የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት፣ ዩኒሴፍ በአፋር ክልል ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ህጻናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል መባሉ እጅጉን እንዳስደነገጠው ገለጸ።

ድርጅቱ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት ስለተገደሉ ሰዎች የተሰማውን የገለጸው ዛሬ ከኒው ዮርክ በዋና ዳይሬክተሯ ሔኔሪታ ፎሬ በኩል ባወጣው መግለጫ ነው። በክልሉ ውስጥ ባጋጠመው ጦርነት ሳቢያ ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች ተጠልለውበት በነበረው ትምህርት ቤትና የጤና ተቋም ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከ100 በላይ ህጻናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነግሯል።

በጥቃቱ በከፍተኛ ደረጃ የምግብ እጥረት ባለበት አካባቢ የነበረ የምግብ እርዳታ አቅርቦትም መውደሙን የመንግሥታቱ ድርጅት ተቋም ገልጿል። ዩኒሴፍ ጨምሮም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ እየተስፋፋ ያለውን ሰብአዊ ቀውስ ለማስቆም አስቸኳይ ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።

“ከምንም በላይ ደግሞ ሁሉም ወገኖች ህጻናትን ከጉዳት ለመጠበቅ የተቻለቻውን ሁሉ እንዲያደርጉ” ጠይቋል።

አፋር ክልል የተከሰተው ምንድን ነው?

በአፋር ክልል ዞን 4 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በተፈጸመ የከባድ መሳሪያ ጥቃት በርካታ ሰዎች ለሞትና ለጉዳት መዳረጋቸውን የክልሉ ባለሥልጣናት እና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ አስታወቁ። የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ኻሎይታ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአካባቢው እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ‘የህወሓት አማፂያን ናቸው’ በዚህም ሳቢያ ንፁሃን ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

በጥቃቱ የተጎዱ ሰዎች የተወሰዱበት የዱፕቲ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር መሐመድ የሱፍ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሴቶች እና ሕጻናትን ጨምሮ 40 የሚሆኑ ሰዎች በጥቃቱ ጉዳት ደርሶባቸው ለህክምና ወደ ሆስፒታሉ መጥተዋል። ተጨማሪ ተጎጂዎች ይመጣሉ ተብለው ሲጠብቁ የነበሩ ቢሆንም መንገድ ላይ መሞታቸውን መስማታቸውን ዶክተሩ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ 12 ሰዎች መሞታቸውን የሚናገሩት ዶ/ር መሐመድ ሁለት ሰዎች ደግሞ ወደ አዲስ አበባ ለከፍተኛ ህክምና መላካቸውን ጨምረው ተናግረዋል። የተባበሩት መንግሥታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ያወጣውን መግለጫ ተከትሎ የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትዊተር ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ ለጥቃቱ የመንግሥት ሠራዊትን ተጠያቂ በማድረግ ቡድናቸው በክስተቱ ላይ ምርመራ ለማድረግ ከተገቢው አካል እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ እንዳሉት በክልሉ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት በዞን አራት ውስጥ ከ76,000 ሰዎች በላይ ሰዎች ተፈናቅለው በአራት መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ እንደሚገኙ ተናግረዋል። ኃላፊው ጥቃቱ የተፈፀመው ከጦርነት ሸሽተው በጋሊኮማ ጤና ጣቢያ በተጠለሉ ሰዎች ላይ መሆኑን ለቢቢሲ አብራርተዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ተፈናቃዮች በአፋር ክልል በፈንቲ ረሱ ዞን በኩል ጥቃት በመክፈቱ ምክንያት ከያሎ እና ጎሊና ወረዳዎች ከቤት ንብረታቸው በመፈናቀል በጎሊና ወረዳ ጋሊኮማ የምትባል ቀበሌ በጤና ጣቢያ እና ትምህርት ቤት ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የነበሩ ናቸው ተብሏል። ክልሉ እንዳለው በተፈናቃይ አርብቶ አደሮች ተጠልለውበት በነበረው ስፍራ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው በከባድ መሳሪያ መሆኑንና በርካታ ሰዎች ላይ የሞትና የመቁሰል ጉዳት ደርሷል።

በጥቃቱ ምን ያህል ሰዎች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የተጠየቁት አቶ አህመድ ሲመልሱ “በጣም ብዙ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው” ከማለት ውጪ በቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። በጥቃቱ ከባድና እና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ወደ ዱብቲ ሆስፒታል ለሕክምና መወሰዳቸውንም ጨምረው ተናግረዋል። ዶክተር መሐመድ እንደተናገሩት በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸው ተጎጂዎች በፍንዳታ ፍንጥርጣሪ የተጎዱ፣ በጭስ መታፈን እንዲሁም ቃጠሎ የገጠማቸው መሆናቸውን አመልክተዋል።

ወደ ሆስፒታላቸው የመጡ ተጎጂዎች በአጠቃላይ ከባድ ጉዳት የገጠማቸው መሆናቸውን የሚናገሩት ዶ/ር መሐመድ በቃጠሎው እና በጭስ መታፈኑ የተጎዱት ሰዎች ሁኔታ የከፋ እንደነበር ተናግረዋል። የኮምዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ አህመድ እንደሚሉት በጋሊኮማ የገጠር ጤና ጣብያ ከ30 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ይገኙ የነበሩ ሲሆን በደረሰባቸው ጥቃት በርካታ ሴቶችና ሕጻናት ለሞት ተዳርገዋል።

በመጠለያ ጣብያው ከያሎ እና ጎሊና ተፈናቅለው የነበሩ ሰዎች መጠለያ ውስጥ እንደነበሩ ጨምረው ተናግረዋል። በክልሉ አራት ወረዳዎች ያሎ፣ እዋ፣ አውራ ውስጥ አሁንም ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን የሚናገሩት አቶ አህመድ የህወሓት ታጣቂዎች በወረዳዎቹ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች ላይ ውድመት ማድረሳቸውን በመጥቀስ ይከስሳሉ።

ጥቃቱ በደረሰበት አካባቢ የስልክ ግንኙነት እንዳልነበረ የሚናገሩት አቶ አህመድ አርብ ከሰዓት በኋላ ስለ ጥቃቱ መረጃው እንደደረሳቸው ወደ ስፍራው ማቅናታቸውን እና ታጣቂዎቹ ከአካባቢው መደረጉን ገልጸዋል። በጤና ጣቢያው ከዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ከፌደራል መንግሥት የተገኘ የምግብ እህል እንደነበር የጠቀሱት ኃላፊው ይህም በደረሰው ጥቃት ሙሉ በሙሉ መቃጠሉን አስረድተዋል።

የፌደራል መንግሥቱ ሰኔ ወር ማብቂያ ላይ ተናተጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች በአማራና በአፋር ክልል ላይ ጥቃት መክፈታቸው ይታወሳል። ክልሎቹ እንደሚሉት በተፈጸሙ ጦርነቱን በመሸሽ በአፋር ክልል ውስጥ ከ70 ሺህ ሰዎች በላይ እንዲሁም በአማራ ክልል ውስጥ ደግሞ ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች ከቤት ንበረታቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች
የምስሉ መግለጫ, ተፈናቃዮች
ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *