የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፤ ሱዳን ወታደሮቿን ከኢትዮጵያ ግዛት እንድታስወጣ ዓለም አቀፉ ማሳሰብ እንዳለበት ተናገሩ።

አምባሳደር ዲና ሳምንታዊ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫቸውን ዛሬ ሲሰጡ፤ ሱዳን እአአ በ1972 በሁለቱ አገሮች መካከል የተደረገውን ስምምነት እንድትከተል አሳስበዋል። የሱዳን ጦር በኢትዮጵያ ድንበር አካባቢ ድልድዮችን እና ወታደራዊ ሰፈሮችን ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ይህንንም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እያሳወቁ መሆኑን አክለዋል።

ሱዳን ከዚህ እንቅስቃሴ መታቀብ እንዳለባት ገልጸው፤ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው አለመግባባት መፈታት ያለበት በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነም ተናግረዋል። ሱዳን እና ኢትዮጵያ በድንበር ጉዳይ ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ወራት ተቆጥረዋል።

አምባሳደር ዲና በዛሬው መግለጫቸው ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ፤ ከግብጽ እና ከሱዳን ጋር 2015 ላይ በደረሰችው የሦስትዮሽ ስምምነት መሠረት የግድቡን ግንባታ መቀጠሏን አንስተዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ጦርነት በተመለከተ፤ የፌደራል መንግሥቱ የተኩስ አቁም ቢያደርግም የህወሓት ኃይሎች “በአማራ እና በአፋር ክልሎች ጥቃት መሰንዘራቸው የተኩስ አቁሙን ውሳኔ የሚፈትን” መሆኑን ጠቁመዋል።

“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ህወሓት የተኩስ አቁሙን እንዲያከብር ጫና ማሳደር አለበት” ብለዋል። የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ካነሷቸው ነጥቦች መካከል በግጭት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ጉዳይ ይጠቀሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በግጭት ከተጎዱ አካባቢዎች መካከል ለጂሌ ጢሙጋ እና ኤፍራታ ግድም ወረዳዎች መልሶ ግንባታ እንዲውል ለእያንዳዳቸው 200,000 ብር መስጠቱም ተጠቁሟል።

የሳዑዲ ተመላሾች ጉዳይ

ኢትዮጵያ በአንድ ወር ውስጥ 42,000 ዜጎችን ከሳዑዲ አረቢያ ወደ አገር ቤት መመለሷ ተገልጿል። ይህም 84 በመቶ ወንዶች እና 16 በመቶ ሴቶችን ያካተተ ነው ተብሏል። ከስደት ተመላሾች ወደ ትውልድ ቀያቸው እንዲመለሱ የሚደረግ ሲሆን፤ አሁን ላይ በትግራይ ባለው ቀውስ ሳቢያ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ከስደት ተመላሾችን ወደ አካባቢው ለመመለስ አዳጋች እንደሆነ ተገልጿል።

አዲስ አበባ ውስጥ ስምንት የስደተኞች መቀበያ ማዕከሎች እንደተቋቋሙና፤ የሳዑዲ ተመላሾች ወደ መዳረሻቸው እስኪሄዱ ድረስ በማዕከሎቹ እንደሚቆዩ ተነግሯል። ከስደት የተመለሱ ዜጎች የአካላዊ ጤናና የሥነ ልቦና ክትትል እንደሚደረግላቸው ተጠቁሟል።

ከዚህ በተጨማሪ ከቤተሰቦቻቸው የተለያዩ ልጆች፣ ልጆች ያላቸው እናቶች፣ የሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሰዎች ልዩ ክትትል የሚያገኙባቸው ማዕከሎች እንዳሉ ተገልጿል። ኢትዮጵያ እአአ ከ2017 ወዲህ ከሳዑዲ ያስመለሰቻቸው ዜጎች ባጠቃላይ 415,000 ይደርሳሉ።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *