መንግሥታዊው የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የህወሓት አማጺያን መሠረተ ልማቶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋሉ በመሆኑ በትግራይ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ነው አለ።
ኤጀንሲው ትናንት ሐምሌ 15 ባወጣው መግለጫ በማይ-ጸምሪ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበት ሁኔታ አስከፊ ወደ ሆነ ደረጃ እየተሸጋገረ በመሄዱ እጅግ አሳሳቢ ሆኗል ብሏል። አብዛኛውን ትግራይ ተቆጣጠሮ የሚገኘው ህወሓት በበኩሉ በክልሉ ስለሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞችን በመተለከተ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ላይ በትግራይ ያሉ ስደተኞች መፈናቀል እና ተፈጽመዋ የተባሉ ጥቃቶች እጅጉን አሳስቦኛል ብሏል።
ህወሓት በተባባሩት መንግሥታት የሚመራ ገለልተኛ አካል በሲቪል ሰዎች እና በስደተኞቹ ላይ ተፈጽመዋል የተባሉ በደሎችን እንዲያጣራ ጠይቋል። ከስምንት ወራት በፊት በፌደራሉ መንግሥት እና በህወሓት መካከል ግጭት ከመከሰቱ በፊት በትግራይ ከ100ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።
የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ በበኩሉ የህወሓት አማጺያን የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ወዳሉባቸው አካባቢዎች መግባታቸውን ገልጾ፤ እስካሁን ድረስ ቢያንስ ስድስት ስደተኞች እንደተገደሉ የሚያሳዩ መረጃዎች ተገኝተዋል ሲል ገልጿል።
“ለሰብአዊ አገልግሎት እንዲውሉ የተዘጋጁና የተቋቋሙ ጤና ጣቢያዎችን ጨምሮ አምቡላንሶችን እና መሠረተ ልማቶችን ለወታደራዊ አገልግሎት እያዋሉ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ” ያለው ኤጀንሲው፤ በጤና አገልግሎት እጥረት ሕይወታቸው ያለፈ ስደተኞች ስለመኖራቸውም አስታውቋል።
ህወሓት ግን በመግለጫው የትግራይ ሕዝብ እና መንግሥት ለዓመታት በሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ስደተኞችን ተቀብሎ ሲያኖር መቆየቱን ገልጾ፤ በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት “በወራሪ ኃይሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ስደተኞችን ለመደገፍ ቁርጠኛ ነን” ብሏል።
ኤጀንሲው በስደተኞች ላይ ያጋጠመውን ችግር ለመቅረፍ በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ መጠለያ ጣቢያ እየተቋቋመ እንደሆነ እና ከግጭቱ ቀጠና ለወጡ ስደተኞች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን እና አገልግሎቶችን በማደራጀት ላይ እገኛለሁ ብሏል።
ስደተኞችን ለመቀበል በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች ማስጠለል እና ትኩስ ምግብ ማቅረብ ጀምረናል ብሏል የስደተኞች እና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ በመግለጫው። ኤጀንሲው ጨምሮም በትግራይ የሚገኙ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና የኤጀንሲው ንብረቶች እንደተዘረፉ መረጃዎች ደርሰውኛል ያለ ሲሆን፤ ስደተኞች ከግጭት ቀጠና ለመውጣት የሚያደርጉት ጥረት “በህወሓት ክልከላ እንደሚደረግበት እና ለጦርነቱ የሚውል በዓይነትና በገንዘብ መዋጮ እንዲከፍሉ እየተገደዱ ይገኛሉ” ብሏል።
ኤጀንሲው እስካሁን ድረስ ማይ-ጸምሪ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች መግባትም ሆነ ለስደተኞች አገልግሎት መስጠት እንዳልተቻለ ገልጾ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተፈፀሙ በጭካኔ የተሞሉ ወንጀሎችን በማያሻማ ሁኔታ እንዲያወግዝ ጥሪ አቅርቧል።
ስደተኞችን ወደ ሌላ መጠለያ ጣቢያ ማሸጋገርን በተመለከተ ህወሓት ከትናት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ የኤርትራ ስደተኞችን ወደ ሌላ የማሸጋገሩ እቅድ በስደተኞቹን ፍቃድ እና ፍላጎት መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ብሏል።
በትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ካምፖች ይገኙ በነበሩ ኤርትራውያን ስተደተኞች ላይ ጥቃቶችና ሌሎችም በደሎች መፈጸማቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ሲወጡ ቆይተዋል።
ግጭቱን ተከትሎ በርካቶች ከስደተኞች መጠለያ ካምፖች በመውጣት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቱን ሸሽተው መሄዳቸው የተገለጸ ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸውም እንዳሉ ይነገራል። የፌደራል መንግሥቱ የህወሓት ኃይሎች ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝን ማጥቃታቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት መቀስቀሱ ይታወሳል።
ከስምት ወራት ቆይታ በኋላ የፌደራል መንግሥት የክረምቱን የእርሻ ጊዜ ምክንያት በማድረግ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ከትግራይ ክልል ማስወጣቱን አሳውቋል። የህወሓት ኃይሎች በበኩላቸው የተኩስ አቁም ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርበው በአማራ እና በትግራይ ድንበሮች አካባቢ ወታደራዊ ግጭቶች አጋጥሟል።
ምንጭ – ቢቢሲ