ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ሕግ የጣሱ የድምፅ አሰጣጥ ሒደቶች ተፈጽሞባቸዋል ባላቸው 28 የምርጫ ወረዳዎች ምርጫው እንዲደገም፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ለፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ ላይ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምላሽ እንዲሰጥ ትዕዛዝ ተሰጠ።
አቤቱታውን እያየው የሚገኘው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሲሆን፣ ትዕዛዙን የሰጠው ኢዜማ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ከጅምሩ እስከ ድምፅ ቆጠራ ድረስ በነበሩት ሒደቶች፣ ከምርጫ ሕግ አዋጅ 1162/2011 እና ቦርዱ ካፀደቀው መመርያ ቁጥር 15/2013 ውጪ በ28 ምርጫ ወረዳዎች (የምርጫ ክልሎች) የተለያዩ ሕገወጥ የሆኑ ተግባራት ተፈጽሞባቸዋል በማለት ምርጫው እንዲደገም ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ ነው፡፡
ኢዜማ ምርጫውን ሲጀምር እንደ መጀመርያ ምርጫ አድርጎ የወሰደው ቢሆንም፣ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ግን ከጅምሩ እስከ የምርጫ ውጤት ገለጻው ድረስ የነበረው ሒደት ግን ካለፉት አምስት ምርጫዎች ያልተለዬ መሆኑን እንዳረጋገጠ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ኢዜማ በተሳተፈባቸው የምርጫ ክልሎች ከፍተኛ የሆነ በደል የተፈጸመበት መሆኑን ጠቁሞ፣ በምርጫ ሕጉ በተቀመጠው መሥፈርት መሠረት የቪዲዮ፣ የሰነድና የሰዎች ማስረጃዎች በማካተት የመጀመርያ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቅሬታውን አስገብቶ እንደነበር አስታውሶ፣ ቦርዱ የሰጠው ምላሽ ግን ሕጉን ያልተከተለና የማይጠበቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በ28 የምርጫ ወረዳዎች ላይ ከድምፅ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ፣ ከቀበሌ እስከ ክልል ባሉ የገዥው ፓርቲ አመራሮች፣ ከቀበሌ ሚሊሻ እስከ ክልል ልዩ ኃይል ድረስ ባሉ የፀጥታ አስከባሪዎች፣ የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈጸሚዎችና ማንነታቸውና ሕጋዊ የሥራ ኃላፊነታቸው በግልጽ ያልታወቀ ግለሰቦች በድምፅ አሰጣጥ ሒደትና በምርጫው ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን ጠቁሟል፡፡
እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን፣ የምርጫ አዋጁንና ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን መመርያዎች በቀጥታ የሚፃረሩ ድርጊቶች መፈጸማቸውን የሚያስረዱ 192 የሰው ምስክሮችና ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን ጨምሮ በቂ ማስረጃዎች በማያያዝ፣ ለይግባኝ ሰሚው ችሎት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማቅረቡ፣ ችሎቱ የቀረበለትን ማስረጃ መርምሮ ቦርዱ ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. መልሱን በጽሑፍ እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጥቷል።
ምንጭ – ሪፖርተር