የአፋር ክልል ከትግራይና ከአማራ ክልሎች ጋር በሚዋሰንበት አካባቢ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ከሰባ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።

ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት ከቅዳሜ ጀምሮ ሐምሌ 10/2013 ዓ.ም ክልሉ ዞን አራት፣ ፋንቲረሱ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ግጭት በመፈጠሩ መሆኑን የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለቢቢሲ ገልጸዋል። “ይህ አካባቢ ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ጋር የሚዋሰን አካባቢ ነው። የትግራይ ታጣቂ ኃይሎች ያንን ጥሰው ገብተው በአካባቢው ከነበረው ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት” ብለዋል።

ቢቢሲ እስካናገራቸው እሰከ ትላንት ምሽት ድረስ በነበራቸው መረጃ መሠረት ከጎሊና፣ አውራ እንዲሁም ኡወና ቴሩ ከሚባሉ ወረዳዎች ከሰባ ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን መረጃ እንደደረሳቸው ጠቁመዋል። ግጭቱ እየተስፋፋ ከሄደ የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል የሚሉ ስጋቶች መኖራቸውን ጠቅሰው “በአጠቃላይ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ስጋት ውስጥ እንዳለ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና ለእርዳታ ድርጅቶች መልዕክት አስተላልፈናል” ብለዋል አቶ መሐመድ።

አሁንም “በየጫካው በየጢሻው ተደብቀው ተበትነው የሚገኙ በበርካታ ማኅበረሰብ አባላት እንዳሉ” ማወቅ መቻሉን አስታውቀዋል። ወደ ጭፍራ እና ሰመራ ሎጊያ ከተሞች በማምራት ዘመዶቻቸው ጋር የተጠለሉ ሰዎች መኖራቸውም ገልጸዋል። እንደ ኃላፊው ጎሊና አካባቢ ጋድኮማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እስካሁን ከ10ሺህ በላይ ሰዎች በትህምርት ቤቶች እና በጤና ተቋማት ውስጥ እንደተሰባሰቡ መረጃዎችን ጠቅሰው ተናግረዋል።

“አብዛኛው ማኅበረሰብ ችግሩ ሲፈጠር በድንጋጤ በየጫካው በየበረሃው ተበትኖ ይገኛል። በአንዳንድ አካባቢዎች የስልክ ግንኙነት የለም በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ በጸጥታ ስጋት ተደራሽ መሆን አልተቻለም” ብለዋል። ክልሉ እስካሁን ባለው አቅም ለአንድ ሺህ ሰው የሚሆን ምግብ አልባሳት እና የህጻናት ምግብ እንዳጓጓዙና ኃላፊው ሌሎችም ድጋፎች እየተጓጓዙ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌሎችም ለጋሽ ድርጅቶች እንዲረዱም እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቁመው ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረባቸውን እና አስቸኳይ ምላሽ እንደሚጠብቁ ገልጸዋል። በአፋር ክልል ለባለፉት አራት ቀናት ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ሪፖርቶች እየወጡ ነው። ከቀናት በፊት የፌደራሉ መንግሥት እና የአፋር ክልል መንግሥት ባወጡት መግለጫ የህወሓት ኃይሎች ተኩስ ከፍተዋል ብለዋል።

መንግሥት በአፋር በኩል ወደ ትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ ሲጓጓዝ የህወሓት ቡድን አካባቢውን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ መንገድ ዘግቷል ሲል የአፋር ክልል መንግሥት ደግሞ የህወሓት ቡድን በያሎ ተብሎ በሚጠራው ወረዳ በኩል ተኩስ መክፈታቸውን ገልጿል። የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በአፋር ክልል በኩል በነበሩ ለፌደራሉ መንግሥት በወገኑ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ ወስደናል ሲሉ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረው ነበር።

ጌታቸው ረዳ “የተገደበ” ያሉት ወታደራዊ እርምጃ በአፋር በኩል ተሰልፎ በነበረው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ላይ ያነጣጠረ እንደነበረ መናገራቸው የሚታወስ ነው።በትግራይ ኃይሎችና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተነሳው ጦርነት ስምንት ወር ያለፈው ሲሆን ወደ አጎራባች ክልሎችም እየተዛመተ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች በዚህ ግጭት በርካታ ንፁሃን መገደላቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የህወሓት ቃለ አቀባይ በበኩላቸው ንፁሃንን ኢላማ አላደረግንም ብለዋል። መንግሥት የአፋር ልዩ ኃይልና የመከላከያ ሠራዊት አማካኝነት ምላሽ ለህወሓት እንደተሰጠ አስታውቋል። ከአካባቢው የሚወጡ ሪፖርቶችን በገለልተኛ አካል ማጣራት አስቸጋሪ ነው።

ከሰሞኑ ወደ ትግራይ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ በነበሩ አስር ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃት መድረሱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለፁን ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የተራቡ የክልሉ ነዋሪዎችን ለመርዳት የበለጠ አዳጋች ሁኔታን እንደፈጠረም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመልክቷል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *