መንግሥታት በግዛት አንድነታቸውና በሉዓላዊነታቸው ላይ ያነጣጠሩና ከአገር ውስጥ የሚነሱ የውስጥ ጠላቶችን ወይም ከውጭ ኃይሎች የሚሰነዘር ማንኛውም ዓይነት ጥቃት ወይም ወረራ ለመመከት፣ አንድም በተለያዩ የፀጥታ መዋቅሮች ከዚያ ሲያልፍ ደግሞ በመከላከያ ኃይል አማካይነት የአገሩን ዳር ድንበርና የሕዝብን ደኅንነት ይጠብቃሉ፡፡

አልፎ አልፎ ደግሞ ከአቅም በለይ የሆነ ጦርነትና ወረራ በሚያጋጥምበት ወቅት የክተት አዋጅ በማውጣት፣ ሕዝቡ ዳር ድንበሩን እንዲያስጠብቅና ዘብ እንዲሆን ማዕከላዊ መንግሥታት ጥሪ ያቀርባሉ፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ታሪክ ማዕከላዊ መንግሥታት የውጭ ወራሪ ጠላትን ለመውጋት የክተት ዘመቻ ጥሪ ያደረጉባቸውን ዘመናት ማስታወስ ይቻላል፡፡

‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› በሚል መሪ ቃል በተለይ በ19ኛውና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታትና መሪዎች፣ ሕዝቡን ያነሳሱ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ፡፡ በዚህ ረገድ በቀዳሚነት የሚነሱት አፄ ዮሐንስ አራተኛ ናቸው፡፡ በመስከረም 1868 ዓ.ም.  የግብፅ ጦር ሰሜናዊው የኢትዮጵያ ክፍል በወረረበት ወቅት የክተት አዋጅ ማወጃቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

ክተቱ በታወጀ በሁለት ሳምንታት ከሰሜን ኢትዮጵያ አውራጃዎች ሃያ ሺሕ ሠራዊት አሠልፈው በጉንደት ድል ከማድረግ ባለፈ፣ ዳግመኛ የመጣውን የግብፅ ጦር ጉርዓ ላይም መተውታል፡፡ ሌላኛው የንጉሠ ነገሥቱ የክተት ዓዋጅ ምፅዋን በያዘው የጣሊያን ጦር ላይ ቢሆንም፣ በምዕራብ በኩል የሱዳን ማህዲስቶች (ደርቡሽ) ጎንደርን በመውረራቸው ዘመቻው ወደዚያው ሆኗል፡፡

የክተት ጥሪ
በወጣቶቹ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ፉከራና ሽለላ ሲደረግ

ጣሊያን በ19ኛ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ኢትዮጵያን መውረሯን ተከትሎ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሕዝቡን ክተት ያሉበት የዓድዋው ጦርነት ተጠቃሽ ሲሆን፣ በዚህም ንጉሠ ነገሥቱ አንድ መቶ ሺሕ የሚያህል ሠራዊት ከባለቤታቸው ከእቴጌ ጣይቱ ብጡል ጋር አሠልፈው፣ ሠራዊቱን እየመሩ ወደ ሰሜን ዘምተዋል፡፡ ከአርባ ዓመት ቆይታ በኋላም በሁለተኛው የጣሊያን (ፋሺስት) ወረራ ሕዝቡ አገሩን እንዲታደግ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በ1928 ዓ.ም. ክተቱን ማወጃቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

ጎረቤት ሶማሊያ በ1969 ዓ.ም. ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ ‹‹ተነስ፣ ታጠቅ፣ ዝመት›› ብለው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ ችለው ነበር፡፡

በ1990 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትም በተመሳሳይ በማዕከላዊ መንግሥት በኩል የክተት ዘመቻ ነበረ፡፡ ይህ ሁሉ ዘመቻ በኢትዮጵያ መሪዎች በ150 ዓመታት ውስጥ የተከናወነው የክተት አዋጅ የውጭ ባዕዳን ወራሪዎች የአገሪቱን ሉዓላዊነት በጣሱ ጊዜ የወጣ ነው፡፡

የፌዴራል መንግሥት  በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች በትግራይ ክልል በሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ጥቃት ካደረሰሱ በኋላ፣ ለስምንት ወራት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ሲያካሂድ ቆየት  ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ገበሬው ወደ እርሻ ሥራው ተመልሶ፣ እስከ እርሻ ወቅት ማጠናቀቂያ ድረስ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ የተኩስ አቁም በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በተናጠል መታወጁ አይዘነጋም፡፡

ይሁን እንጂ በአሸባሪነት በተሰየመው ሕወሓት መሪነት የሚንቀሳቀሰው ታጣቂ ኃይል የመንግሥትን ውሳኔ ውድቅ በማድረግ፣ በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚገኙ ከተሞችን ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ በመጀመሩ ምክንያት የአማራ ክልል መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በሕወሓት የተሰነዘረው ጥቃት የህልውና ትግል መሆኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሕይወት መስዋዕትነት አስፈላጊውን ለማበርከት ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እዲጠባበቅ የሚል ጥሪ አቅርቦ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት ከሰሞኑ በአማራ ክልል ውስጥ ማንኛውም የመንግሥትና የግል መሣሪያ የታጠቀ፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ሁሉ ከሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለክተት ዘመቻ እንዲነሳ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ለክልሉ ሕዝብ መልዕክት ያስተላለፉት ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡

የክልሉ ፕሬዚዳንት ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልከተው በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አሸባሪው ትሕነግ በተለያዩ ግንባሮች ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ የማጥቃት ሙከራ እያደረገ ነው፡፡ ሕዝቡ ከጎናችን እንዲሆን ባስተላለፍነው መልዕክት በአሁኑ ወቅት በሁሉም ረገድ ከጎናችን በመሆኑ ለመላው የክልሉና የኢትዮጵያ ሕዝብ ምሥጋና ይገባዋል፤›› ብለዋል። ‹‹ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል ማሠለፍና ሎጂስቲክስ ያስፈልጋል፤›› ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ‹‹የክልሉ ሕዝብና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ያሳዩት ምላሽ የሚደነቅና ክልሎች እያደረጉት ያለው ድጋፍም ታሪካዊ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ የተጀመረው ዕርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማስታወቅ፣ ‹‹ጦርነቱ የአማራን ሕዝብ ዓልውና የምንታደግበት በመሆኑ የህልውና ጦርነቱን በአሸናፊነት ለመጨረስ የአማራ ሕዝብ አስተዋጽኦ የጎላ መሆን ይኖርበታል፤›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ‹‹አገር የማፈራረስ ዓላማ ያለውን ኃይል በተባበረ ክንድ በመደምሰስ ፀረ ኢትዮጵያ የሆነውን ከሀዲ ቡድን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት ሁሉም መነሳት አለበት፤›› ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አቶ አገኘሁ በመግለጫቸው ‹‹የአማራን መሬት ለወያኔ እሾህ እናደርገዋለን፣ በየትኛውም አቅጣጫ ሊንቀሳቀስ እይችልም፣ ለዚህ ሁሉም በየደረጃው መደራጀት አለበት፣ ወደ ግንባርም መሄድ እንዳለበት፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ሰኔ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት አራተኛ ልዩ ስብሰባ ላይ፣ በትግራይ ክልል በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምንም ዓይነት የክተት ዘመቻ እንዳልተጠራ በመግለጽ፣ ነገር ግን አስፈላጊ ከሆነ በሁለት ሳምንታት ብቻ ከሁለትና ሦስት ክልሎች ውስጥ ከ100 ሺሕ ልዩ ኃይል ውስጥ የሠለጠነ፣ የታጠቀ፣ የተደራጀና የተቀመጠ ኃይል በመኖሩ ማውጣት ይቻላል ብለው ነበር፡፡

አክለውም ይህም አይበቃምና ሚሊሻ ነው የሚያስፈልገው ከተባለ፣ በአንድና በሁለት ወራት ውስጥ ግማሽ ሚሊዮን ሚሊሻ ከሞላ ጎደል የታጠቀና መተኮስ የሚችል ኃይል ማውጣት ይቻላል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር በመሆኗ ሌላ አንድ ሚሊዮን ወጣት ቀስቅሶና አሠልጥኖ ማሰማራት አንደሚቻል ገልጸው ነበር፡፡

ነግር ግን ከቀናት በፊት የአማራ ክልልን የክተት ጥሪ አስመልክቶ፣ በርካቶች በመንግሥታት ታሪክም ሆነ አወቃቀር የአማራ ክልል የጠራው የክተት ጥሪ አግባብነት ላይ አስተያየቶች ይሰማሉ፡፡

በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተማራማሪና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ መምህር ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ሲያደርግ የሕወሓት ታጣቂዎች ያራመዱት አቋም በተለይም ሒሳብ እናወራርዳለን በሚል መልዕክት ፀብ አጫሪ ንግግሮችን እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ በመዛት ጭምር በአደባባይ ወጥተው በአማራ ክልል ላይ ያረጉት ትንኮሳ፣ የአማራ ክልልን ለክተት ጥሪ ካነሳሱት አስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን አክለዋል፡፡

በዚህም የአማራ ክልላዊ መንግሥት ለሚመጣበት ጥቃት ራሱን መከላከል እንዳለበት፣ ማንም አካል ጠላት ሲመጣበት ሊያደርገው በሚችለው ሁኔታ መቆም ካልቻለ ጠላትን ኑ ቁጭ ብለን እንደራር ሊል እንደማይችል፣ እንዲሁም ከዚያኛው ወገን ሊመጣ የሚችለውን ጥቃት ሊቋቋም የሚችል አቅም ለመፍጠር የክተት ጥሪ ማድረግ ያስገድደዋል ብለዋል፡፡

ከትግራይ ክልል በኩል የሚታየው አካሄድ በልዩ ኃይል ወይም በክልሉ መንግሥት ፀጥታ መዋቅር ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን፣ ሕፃናትንና ሽማግሌዎችንም ጭምር በአጠቃላይ ሰብዓዊ ማዕበል (Human Wave) በሚመስል ሁኔታ ሲመጣ በጦርነት ወቅት ቁጥር በጣም ተፅዕኖ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአማራ ክልል ላይ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ በመፍጠር ሥጋት ውስጥ እንዲገባ ከማድረግ ባለፈ፣ የክልሉን ማኅበረሰብ ህልውና ሊፈታተን የሚችል መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹በዚህም የህልውና ምክንያት የተነሳ የመጣውን ኃይል ለመመከት ከ18 ዓመት በላይ የሆነ የክልሉን ማኅብረሰብ ለክተት ዘመቻ ጥሪ ነው የቀረበው፡፡ ወገን ከመጣው ኃይል ጋር ስታነፃፅረው ትክክለኛ ውሳኔ ነው ብዬ ነው የማስበው፤›› ሲሉ የዓለም አቀፍ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ተማራማሪው ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል የመጣውን ጦር ለመመለስ እንቅስቃሴ ለማድረግ አንድም ያወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም ማንሳት አለበት ብለው፣ የሕወሓት አመራሮች ያቀረቡትን በቅደመ ሁኔታ የታጠረ መደራደሪያ ፌደራል መንግሥት ባለመቀበሉ ትንኮሳው ሲቀጥል ለአማራ ክልል እንደ አማራጭ ያለው የክተት ጥሪ ማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ የተነሳ የፌደራል መንግሥት ለአማራ ክልል ተጨማሪ ድጋፍ እስካላደረገ ድረስ፣ ክልሉ ሌላ አማራጭ ስለሌለው በወታደራዊ  ሕግ  ሲተነተንም የክተት ጥሪ መቅረቡ ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ የአማራ ክልላዊ መንግሥት እንደ መንግሥት የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ የመጠበቅ ግዴታ ያለበት በመሆኑ፣ በክልሉ ሕገ መንግሥት መሠረት የሕዝቡ ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ምንም እንኳ እየታየ ያለው ጉዳይ የመጠፋፋት አንድምታ ያለውና በቀጣይ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦችን የቆየ የጋራ ታሪክና መስተጋብር የሚያበላሽ ቢሆንም፣ የአማራ ክልል ራሱን ለመከላከል እያደረገ ያለው ጥረት ትክክል አይደለም ተብሎ ሊወሰድ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል የክተት ጥሪ ድሮ ከነበረው የአፄ ዮሐንስ ወይም የአፄ ምኒልክ ዘመን ዕይታ ወጣ በማድረግ በተለየ መንገድ ማየት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ስሜነህ ኪሮስ አሰፋ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

በዚህም በአፄዎች ዘመን የነበረው የውጭ ወራሪ እንደበርና አሁን ግን ችግር እየተፈጠረ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ነው ብሎ በሰየመው የሕወሓት ቡድን በመሆኑ፣ የአማራ ክልል እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ራሱን ለመከላከል ነው ይላሉ፡፡ የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጓል፡፡ ነግር ግን የአማራ ክልል የክተት ጥሪ ሲታሰብ አንደኛ የክተት ትርጉም ድሮ በነበረው ዓይነት ትርጉም በቀጥታ ሊታይ እንደማይችል፣ ሁለተኛ በአሁኑ ጊዜ ሉዓላዊነት የፌደራል ቅርፅ ስለያዘ የክልልና የፌደራል ሥልጣን ተብሎ የተለየ በመሆኑ ምክንያት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ስሜነህ (ዶ/ር) አክለውም በድሮው ዘመን አፄ ዮሐንስ ወይም አፄ ምኒልክ ክተት ሲያውጁ የውጭ ጠላት ወራሪ በመምጣቱ የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለመጠበቅ መንግሥታቱ መደበኛ ሠራዊት ስለሌላቸው፣ ሕዝቡን ክተት ሲሉ ወንዶች ታጥቀው ሴቶች ሰንቅ እያቀረቡ ውጊያ ይደረግ ነበር ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን ግን የአማራ ክልል የክተት ጥሪው የክልሉን ሕዝብ በመጥራት ክልሉን ለመጠበቅ፣ በሌላ በኩል ትግሉ ሽብርተኛ ተብሎ ከተሰየመው ድርጅት ጋር በመሆኑ በዚህ ቋንቋ ሕወሓት ወራሪ ኃይል ተብሎ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በተጨማሪም ሕወሓት ራሱን ችሎ ሳይሆን የመጣው የትግራይን ሕዝብ አሞኝቶም አባብሎም የሰው ማዕበል ይዞ የአማራ አካባቢዎችን ለመውረር ነው፡፡ የአማራ ክልል የተነሳበት ክተት የሚለው ጥሪ በዚህ አካሄድ መደበኛ ትርጉም እንደማይሰጠው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም የአማራ ክልል የመጣበትን ጥቃት ለመመለስ ራሱን ማደራጀቱ አግባብነት እንዳለው  ስሜነህ (ዶ/ር)  በአፅንኦት አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የክልሉ መንግሥት ያወጣውን የክተት ጥሪ አስመለክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ጥሪው ዘግይቶ የመጣ ቢሆንም የአማራ ክልል መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የህልውና ሥጋት የተጋረጠበትን አገረ መንግሥትና በጠላትነት የተፈረጀውን ሕዝባችን ለመታደግ ያወጀውን የክተት ጥሪ በሙሉ ልብ እንቀበለዋለን፤ ብሎ ለተግባራዊነቱም የበኩሉን ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

አብን መላው የድርጅቱ አመራሮች፣ አባላት፣ ደጋፊዎቻችና እንዲሁም ሕዝቡ ይህን ጥሪ በመቀበል በየደረጃው ካለው መንግሥታዊ መዋቅር ጋር በመቀናጀት የክተት ዘመቻውን እንዲቀላቀል ጥሪ አድርጓል:: የአገር መከላከያ ሠራዊት ምንም እንኳ የተናጠል ተኩስ አቁም ላይ ቢሆንም፣ ከአማራ ክልል የተደረገውን ጥሪ በመቀበል ወደ ክልሉ ከተላኩት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ልዩ ኃይል በተጨማሪ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በርካታ ከክልሎች የተውጣጡ ወጣቶች የአገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ሽኝት እየተደረገላቸው ነው፡፡

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *