የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው የነበሩት የትግራይ ኃይሎች በድርድር ላይ የተመሰረተ ተኩስ አቁም ለማድረግ የተሻሻለ አዲስ ቅድመ ሁኔታ አቀረቡ።

በወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ “የትግራይ መንግሥት አቋም” በሚል የወጣው መግለጫ፤ “በፍጥነት እየተቀያየረ ያለው ወታደራዊ እና ፖሊቲካዊ ሁኔታ በአገሪቱ ሰላም እና ደኅንነት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተጽእኖ ከግምት በማስገባት የትግራይ መንግሥት ከዚህ ቀደም የተኩስ አቁም ለማድረግ ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሻሻል አስፈልጎታል” ብሏል።

ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎቱን አለኝ ያለው ህወሓት፤ ዳግም ባወጣው የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይት እና የሽግግር ሂደት እንዲካሄድ ጥሪ አቅርቧል። የአቋም መግለጫው የትግራይ መንግሥት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎቱን እና ምርጫውን ሲያንጸባርቅ ቆይቷል ብሏል።

የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ትግራይን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች በርካታ የክልሉን ስፍራዎች ተቆጣጥረው የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎችን ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ማውጣታቸው ይታወሳል።

ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በወጣው ቅድመ ሁኔታ ላይ በኤርትራ ወታደሮች እና በአማራ ኃይሎች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግባቸው እና እነዚህ ኃይሎች የትግራይ ስፍራዎችን ለቀው ይውጡ ብሎ ነበር።

የተቋረጡ መሠረተ ልማቶችን መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ፣ ዓለም አቀፍ በረራዎች ትግራይ ከሚገኙ አየር ማረፊያዎች በቀጥታ በረራ ያደርጉ፣ ያለ ምንም ገደብ የሰብአዊ እርዳታ የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻች እና የክልሉ በጀት እንዲለቀቅ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርቦ ነበር።

በአዲሱ ቅድም ሁኔታ ህወሓት ምን አለ?

ዛሬ የአቋም መግለጫው ይፋ የተደረገው በፓርቲው ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ይፋዊ የትዊተር ገጽ ሲሆን፤ ከአቋም መግለጫው በታች ሐምሌ 20/2013 ዓ.ም. የሚል ቀን ተመልክቷል።

የትግራይ መንግሥት ወቅታዊ የአቋም መግለጫ በሚል ርዕስ በወጣው መግለጫ ላይ፤ “አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገሪቱን መምራት የሚያስችለው ሕገ መንግሥታዊ መብት የለውም” ካለ በኋላ፤ በአገሪቱ የተከሰተውን ፖለቲካዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ችግሮችን ለመፍታት ዋና የፖለቲካ ተዋናዮችን ያቀፈ አካታች ፖለቲካዊ ሂደት እና የሽግግር ሥርዓት እንዲካሄድ ጥሪ እናቀርባለን ይላል የመጀመሪያው ነጥብ።

ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ መንግሥት በድርድር የሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላታቸው አለባቸው ሲል ከዚህ ቀደም ካወጣው የአቋም መግለጫ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ስድስት ነጥቦችን ዘርዝሯል። ከእነዚህ ነጥቦች የመጀመሪያው በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮምዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤና እና የንግድ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት መጀመር አለባቸው የሚለው ነው።

የአገር መከላከያ አባላት የሆኑትን ጨምሮ ማንነታቸውን መሠረት ተደርጎ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ፤ በመላው አገሪቷ የትግራይ ተወላጆች የጅምላ እስር ይቁም ይላል። የ2013 ዓ.ም. እና የ2014 ዓ.ም. በጀት በፍጥነት መለቀቅ አለበት፣ የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ይውጡ (ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጋገጥ አለበት) ብሏል።

የሰብዓዊ እርዳታ ለማድስ ለሁሉም አይነት የትራንስፖርት አማራጮች በርካታ መተላለፊያ ኮሪደሮች ክፍት መደረግ አለባቸው የሚሉት ቅድመ ሁኔታዎች በአቋም መገለጫው ላይ ሰፍሯል። የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ተፈጻሚ ሆነው ይህም በአገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት ይላል መግለጫው።

በህወሓት የሚመራው የክልሉ መንግሥት ከመንበሩ ከተወገደ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የአገሪቱ ፌዴራል መንግሥት “ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ” የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቀረቡ ይታወሳል።

የፌደራሉ መንግሥትም የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጥያቄ ተቀብሎ በክልሉ የሚገኙ አርሶ አደሮች በክረምቱ ወራት የእርሻ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እና የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ እንዲቻል የተናጠል ተኩስ አቁም አውጃለሁ ብሎ ነበር።

የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የነበረው የህወሓት ኃይሎች በአገሪቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ ከሥልጣኑ ተወግዶ የነበረ ሲሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የክልሉን አስተዳደር ሕገወጥ ብሎ መበተኑ ይታወሳል። ከጥቂት ወራት በፊትም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የክልሉ ገዢ ፓርቲ የነበረውን ህወሓትን ሽብርተኛ ቡድን ብሎ ሰይሞታል።

የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ካስወጣ በኋላ ወደ መቀለ ተመለሱት የህወሓት አመራሮች ግን “በሕዝብ የተመረጥን ሕጋዊ የክልሉ አስተዳዳሪዎች ነን” ማለታቸው ይታወሳል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *