የአፋር ክልላዊ መንግሥት ነዋሪዎች ታጥቀው የትግራይ አማፂያንን እንደሚክቱ ጥሪ አቅርቧል ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘገበ።

“እያንዳንዱ አፋር መሬቱን በተቻለው መንገድ ሊጠብቅ ይገባል። በጥይትም ይሁን፣ በዱላ አሊያም በድንጋይ” ሲሉ የክልሉ ፕሬዝደንት አዎል አርባ ተናግረዋል ሲል ኤኤፍፒ አስነብቧል። “የትኛውም መሣሪያ ዝቅ እንድንል ሊያደርገን አይችልም። ይህንን ጦርነት በጠንካራ ኃይላችን እንረታዋለን።” የአማራ ክልል ብሔራዊ መንግሥት የህወሓት አማጺያንን ለመውጋት የክተት አዋጅ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል።

የህወሓት አማፂያን ትግራይ እና አፋር ድንበር አቅራቢያ ጥቃት ስለመክፈታቸው በስፋት ተዘግቧል። የአፋር ክልል አደጋ መከላከል ኃላፊ ባለፈው ሳምንት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች በግጭቱ ተፈናቅለዋል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር። ኤኤፍፒ ደግሞ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ከ20 በላይ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል ሲል ዘግቧል።

የአማፂያኑ ቃል አቀባይ ግታቸው ረዳ በአፋር ክልል ያለውን ኦፕሬሽን ለመንግሥት ወግነው አፋር ክልል ውስጥ በሚዋጉ የኦሮሚያ ልዩ ኃይሎች ላይ የተሰነዘረ “በጣም የተገደበ” ጥቃት ነው ብለው ነበር። ነገር ግን የአፋር ክልል ፕሬዝደንት ይህ ሃሰት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

“አንዳንድ ሰዎች አማፂያኑ የወረሩን የኦሮሚያ ልዩ ኃይልን ስላስጠለልን ነው ብለው ያስባሉ። ነገር ግን ይህ ከእውነት የራቀ ነው። እነሱ ከኢትዮጵያ በኃይል ሊገነጥሉን ይፈልጋሉ” ብለዋል። በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል ፕሬዝደንት ሕዝቡ መሣሪያውን በመታጠቅ የሕወሓት ኃይሎችን “እንዲመክት” ጥሪ አቅርበዋል።

ፕሬዝደንቱ በክልሉ ቴሌቪዥን ቀርበው ባወጁት ክተት “በመንግሥትም ሆነ በግላቸው መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ዘመቻውን እንዲቀላቀሉ” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ፕሬዝደንት አገኘሁ ተሻገር “ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግ ነው” ሲሉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

በተያያዘ ዜና በ6ኛው አገራዊ ምርጫ የፖርላማ መቀመጫ ካሸነፉ ጥቂት ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በአማራ ክልል መንግሥት የታወጀውን የክተት አዋጅ ጥሪን ተቀብያለሁ ብሏል።

ፓርቲው “. . . በጠላትነት የተፈረጀውን ህዝባችን ለመታደግ የአወጀውን የክተት ጥሪ በሙሉ ልብ የምንቀበለውና ለተግባራዊነቱም የበኩላችን ከፍተኛ ጥረት የምናደርግ መሆኑን እየገለፅን የክልሉ መንግስትም አልፎ አልፎ የሚታዩ አስተዳደራዊ ችግሮችን በመፍታት የመሪነት ሚናውን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ እንጠይቃለን” ብሏል ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ።

የድጋፍ ሰልፎች

ትናንት እና ከትናንት በስቲያ በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች ሰልፎች ተካሂደዋል። የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በጎንደር ዙሪያ ወረዳ፣ በዳንሻ ከተማ፣ በጎንደር እና እንጅባራ ለአገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፉ እና ህወሓትን የሚቃወሙ ሰልፎች መካሄዳቸውን ዘግቧል። የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ለአገር መከላከያ ሠራዊት አጋርነትን ለማሳየት ያለመ ህዝባዊ ሰልፍ በአፋር ክልል ሰመራ-ሎግያ፣ አይሳኢታና አበአላ ከተሞች መካሄዱን ዘግቧል።

በሠመራ-ሎግያ ከተማ በተካሄው ሰልፍ ላይ በከተማው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ተሳትፈውበታል ሲል ኢዜአ ጨምሮ ዘግቧል። ከቀናት በፊት በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ የተካፈለበት የአገር መከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ እና ህወሓትን የሚቃወም ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል።

ስምንት ወራት የዘለቀው በሕወሓትና በመንግሥት መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ከትግራይ አልፎ ወደ ሌሎች ክልሎች እየተስፋፋ ነው። የተባበሩት መንግሥታት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በዚህ ግጭት ሞተዋል፤ በመቶ ሺዎች የሚሆኑ ደግሞ ለረሃብ አደጋ ተጋልጠዋል ይላል። የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅ አውጆ ከትግራይ አካባቢዎች ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የህወሓት አማጺያን የክልሉን በርካታ ስፍራዎች መልሶ መያዝ ችሏል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *