ኢትዮጵያ በአሜሪካ መንግሥት ከ20 ዓመታት በፊት የተሰጣትን ከታሪፍና ከኮታ ነፃ የሚያደርገውን ‹‹አፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት›› (አጎዋ) ተጠቃሚነት ለማሰረዝ የተነሱ፣ እንዲሁም ይህ ዕድል እንዳይሰረዝ የሚታገሉ ቡድኖች መፋጠጣቸው ታወቀ፡፡

የመንግሥት ተቃዋሚ የሆነ አንድ ቡድን ኢትዮጵያን ከ20 ዓመታት በላይ ተጠቃሚ የሆነችበት የአጎዋ ዕድል እንዳይቀጥል ከአንድ ወር በፊት ጀምሮ እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ የአቤቱታ ደብዳቤውንም ለአሜሪካ መንግሥትና ለኮንግረስ ማስገባቱን ሪፖርተር ያገኘው የሰነድ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ለማሰረዝ የሚንቀሳቀሰውን ቡድን ሐሳብ ለማክሸፍ ደግሞ ‹‹አሜሪካን ኢትዮጵያን ፐብሊክ አፌይርስ ኮሚቴ›› የተሰኘ ሌላ ቡድን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይል ኢትዮጵያ ከዕቅዱ ተጠቃሚነት እንድትሰረዝ ያቀረበውን ጥያቄ የአሜሪካ መንግሥት ውድቅ እንዲያደርግ ግፊት እያደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጎዋ ተጠቃሚነት እንድትሰረዝ በአሜሪካ አገር ያሉ የሕወሓት ደጋፊዎች አጎዋን የፖለቲካ መጠቀሚያ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስቀድመው ቡድን ባወጣው ሰነድ አስታውቋል፡፡

ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፌርፋክስ አፍሪካ ፈንድ መሥራች አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ፣ ‹‹አጎዋ በአሁኑ ጊዜ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ቀጥረው የሚያሠሩ የውጭ አገር ባለሀብቶችና አልሚዎች፣ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበት ትልቁ ምክንያታቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመሆኑም አሜሪካ ሆነው ለጊዜያዊ ስሜት መግለጫ ሲሉ ኢትዮጵያ ከነፃ ገበያው እንድትሰረዝ እያደረጉት ባለው እንቅስቃሴ፣ እነዚህ ሠራተኞች ሕይወታቸው ሊበላሽ እንደሚችል ቆም ብለው ማሰብ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ በ2012 ዓ.ም. ብቻ በዚህ የነፃ ገበያ ዕድል ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመቱ ምርቶች ወደ አሜሪካ መላኳን በመግለጽ፣ ከዚህ ተጠቃሚነት ኢትዮጵያ ተሰረዘች ማለት በቀጣይ ተመልሶ ለመግባት ከፍተኛ የሆነ ጥረት የሚጠይቅና በቀላሉ ኤሌክትሪክ አጥፍቶ እንደ ማብራት እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም አጎዋን ተስፋ አድርገው ኢትዮጵያ የመጡ ባለሀብቶችና የኢንዱስትሪ አልሚዎች፣ ይህ ተጠቃሚነት ቢሰረዝና ከአገር ቢወጡ ተመልሰው መምጣታቸው በጣም ከባድ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ እንደ ካልቪን ክለይን፣ ቶሚ ሂልፊገር፣ ኤችኤንድኤም የመሳሰሉ በዓለም ታዋቂ አምራቾች ለመቆየታቸው ዋስትና የለም ሲሉ አቶ ዘመዴነህ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመስፋፋታቸው የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ይህንን ዕድል እንዳታጣ በጥንካሬ ሊሠራበት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *