በአማራ ክልል ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ሁሉ ከሰኞ ሐምሌ 19/2013 ዓ.ም ጀምሮ እንዲዘምት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ጥሪ ማስተላለፋቸውን አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እሁድ ዕለት ባስተላለፉት የክተት ጥሪ “የመንግሥትን መሳሪያ የታጠቀ፣ የግል መሳሪያ የታጠቀና ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ሁሉ ለህልውና ዘመቻ እንዲዘምት” ብለዋል። አክለውም “በክልላችን በሁሉም ቀበሌ የሚገኝ አካላዊ ሁኔታው ለግዳጅ ብቁ የሆነ፣ ለጦርነት ብቁ የሆነ ወጣት በሙሉ ከነገ ጀምሮ በየወረዳ ማዕከል እንዲከት” በማለት ጥሪ አድርገዋል።

በዚህም መሰረት ብቁ የሆነው ወጣት ሁሉ ወደ ወረዳ ማዕከል እንደሚገባ፣ የግዳጅ ቀጠናውና የግዳጅ ግንባሩ እንደሚነገረው ተነግሯል። “ህወሃት የሚከተለውን ስትራቴጂ ተጠቅመን እኛም ህወሃትን እንፋለመዋለን” ብለዋል። ሁሉም ሰው ለክተት ጥሪው አዎንታዊ ምላሽ መስጠት አለበት በማለት ርዕሰ መስተዳድሩ አፅንኦት መስጠታቸውን የክልሉ የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ዘግቧል።

ወቅታዊ ጉዳይ አስመልክቶ ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት መግለጫ “ህወሓት በተለያዩ ግንባሮች ያለ የሌለ ኃይሉን ተጠቅሞ የማጥቃት ሙከራ እያደረገ ነው” ብለዋል። ከዚህ ቀደምም ሕዝቡ ከጎናቸው እንዲሆን ባስተላለፉት መልዕክት የክልሉ ባለሃብቶችና የንግድ ማኅበረሰቡን ጨምሮ በርካቶች ምላሹ በጎ መሆኑን አውስተዋል። የተለያዩ ክልሎች እያደረጉት ያለውንም ድጋፍ ታሪካዊ መሆኑንም በዚሁ ዕለት ጠቅሰዋል።

የትግራይ ኃይሎች የኮረም እና አላማጣ ከተሞች መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የተለያዩ የአገሪቱ ክልልሎች ወደ አካባቢው ሠራዊት አንቀሳቅሰዋል። የትግራይ ኃይሎች በጦርነቱ ወቅት ወደተያዙ ግዛቶች የገፉ ሲሆን ደቡባዊ ትግራይ የሚሉትን ኮረምና አላማጣን መቆጣጠራቸውንም አሳውቀዋል። የትግራይ ኃይሎች ምዕራብና ደቡብ ትግራይ ናቸው የሚሏቸውን ግዛቶች በአማራ ክልል በኩል ቀደም ሲል የተወሰዱብኝ አካባቢዎች ናቸው በማለት ግዛቶቹ ይገቡኛል ይላል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት ሌፍተናንት ጄነራል ባጫ ደበሌ ሕዝቡ ለሠራዊቱ እና ለመንግሥት ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ማቀረባቸውን ተከትሎ ነው የተለያዩ ክልሎች ኃይላቸውን ወደ ጦር ግንባር እየላኩ የሚገኙት። የክልሉ ተመላሽ የሠራዊት አባላትና የጦር መኮንንኖች ሰራዊቱን ተቀላቅለው እየተዋጉ እንደሚገኙ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ከዚያኛው ወገን ከተሰለፈው አኳያ “ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግ ነው” ብለዋል።

ሁሉም የክተት ጥሪውን ተቀብሎ ለፀረ-ህወሓት ዘመቻ መዘጋጀት እንዳለበትም ጥሪያቸውን አቅርበዋል። “የክተት ጥሪው አማራንና ኢትዮጵያን የመታደግ ጥሪ ነው” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። አሁን ባለው ጦርነት የመከላከያ ሠራዊትና የክልሉ ልዩ ኃይሎች በጥምረት በመሆን በተለያዩ ግንባሮች እያሸነፉ መሆናቸውን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ ሁሉም የጦርነት መረጃዎች ስለማይነገሩ ሕዝቡ በትዕግሥት እንዲጠብቅ አሳስበዋል።

በራያና በጠለምት ግንባሮችም “ጠላት” ብለው የጠሩት የህወሓት ኃይል ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት እንደሆነም አመልክተዋል። አቶ አገኘሁ ማኅበረሰቡ መረጃ እንደሚፈልገው ጠቁመው መረጃዎች በፌደራልና በክልል መንግሥታት በኩል ይተላለፋሉ ብለዋል። “የአማራን መሬት ለወያኔ እሾህ እናደርገዋለን፣ በየትኛውም አቅጣጫ ሊንቀሳቀስ እይችልም፣ ሁሉም በየደረጃው መደራጀት አለበት፣ ወደ ግንባርም መሄድ አለበት “ብለዋል።

የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሰሞኑ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት የትግራይ ኃይሎች እያሸነፉ እንደሆነ ገልፀው “በቆቦ እና በአዲ አርቃይና ጨው በር የነበሩት የመጨረሻዎቹ ጠንካራ ምሽጎች ተሰብረዋል” ብለዋል። የክተት ጥሪውን ያቀረቡት ርዕሰ መስተዳድሩ “ሰርጎ ገብነት” ላይ ሕዝቡ መጠንቀቅ አለበት በማለት አሳስበዋል።

“በክልላችን የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በሰላም እንዲኖሩ እንፈቅዳለን፣ ለጠላት የሚያብሩ ካሉ ግን ሕጋዊ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል። የትግራይ ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው ባሉበት መልዕክታቸው የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ወደ ጦርነት ከማሰለፍ መታቀብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

“የትግራይ ሕዝብ ወንድማችን ነው፣ ትግሬ የሆነ ሁሉ ጠላታችን አይደለም፣ በህወሓት ፕሮፓጋንዳ ተሳስቶ ከሕፃን እስከ ሽማግሌ እየተዋጋ ነው፣የመከላከያ ኃይላችንን ወግቷል አሁንም እየወጋ ነው። ሆኖም አሁንም መላው የትግራይን ሕዝብ አይወክልም ነው የምንለው። ነገር ግን የትግራይ እናቶች ልጆቻቸውን ወደጦርነት ከማሰለፍ መታቀብ አለባቸው፣ የትግራይ ሕዝብ ታሪካዊ ስህተት እየፈፀመ ነው፣ ህወሓትን በቃህ ማለት አለበት” ብለዋል።

ህወሓት በበኩሉ ከሰሞኑ የትግራይ ህዝብ ለትግል እንዲነሳሳ ባወጣው መግለጫ የምዕራባዊ ዞንና አንዳንድ የደቡባዊ ትግራይ አካባቢዎች “ነፃ ባለመውጣቱ ሕዝቡ በርካታ ዘግናኝ ግፎችና በደሎች እየደረሱበት ነው” ብሏል። “ነፃ ባልወጡት የትግራይ ቦታዎች የሚኖረውን ሕዝባችን ጨምሮ በአጠቃላይ የትግራይ ሕዝብ እንደሕዝብ በጥይት፣ በረሃብ በፆታዊ ጥቃትና ሃብትና ንብረቱን በማውደም ከምድረ ገፅ ለማጥፋት ቀርፀው ተግባራዊ ያደረጉትን እኩይ ፓኬጅ አሁንም አጠናክረው ቀጥለውበታል” ብሏል።

ከስምንት ወራት በፊት በትግራይ የተከሰተው ጦርነት ወደ አፋርና አማራ ክልሎች የተዛመተ ሲሆን 2 ሚሊዮን የሚሆን ነዋሪ ከክልሉ የተፈናቀለ ሲሆን 400 ሺህ የሚሆኑ ደግሞ ለረሃብ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግሥታት መግለጹ ይታወሳል። በአፋር ክልልም ከሰሞኑ በተነሳው ግጭት ከ70 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት የጦርነት ክተት ጥሪ በየቦታው በሚቀርብበት በዚህ ወቅት ግጭቱ ወደ አዲስ እና ይበልጥ ደም አፋሳሽ ወደ ሆነ ምዕራፍ ሊያመራ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል። በአሁኑ ወቅት ያለውን የውጊያ መፋፋምም አስመልክቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ለአላስፈላጊ ስቃይ እና ሞት የሚዳርግ ነው በማለት ያላቸውን ስጋት ከሰሞኑ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

አምባሳደሯ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት በድርድር የተመሰረተ የተኩስ አቁም እና ፖለቲካዊ ውይይት ሊስማሙ ይገባል ብለዋል። የፌደራል መንግሥቱና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል። ከጥቂት ሳምንታት በፊት የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ የገለፀ ሲሆን፤ ህወሓት በበኩሉ መቀለንና ሌሎች የትግራይ ግዛቶችን እንደተቆጣጠረ ተናግሯል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በኩል ኢትዮጵያ የተኩስ አቁሙን ለማወጅ የወሰነችበት ሁኔታም መገለፁ የሚታወስ ነው። ከዚህም መካከል አብዛኛዎቹ የህወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ መሪዎች በመገደላቸውና በመታሰራቸው እንዲሁም የቀሩትን ጥቂት የህወሓት አመራሮች ለመያዝ ሲባል ጦርነቱን መቀጠል አስፈላጊ ባለመሆኑ ነው ተብሏል።

በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች የግብርና ወቅታቸውን እንዳይስተጓጎል፣ የረድዔት ድርጅቶች የበርካቶችን ህይወት እንዲያድኑ እድል ለመስጠት እንዲሁም የግጭቱ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የትግራይ ሕዝብ ሰላም የሚያስፈልገው በመሆኑ እና ለችግሩ ሰላማዊ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ከጠቀሷቸው ምክንያቶች ናቸው።

ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።

ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *