የሩቅ ኃይላትና አገራት ጋር ጭምር ነው” ሲል አመልክቷል።
የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት በመግለጫው የህወሓት ቡድንን የእርዳታ ሥርጭትን እና የእርሻ ሥራን በማስተጓጎል፣ መሠረተ ልማቶች እንደገና ሥራ እንዳይጀመሩ በማደናቀፍ፣ የጤናና የትምህርት ተቋማትን በማውደም፣ የአካባቢ አመራሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል ከሷል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም የሂደቱን ውስብስብ ጠባይና የአሸባሪውን የጥፋት ባህሪ የመገንዘብ ፍላጎት የለውም ያለ ሲሆን፤ “አጥፊውን ኃይል ለራሳቸው አጀንዳ ማስፈጸሚያነት ስለሚፈልጉት፣ እርሱን ለማዳን ሲሉ የመንግሥትን መልካም ጥረት እንዳላዩ ማለፍን መርጠዋል” ብሏል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የህወሓት ኃይሎች በፌደራሉ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት ለወራት ቆይቶ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ከትግራይ ክልል መውጣቱ ይታወሳል። ነገር ግን የህወሓት ኃይሎች የተኩስ አቁሙን ለመቀበል ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው በአጎራባች የአማራና የአፋር ክልሎች ውስጥ ጥቃት በማካሄድ ታሪካዊቷን ላሊበላ ከተማን ጨምሮ አንዳንድ ቦታዎችን መያዛቸው ተዘግቧል።
የህወሓት ኃይሎች አመራር ናቸው እንሆኑ የሚነገርላቸው ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳይ ከሳምንት በፊት ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በኩል ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየሰነዘሩ ያሉት የተኩስ አቁም ለማድረግ ያስቀመጧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች የፌደራሉ መንግሥት እንዲቀበል ጫና ለማሳደር መሆኑን ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ማበቂያ ላይ ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በአጎራባች ክልሎች ውስጥ በሚሰነዝራቸው ጥቃቶች ሳቢያ የፌደራሉን መንግሥት ትዕግስት እየተፈታተነ መሆኑን አመልክቶ ይህንን ለማስቆም መንግሥት ሙሉውን የመከላከያ ኃይሉን በማሰማራት እርምጃ ለመውሰድ እየተገደደ መሆኑን ገልጾ ነበር።