ከሁለት የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን የተውጣጡ የሚዲያ ሠራተኞችን ጉዳይ በተመለከተ አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታ እየተመለከተ ያለው ፌደራል ፍርድ ቤት፤ ፖሊስ በፈንታሌ ወረዳ ጋዜጠኞቹን ለግዜ ቀጠሮ ማቅረቡን የሚያስረዳ ሰነድ እንዲልክ ትዕዛዝ ሰጠ።
በእስር ላይ ያሉት 14 የመገናኛ ብዙኃን ሠራተኞች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ጠበቆች እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ሊያገኟቸው ባለመቻላቸው እና ታስረው በነበሩበት አካባቢ ባለ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ተከትሎ ነበር አካልን ነጻ የማውጣት አቤቱታው የቀረበው።
ፖሊስ ሰኞ በችሎት ቀርቦ የግዜ ቀጠሮ እንዲፈቀድለት ያቀረበውን አቤቱታ የሚያስረዳ ሰነድ ለችሎቱ ያቀረበ ሲሆን፤ ጋዜጠኞቹ ከ24 ቀናት በኋላ የት እንደሚገኙ አስታውቋል። ፍርድ ቤት የግዜ ቀጠሮውን የፈቀደበትን ሰነድ ፖለስ ይዞ ባለመቅረቡ ለትላንት ሃሙስ ይህንኑ ሰነድ እንዲያቀርብ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር። በዚህም መሠረት ፖሊስ ከአፋር ክልል፣ ፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት ግዜ ቀጠሮ ተፈቅዶበታል ያለውን ሰነድ አቅርቧል።
ፌደራል ፖሊስም ባለ ስምንት ገጽ ሰነድ ለችሎቱ አቅርቧል። ማስረጃዎቹ ለፖሊስ የተሸኙበት ደብዳቤም የግዜ ቀጠሮ ትዕዛዙ 19/11/2013 ዓ. ም. የሰጠ መሆኑን ያመላክታል። በእስር ላይ ያሉት 14 የሚዲያ ሠራተኞችም በሶሦስት የተለያዩ መዝገቦች ተከፍለው ለግዜ ቀጠሮ ችሎት መቅረባቸውን እና ፖሊስ የጠየቀው ግዜ መፈቀዱን የሚያሳዩ ሦስት የተለያዩ ሰነዶችን ፖሊስ ለችሎቱ አቅርቧል።
ምንም እንኳን የመሸኛ ደብዳቤው የግዜ ቀጠሮ ትዕዛዙ ሐምሌ 19 ተሰጠ ቢልም፤ በውስጥ የተያያዙት የፍርድ ቤት ግልባጭ ማስረጃዎች ግን ግዜ ቀጠሮው ሰኔ 29 የተሰጡ ትዕዛዞች መሆናቸውን ያመለክታሉ። በእስር ላይ የሚገኙት ጋዜጠኞች ጠበቃም በችሎት ፌደራል ፖሊስ ያቀረበው ሰነድ ተአማኒነት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ችሎቱ ሰኞ ሐምሌ 19 ማስረጃ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ የፈንታሌ ወረዳም የግዜ ቀጠሮ ትዕዛዙን በተመሳሳይ ቀን ሰጥቻለሁ ሲል በመሸኛ ደብዳቤው ላይ መገልለጹ ይቃረናል ሲሉ ጠበቃው ተከራክረዋል።
እንዲሁም በዝርዝር ማስረጃው ላይ በተጠቀሰው መሠረት ሰኔ 29 የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ከአንድ ሳምንት በፊት የሚጠናቀቁ እና ፖሊስ ሰኞ በችሎቱ የግዜ ቀጠሮ ጠይቄበታለሁ ብሎ ካቀረበው ማስረጃ ጋር ይቃረናል ሲሉም ጠበቃው ሞግተዋል። ፖሊስ ለመጨረሻ ግዜ ሐምሌ 12 ጋዜጠኞቹን በፈንታሌ ወረዳ አቅርቤ ተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ግዜ ተፈቅዶልኛል ሲል ግዜ ቀጠሮ የጠየቀበትን ሰነድ ለችሎቱ ማያያዙ ይታወሳል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ ለፈንታሌ ወረዳ ፍርድ ቤት እና ለአመልካች ትዕዛዛ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞቹን ጉዳይ ይዞ ከሆነ እና እነሱን በተመለከተ የተሰጠ ውሳኔ ግልባጭ እንዲላክ ትዕዛዝ አሳልፏል።
ምንጭ – ቢቢሲ