ባለፈው ቅዳሜ በአፋር እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በሆነ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ቦታ በተፈፀመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን የሶማሌ ክልል ኮምዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ ለቢቢሲ ገለጹ።

የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ሮብሌ እንዳሉት ቅዳሜ ሐምሌ 17/2013 ዓ.ም በአፋር ክልል ሥር በሚገኘው እና በርካታ የሶማሌ ብሔር ተወላጆች ይኖሩበታል ባሉት ከተማ በንጹሃን ሰዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ300 በላይ ሰዎች ሞተዋል። የተባበሩት መንግሥታትን ይፋ ያልተደረገ ሪፖርተ ተመልክቻለሁ ያለው ሮይተርስ የዜና ወኪል ክስተቱን በሚመለከት ሪፖርቱ ገዳማይቱ ተብላ በምትጠራው ከተማ ግጭት ተከስቶ በሁለቱም ወገን ጉዳት መድረሱን ያመላክታል ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም ስማቸው ያልተጠቀሰ ሁለት የሶማሌ ክልል ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በግጭቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ እንደነገሩት ሮይተርስ ዘግቧል። ስለ ጉዳዩ ከአፋር ክልል በኩል መረጃ ለማግኘት ወደተለያዩ የክልሉ ባለሥልጣናት ስልክ በተደጋጋሚ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።

ጥቃት ተፈፀመበት ያሉትን ገብረኢሴን ከተማን ጨምሮ ፎና እና አደይቱ የሚባሉ ከተሞች በሁለቱ ክልል የይገባኛል ጥያቄ እንደሚነሳባቸው ያስታወሱት የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ፤ የዚህ ጥቃት መንስኤም ይኸው የይገባኛል ጉዳይ ነው ይላሉ። “በጸብ ጫሪነት የሚካሄድ ግጭት ነው ያለው። በገብረኢሴን ከተማ ሙሉ በሙሉ ሶማሌዎች ናቸው የሚኖሩበት። አፋሮች ገብረኢሴን፣ ፎና እና አደይቱ የኛ ናቸው ይላሉ” በማለት ያስረዳሉ።

እነዚህ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሱባቸው ቦታዎች አዲስ አበባን ከጂቡቲ የሚያገናኘው መንገድ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ኃላፊው፤ የአፋር ታጣቂዎች ቅዳሜ ዕለት ጥቃት ከማድረሳቸው በፊትም በከተማዋ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጸዋል። በጥቃቱ በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን የተጠየቁት ምክትል ኃላፊው፤ ቁጥሩን በውል ማወቅ ባይቻልም፤ “ከ300 በላይ ሰዎች መገደላቸውን” ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰሙ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ሽሽት ወደ 700 የሚጠጉ ሰዎች ወደ አገር መከላከያ ካምፕ ገብተው እንደነበረ እና ከትናንት በስቲያ [ሰኞ] ነዋሪዎቹ ከተሸሸጉበት እንደወጡ አክለዋል። ከተማዋ አሁንም በአፋር ታጣቂዎች ስር ትገኛለች ያሉት ምክትል ኃላፊው ወደ ከተማዋ ዘልቀው መግባት ባለመቻላቸው በጥቃቱ በትክክል የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ አልቻልንም ብለዋል።

ጥቃቱን የተፈፀመው በአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎችና ኡጉጉሙ በሚባል ታጣቂ ቡድን ነው ሲሉ ምክትል ኃላፊው ይከሳሉ። በዚህ ጥቃት የተቆጡ የሶማሌ ተወላጅ ወጣቶች ጂቡቲን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘውን የመኪና መንገድና የባቡር መስመር ዘግተው እንደነበር መረጃው አለኝም ብለዋል። የተዘጋውን የመንገድ እና የባቡር መስመር ለማስከፈት የሶማሌ መንግሥት ባለስልጣናት እና የአገር ሽማግሌዎች ጥረት ማድረጋቸውን አቶ መሐመድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አሁንም በከተማዋ አለመረጋጋት እንዳለ የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ ከጥቃቱ ተርፈው ከከተማው እንዲወጡ ለተደረጉ ሰዎች ጊዜያዊ እርዳታ እየተደረገ እንደሆነና የተጠፋፉ ቤተሰቦችን ለማገናኝትም የማፈላለግ ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ከአፋር ክልል መንግሥት ምላሽ ማግኘት ባይቻልም ከትናንት በስቲያ ሰኞ በገብረኢሴ ከተማ ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ መንገድ ተዝግቷል መባሉን ተከትሎ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የአፋር ክልል ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ካሎይታ፤ “ጁንታው መንገድ ዘግተናል እያለ ፕሮፖጋንዳ እያስራጨ ነው፤ ይህ ሐሰት ነው” ያሉ ሲሆን በአፋር ታጣቂዎች ተፈጽሟል ስለተባለው ጥቃት ግን ያሉት ነገር የለም።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *