የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) ጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች እንዲሁም ግለሰቦች ለእስራት እንደሚዳረጉና ታሳሪዎቹ የት እንዳሉ ለማወቅ ባለመቻሉ የሰብዓዊ መብት አያያዛቸውን መከታተል እንዳልቻለ አስታወቀ።

“እስራት የተፈጸመባቸው ሰዎች ቤተሰቦች ታሳሪዎቹ የት እንዳሉ ለማወቅ እና ለመጠየቅ እንዳልቻሉ መረጃ አግኝተናል” ያለው ኢሰመጉ፤ ጉዳዮን በተመለከተ መንግሥት የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስድ ከዚህ ቀደም ማሳሰቡን ጠቁሟል። ኢሰመጉ ስለ እስረኞች ሁኔታ ስጋቱን ያስታወቀው አስቸኳይ መፍትሔ ያሻቸዋል ያላቸውን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚደርሱ የመብት ጥሰቶች ዝርዝር ዛሬ ሐምሌ 15/2013 ዓ. ም. ይፋ ባደረገበት መግለጫው ነው።

በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሰዎች ያሉበት ቦታ አለመታወቁ ኢሰመጉ የታሳሪዎቹን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ እንዳይከታተል እንቅፋት እንደሆነበትም አስታውቋል። የእነዚህ ሰዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ መገምገም አለመቻሉን ጠቅሶ “የመብታቸው አጠባበቅ ሁኔታ ኢሰመጉን እጅግ ያሳስበዋል” ብሏል። በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ከመያዛቸው በፊት እንዲሁም ከተያዙ በኋላም በሕገ መንግሥት የተደነገገ መብታቸው እንዲከበር አሳስቧል።

አያይዞም እስራትን ጨምሮ ሌሎችም በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች በበቂ ምክንያት የተደገፉ፣ ሕጋዊ ሂደትን የሚያከብሩና ሰብዓዊ መብትን የማይጥሱ እንዲሆኑ መንግሥትን ጠይቋል። በተለያየ ጊዜ በቁጥጥር ሥር የዋሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎችም ግለሰቦች የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ሲገለጽ ነበር። ይህንን በመቃወም ጠበቆቻቸው፣ የመብት ተሟጋቾችና ቤተሰቦቻቸው ቅሬታ ሲያሰሙ ቀይተዋል።

በቅርቡ 14 የኢትዮ-ፎረም እና የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ሳምንታት ቢያልፍ እስካሁን ፍርድ ቤት ስላለመቅረባቸው መዘገቡ አይዘነጋም። ከእስረኞች የሰብዓዊ መብት ጥበቃ በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ስለሚቀሰቀሱ ብሔርን ያማከሉ ግጭቶች እና የነዋሪዎች መፈናቀልም ኢሰመጉ ስጋቱን ገልጿል።

ጥቃት እና መፈናቀል

በኦሮሚያ ክልል፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርቴ ወረዳ ውስጥ የአማራ ብሔር ተወላጆች በሸኔ ታጣቂዎች “በአካባቢው መኖር አትችሉም” ተብለው በወረዳው ከሚገኙ አምስት ቀበሌዎች ማለትም ሆሮሎጎ፣ ጃንጂማረ፣ ሆሮዳዴ፣ አብዲ ዲንጊ እና አሣ ጉዲና መፈናቀላቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቁሟል። በተቀሩት ስድስት የሚሆኑ የወረዳው ቀበሌዎች ያሉ ነዋሪዎችም አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ማዋከብና ጫና እየደረሰባቸው እንደሚገኝ መረጃ እንደደረሰው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታውቋል።

“ሰንቦ-ጨፌ ቀበሌ ውስጥ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በርካቶች በሸኔ ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን የተቀሩትም በሻምቡ በኩል አድርገው ወደተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ለመሄድ ሲሞክሩ ተከልክለው ችግር ላይ እንደሚገኙ የሚጠቁሙ መረጃዎች ለኢሰመጉ ቀርበዋል” ይላል መግለጫው።

ሐምሌ 11/2013 ዓ. ም. በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ ማቆያ ቤት የነበሩ ከ250 እስከ 300 የሚደርሱ ታራሚዎች ወጥተው፣ ከመሣሪያ ግምጃ ቤት ጥይት በመዝረፍ “በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ሲተኩሱ ማደራቸውን” ኢሰመጉ በመግለጫው ጠቅሷል። ጨምሮም ወደ 30 ሺህ የሚደርሱ ነዋሪዎች ከአካባቢው መውጣት አትችሉም ተብለው በከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሷል።

“ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር ታስረው ለበሽታ የተዳረጉ አሉ”

በሌላ በኩል ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በርካታ ሰዎች “ሸኔን ተባብራችኋል፣ ልጆቻችሁ ሸኔን ተቀላቅለዋል” እየተባሉ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በተጨናነቀ ክፍል ውስጥ እንደሚታሰሩና ለህመም እየተዳረጉ እንደሚገኙ ኢሰመጉ ገልጿል። “ከሕፃናት ልጆቻቸው ጋር ታስረው ለበሽታ የተዳረጉና ሕክምና ለማግኘት የተቸገሩ ሴቶች አሉ። ከታሰሩበት ቦታ ተወስደው የት እንዳሉ የማይታወቅ ሰዎች አሉ” ሲልም መግለጫው አክሏል።

በመንግሥት የጸጥታ አካላት እንዲሁም በሕገ ወጥ ታጣቂዎችም ግድያ እና መሰወር እየተፈጸመ ነው ብሏል ኢሰመኮ። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን እና ድባጤ ወረዳ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንዳለና በሕገ ወጥ ታጣቂዎች ጥቃት እንደሚሰነዘር ጠቅሷል። በሌላ በኩል በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ወረታ ከተማ፣ ፎገራ ወረዳ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በአካባቢው ሰዎች ተደብድበው መገደላቸውን ገልጿል።

በተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ውጥረት አስመልክቶም በጸጥታ ችግር ምክንያት የሰዎች በሕይወት የመኖር፣ የመንቀሳቀስ እንዲሁም ንብረት የማፍራት መብት እንዳይጣስ መንግሥት ተገቢውን እርምጃ እንዲወስድ ኢሰመኮ አሳስቧል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *