በዚህ ክፍል ጋዜጠኞች የግጭት ዘገባ በሚሠሩበት ጊዜ ግምት ውስጥ ማስገባት የሚያስፈልጋቸውን በርካታ ስልቶች እንመለከታለን። እነዚህ ሁሉ በዋነኝነት ለአንባቢዎች እና ለተመልካቾች በጣም ሊጠቅሙ የሚችሉ ታሪኮችን ለመሥራት የታሰቡ ቢሆንም፣ ለግጭት ቁጥጥር እና አፈታት አስተዋፅዖ የማድረግ አቅምም አላቸው።

6.1. ሰላም ጣሪዎችን ታሪክ መንገር

በሰላም ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ማንነትና ሥራ የግጭት ዘገባ ላይ ማካተት የሰላም ሐደቱን እና ከነውጥ ውጪ ያሉ አማራጮችን በተመለከተ የሰዎችን ግንዛቤ ለማሳደግ በጣም ጠቃሚ መንገድ ነው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ዘገባዎች በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ዕውቅና ያላቸው ሰዎች ታሪክ ላይ የሚያጠነጥኑ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ነገር ግን በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ውስጥ ለውጥ እያመጡ ስላሉ የተራ ሰዎች ታሪክ መንገርም ቀልብን የሚገዛ ነገር ሊሆን ይችላል። በአካባቢ ደረጃ ባሉ ቡድኖች መካከል ድልድይ የሚገነቡ ሰዎችን፣ ነውጥ በሚፈጠርበት ጊዜ ጣልቃ የሚገቡ የሰላም ኮሚቴ መሪዎች፣ ከተለያዩ ቡድኖች የሚመጡ ሕፃናት መዋያዎችን ወይም የሰላም መናፈሻዎችን የሚያቋቁሙ ሰዎችን ታሪክ ያካትታሉ። እንደነዚህ ያሉ ታሪኮች ጭፍን አመለካከቶችን እና እርስ በርስ ያላቸውን የጠላትነት ዕሳቤ በመፈተን ረገድ ወሳኝ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ።

በሰላም ግንባታ ውስጥ የተሳተፉ ሰዎችን ተግባር የመዘገብ ጥቅምን መገንዘብ ተገቢ ቢሆንም ግጭት አገናዛቢ ዘገባ ውስጥ ይህንን እንደ ብቸኛ አማራጭ ስልት አድርገው መቁጠር እንደሌለባቸው ክሪስ ቺናካ ያስጠነቅቃሉ። ክሪስ የሰዎቹ ታሪክ ብዙውን ጊዜ ለመሥራት በጣም ቀላል ቢሆኑም የግጭቱን ዝርዝር ዘገባ ግን መሸፈን የለባቸውም ብለው ያምናሉ። ትረካዎቹ ሰዎች እንዴት ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ምሳሌዎች መሆን አለባቸው እንጂ ጋዜጠኞች “የግለሰቦች ስብእና ከግጭቱ ምንነት በላይ ገኖ እንዲወጣ ወይም እንዲሸፍን” መፍቀድ የለባቸውም።

ልዩነት እያመጡ ያሉ ተቋሞችን ተግባርም ማሳየት ጠቃሚ ነው። የወጣት ማኅበራት፣ የስፖርት ክለቦች፣ የሴቶች የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ሌሎች በርካታ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ማኅበረሰብ ዐቀፍ ተቋማት በግጭት ወቅት እና በኋላ ሕዝቦችን በማቀራረብ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

6.2 የመፍትሔ ፍለጋዉን ማስፋፋት

ምንም እንኳን ግጭቶችን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው በግጭት ለሚሳተፉ ወገኖች መንገር የጋዜጠኛ ተግባር ባይሆንም፣ አስበዋቸው የማያውቁትን የመፍትሔ አማራጮች እንዲለዩ በመርዳት ረገድ ሚና ልንጫወት እንችላለን። እንደተመልካችነትታችን እና በግጭት ውስጥ ካሉ ሁሉም አካላት ጋር ባለን ግንኙነት ግጭትን ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚመለከቱ ወገኖች ሳይረዱት ቀርተው ወይም ሳያውቁ ሊሆን እንደሚችል እንረዳለን።

ስሜታችን በዘገባችን ላይ ተፅዕኖ እንዲያሳድር ሳንፈቅድ አማራጭ መፍትሔዎችን እንዴት እናቀርባለን? ለዚህ ጥያቄ ሁለት ምላሾች አሉት።

  • እያንዳንዱ ጋዜጣ እና ሬዲዮ ጣቢያ ሰዎች አስተያየታቸውን የሚሰጡበት ሰዓት አለው። ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን አማራጭ መፍትሔዎችን በተመለከተ ግንዛቤ ለመስጠት እንችላለን። ሰዓቱ የግል አስተያየት የሚተላለፍበት መሆኑን ተደራሾቻችን እንደሚያውቁ እርግጠኛ መሆን አለብን። የእውነት የተከሰተን ጉዳይ እና አስተያየቶችን ስናቀርብ መለየት መቻል አለብን።
  • “እንዲህ ቢሆንስ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረብ እንችላለን። በተደራሾቻች ፋንታ ጥያቄዎችን ማቅረብ የጋዜጠኞች ሚና መሆኑን አይተናል፤ “እንዲህ ቢሆንስ?” ብለን በመጠየቅ ይህንን ሚና ማሳካት እንችላለን። አንድ ጋዜጠኛ በግጭቱ ውስጥ ላለ አንድ ቡድን አማራጭ መፍትሔ ቢያቀርብ እና አስተያየት እንዲሰጡበት ቢያደርግ ምንም ስህተት የለውም። ይህንን ዘዴ በመጠቀም ተደራሾቻችንን የሚስቡ ጥያቄዎችን ማቅረብ ብቻ ሳይሆን ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ስለ ሰላማዊ መፍትሔዎች እንዲያስቡ ማበረታታትም እንችላለን። ምንም እንኳን ለቡድኖች የምናቀርባቸው መላምታዊ መፍትሔዎች ተሥማሚ ባይሆኑም ግጭቱን ለመፍታት አማራጭ መንገዶችን እንዲያስቡ ያበረታቷቸዋል።

መፍትሔ ያገኙ ግጭቶችን ያለፈ ታሪክ እንደምሳሌ በማምጣት ከመፍትሔው እና ከተከተሏቸው ሒደቶች በአዲሱ ዐውድ ውስጥ ተፈፃሚ መሆን የሚችለው የቱ እንደሆነ መመርመር ጠቃሚ እንደሚሆን ባርባራ አሞንግ ያስገነዝባሉ። ይህ በሚደረግበት ወቅት ቡድኖች ግጭቱን ለመቆጣጠር እና ለመፍታት በነበረው ሒደት የሚሠራ እና የማይሠራ የነበረውን ለመረዳት በእነዚህ ሒደቶች ውስጥ የተሳተፉ ሰዎችን ቃለ መጠይቅ ማድረጉ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሰዎች አሁን ባለው ችግር ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ሰዎችን ምን ዓይነት እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ምክራቸውን እንዲሰጡ ሊጠየቁ ይችላሉ። ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ምክሮቹን እንዲቀበሉ የሚያስገድዳቸው ነገር የለም። ነገር ግን የተለያዩ አማራጮችን ማቅረቡ ቡድኖች ያላቸውን አማራጮች ሊያሳድግ ይችላል።

እንዲሁም የነውጠኛ መሪዎች ደጋፊዎች እንዲያስቡበት እና በቡድናቸው ውስጥ ያሉ አባላት ነውጥ እንዳይጠቀሙ ለማግባባት የሚጠቅሙ የመከራከሪያ ነጥቦችን ያሳውቃቸዋል። ነውጥ የምርጫ ጉዳይ መሆኑን እና ሰዎች ፈቃደኛ ከሆኑ ሁል ጊዜም ሰላማዊ አማራጮች እንዳሉ ማሳየት ጠቃሚ ነው።

6.3 አቃላይ አጠራሮችን ስወገድ

በግጭት ዙሪያ ዘገባ የሚሠሩ ጋዜጠኞች ሁል ጊዜ ከሁለት መሠረታዊ ጥያቄዎች ጋር መጋፈጥ አለባቸው። እነሱም፦ በአብዛኛዎቹ ግጭቶች ውስጥ የሚፈጠረውን ውስብስብነት ተደራሾቻችን በሚረዱበት መንገድ እንዴት እንገልጸዋለን? የሚለው እና በተመደበልን ውስን ጊዜ ወይም ቦታ መረጃዎቹን በሙሉ እንዴት ጨምቀን ማቅረብ እንችላለን? የሚለው ናቸው። ችግር የሚገጥመን ስለ ግጭቱ ጥቂት መረጃ ላላቸው ተደራሾች ለማብራራት ስንሞክር ብዙ ጊዜ ታሪኩን በጣም አቃለን ልንገልጽ ስለምንችል ነው። ይህ ማለት ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖችን አመለካከቶች እና ግጭቱ እየተፈፀመበት ያለውን ዐውድ መገለጫዎች በተመለከተ በቀላሉ መናገር ማለት ነው። ይህን ለማድረግ ከሚረዱ ዘዴዎች አንዱ ለግጭቶች መጠሪያ ማውጣት ነው። ጋዜጠኞች በተለያዩ ዓይነት ግጭቶች ውስጥ በግጭቱ ማን እንደሚሳተፍ ወይም ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት የሚጣሉበት ጉዳይ ላይ በመመርኮዝ ቀለል ያሉ ሥያሜዎችን መጠቀማቸው የተለመደ ነው።

ይህ ዓይነቱ አቀራረብ ጋዜጠኞች የመጨረሻውን እውነታ ብቻ የሚያንፀባርቅ ገለጻዎችን በአቋራጭ እንዲያገኙ ይገፋፋቸዋል። በሚያሳዝን ሁኔታ ጋዜጠኞች ግጭቶችን በፍጥነት ለማብራራት ቀላል ሥያሜዎችን መጠቀማቸው የተዛባ እና ሁኔታውን ያላገናዘበ የግጭት ታሪኮች ያቀርባሉ ማለት ነው። እነዚህ አቃላይ አጠራሮች ብዙውን ጊዜ የሚያተኩሩት በግጭቱ አንድ ገጽታ ላይ ብቻ ሲሆን አብዛኛዎቹ ግጭቶች በተለያዩ ሁኔታዎች እና ተለዋዋጭነት የተገኙ ውጤቶች መሆናቸውንም ችላ ይላሉ። እንደዚህ ዓይነት አቃላይ አጠራር ምሳሌዎች የሚከተሉትን ያካትታል ‘ጥቁር በጥቁር ነውጥ’ የሚለው በአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል፣ ‘ሁቱ-ቱትሲ’ የሚለው የሩዋንዳን ግጭት ለመግለጽ ውሏል፣ ‘ክርስቲያን-ሙስሊም’ የሚለው በኢንዶኔዥያም እንዲሁ።

‘የክርስቲያን-ሙስሊም ግጭት’ ወይም ‘የሃይማኖት ጦርነት’ የሚሉ አቃላይ መጥሪያዎች መጠቀም በእምነቶች መካከል የሚኖር ግጭት የማይቀር መሆኑን እንዲታሰብ ያደርጋል። እንደዚህ ያሉ አጠራሮች የቡድኖቹ ልዩነት ለግጭት በቂ ምክንያት እንደሆነ በማስመሰል በዓለም ዙሪያ የተለያየ እምነት እና የተለያየ ጎሳ ሰዎች ወደ ግጭት ሳይገቡ አጠገብ ለአጠገብ የመኖራቸውን እውነት ይጋጫል።

ለክሪስ ቺናካ መፍትሔው አጠራሮቹን መጠቀም ሳይሆን፥ ምን እየሆነ እንዳለ ለመግለጽ ትልቅ ጥረት ማድረግ ነው። ጊዜ ሊወስድ ይችላል ነገር ግን ተደራሾቻችን የተገናዘበ ውሳኔ እንዲያሳልፉ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ያደርጋል። ሌሎች የዝግጅት ክፍሉ አባላት ከአጠራር ጋር የተያያዘው ችግር ግጭቶች አጠራር ላይ ብቻ አያቆምም። በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎችንም ይነካል።

ባርባራ አሞንግ በሰሜን ኡጋንዳ ለሎርድ ሬዚስታንስ ሠራዊት ይዋጉ የነበሩትን ወጣቶችን ጉዳይ በማንሳት ጉዳዩ እንዴት ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ፦

እነዚህ ሰዎች በጦርነት ላይ ሲገደሉ እንደ አማፂያን ወታደሮች ተደርገው ተገልጸዋል፤ ነገር ግን ወደ አገራቸው ሲመለሱ እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲቀላቀሉ የተጠለፉ ልጆች ተብለው ይጠራሉ። እነዚህ የአኮሊ ሕዝቦች ከእነዚህ ተቃርኖዎች ጋር አብረው ለመኖር ተገድደዋል። በአንድ በኩል የሚያሰቃዩን እና በድህነት እንድንኖር የሚያስገድዱን ሰዎች ናቸው፤ በሌላ በኩል ከእኛ የተወሰዱት ልጆቻችን ናቸው።

ባርባራ እንደሚሉት ለዚህ ችግር ብቸኛው መፍትሔ ወጣቶቹን “አብዛኛዎቹ በጠለፋ የተወሰዱ ሕፃናት የሆኑ የሎርድ ሬዚስታንስ ሠራዊት” ብሎ መግለጽ ነው። ይህ እነርሱን ባጭሩ አማፂያን ብሎ ከመጥራት የበለጠ ብዙ ቦታ እንደሚወስድ ታምናለች። ነገር ግን ተደራሾችን ማሰብ ወሳኝ መሆኑን አፅንዖት ይሰጡበታል። የሎርድ ሬዚስታንስ ሠራዊት በአብዛኛው የተዋቀረው በተጠለፉ ሕፃናት መሆኑን ሰዎች መርሳት የለባቸውም። ባርባራ ልክ እንደ ክሪስ ሁሉ ከአማፂያን ውጪ ያለው የመጠሪያ አማራጭ የሰዎችን ድርጊት መግለጫ በመስጠት አንባቢው እና አድማጩ በራሱ እንዲወስን የሚፈቅድ ነው በሚለው ይስማማሉ። ባርባራ ሲያስረዱም፦

የግለሰቡን ድርጊት በመግለጽ አንድን ሰው አምባገነን ወይም ፅንፈኛ ብሎ ከመጥራት ይልቅ የበለጠ ጥልቅ ታሪክ እንናገራለን። የግለሰቡን መግለጫ የሚያረጋግጥ ግለሰቡ ያደረገውን ነገር ለሰዎች ማሳየት አለብን።

ኪዮኮ ኪቫንዲ ደግሞ ሕገ ወጥ ተብለው የተሰየሙ የሰዎች ስብስብን ምሳሌ ይጠቅሳል። በዚህ ጊዜ አንድን ቡድን በዚያ በተወሰነ ሁኔታ ውስጥ ሕገ ወጥ ብሎ መጥራት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽ መደረግ አለበት። በመንግሥት ታግደው እና ሕገ ወጥ ተብለው ተፈርጀዋል? በምን ምክንያት? ብዙ የነጻነት ንቅናቄዎች ከዚህ በፊት እንደ ሕግ ወጥ ይቆጠሩ ነበር። እንዲሁም የቡድኑን ሁኔታ ሕገ ወጥ ያስባለውን ሁኔታ ማወቅ ያስፈልጋል።

6.4 ቋንቋዎን በጥንቃቄ ረጡ

በዘገባችን የምንጠቀምበት ቋንቋ ተደራሾቻችን ግጭቱን የሚረዱበት መንገድ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። እንዲሁም ሚዲያችንን በሚመለከቱበት መንገድ ላይም ተፅዕኖ አለው። አድማጮች የቋንቋ አጠቃቀማችን ስሜት የሚነካ ወይም የተሳሳተ ነው ብለው ከወሰዱት ተዓማኒነታችን እና በግጭቱ ዙሪያ ገንቢ ሚና እንዳይኖረን ተፅዕኖ ያሳድርብናል። ክሪስ ቺናካ ሐሳባቸውን እንደሚከተለው ያስቀምጡታል፦

… የግጭት ዘገባ ሲሠራ የቋንቋ ጉዳይ ዋና መሠረታዊ ነጥብ ስለሆነ በጣም በጥንቃቄ ልንይዘው ይገባል። የምንጠቀመውን ቋንቋ በተቻለን አቅም በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በዜና ክፍል ውስጥ ተከራከሩበት፣ የጥላቻ ቋንቋ መጠቀምን የሚያስወግድ እና ተገቢውን ቋንቋ በመጠቀም ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችን የሚያበረታታ የቋንቋ አጠቃቀም መመሪያ በማውጣት ተለማመዱ።

ሊንሽ እና ማክጎድሪክ (2005) የግጭት ዘገባ በሚሠራበት ወቅት የቃላት አመራረጥን በተመለከተ ለጋዜጠኞች የሚከተሉትን ምክር ይሰጣሉ።:

  • እንደ ‘ተንኮለኛ’ ፣ ‘ግፈኛ’‘ጨካኝ’ እና ‘አረመኔ’ የመሳሰሉ መገለጫዎችን አስወግዱ። ይህ ምንግዜም ጋዜጠኞች ለአንደኛው ወገን እንደወገኑ ያስቆጥራቸዋል። ይልቁንም እርስዎ ያልትን ትክክለኛ መረጃ ያቅርቡና እና ተደራሾቹ በራሳቸው ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ያድርጓቸው።
  • እንደ ‘አሸባሪ’‘ፅንፈኛ’ ወይም ‘አክራሪ’ ያሉ ፍረጃዎችን ያስወግዱ። እነዚህን ቃላት መጠቀም ጋዜጠኞች ለአንድ ቡድን እንደሚያደሉ ያሳያል። እነዚህ ፍረጃዎች ሰዎቹ ምክንያታዊ እንዳልሆኑ እና አመለካከታቸውም የጥቂቶች ብቻ መሆኑን ያመላክታሉ። ይህ በጭራሽ ሁልጊዜ የሚሆን ነገር አይደለም።
  • እንደ ‘የወደመ’፣ ‘ተከላካይ አልባ’ እና ‘ምስኪን’ ያሉ ተጠቂነትን የሚገልጹ ቋንቋዎች ከመጠቀም ይቆጠቡ። ይህ የሰዎችን አቅም ማዳከም ይሆናል። በሰዎች ላይ በተከሰተው ነገር ላይ ብቻ ትኩረት አታድርጉ። ሰዎች እንዴት እየተቋቋሙት እንዳሉ ጭምር ያሳዩ።
  • ጋዜጠኞች ሐሳቦችን የሚገልጹበት መንገድ ሌላው አድሏዊ እንደሆኑና እና አንድ ቡድንን ከሌላኛው እንደሚያበላልጡ የሚያሳይ ነው። ከዚህ በታች ያሉት ምሳሌዎች የአንድ ሰውን ንግግር በምንጠቅስበት ጊዜ እንዴት ልንገልጸው እንደምንችል ያመለክታል። ነገር ግን ሁሉም ስለ ተናጋሪው የተለያየ ነገር ነው የሚያወሩት።
  • አቶ እከሌ… አመነ
  • አቶ እከሌ… ተናዘዘ።
  • አቶ እከሌ… ወቀሰ።
  • ወ/ሮ እከሊት… ወነጀለች።
  • አቶ እከሌ… አጋለጠ።

በሁሉም ሁኔታዎች ማለት ይቻላል “ተነገረ” የሚለው ቃል የንግግርን ተግባርን ለመግለጽ ገለልተኛ እና ፍትሐዊ መንገድ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። እነሱ የተናገሩት እንዴት እንደሆነ ለመግለጽ ለየት ያለ ቋንቋ ከመጠቀም ይልቅ የተናጋሪዎቹ ቃላት በራሳቸው እንዲናገሩ መተው የተሻለ ነው። የበለጠ ዝርዝር ሐሳቡን መስጠት አስፈላጊ ከሆነ ግለሰቡ አመለካከቱን በተነገረበት አኳኋን መግለጹ የተሻለ ይሆናል። ጋዜጠኞች የሰዎቹን ቃላት አጠቃቀም ወይም ቴክኒካዊ ገለጻ ማስወገድ አለባቸው። በተለይም ጋዜጠኞች ከወታደራዊ ኃይል ጋር አብረው በሚያሳልፉበት ጊዜ እንደ “ተያያዥ ኪሳራዎች” ያሉ ሐረጋትን ወታደሮች በውጊያው ወቅት በግርግር ሕይወታቸውን ያጡ ንፁሐን ዜጎች ለመግለጽ የሚጠቀሙበትን ቃል በማስወገድ ረገድ አስፈላጊ ነው። የአንድ ቡድንን ልዩ ቋንቋ መጠቀም እርስዎ ለዛ ቡድን ድጋፍ እንዳልዎት ሊያስመስል ይችላል። ይህም የራስዎን እና የሚዲያ ተቋሙ ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ ሊጥለው ይችላል።

6.5 አስተያየትዎ የሚያስፈልግበት ጊዜ

ጋዜጠኞች በግጭት ዘገባዎች ወቅት የራሳቸውን አስተያየት ማካተታቸው ብዙም ተቀባይነት የለውም። ነገር ግን በተወሰነ መልኩ ተቀባይ የሚሆንበት ሁኔታ አለ። የጋዜጣ ርዕሰ አንቀፅ እና የሬዲዮ ፕሮግራም መግቢያ ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። እንዲሁም ጋዜጠኞች ራሳቸው በሌሎች የጋዜጠኞች ዘገባ ላይ ምንጭ የሚሆኑበት እና ስለታሪኩ ለመናገር ብቸኛው መንገድ ክስተቱን እንዴት እንዳሳለፉ በማጋራት የሚሆንበት አጋጣሚ አለ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የሚዲያ ተቋማት ጋዜጠኞችን ስለ ሥራቸው ጦማር አንዲጽፉ ያበረታታሉ እናም ጋዜጠኞች የግል አመለካከታቸውን እንዲሰጡ የሚያደርግ ተጨማሪ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው። በግጭት ላይ የአስተያየት መጣጥፎችን ለሚያቀርቡ ጋዜጠኞች የሚከተሉት ምክሮች ይጠቅሟቸዋል።

  • ተደራሲዎችዎን ያክብሩ። ፍላጎቶችዎን ወይም የቡድንዎን ፍላጎቶች ለማስተዋወቅ የተሰጥዎትን መድረክ መጠቀሚያ አያድርጉ። በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ የሌሎች ቡድኖችን ስጋቶች ከግምት ውስጥ ማስገባት እና ሰዎች የእያንዳንዳቸውን አቋም እንዲገነዘቡ ለመርዳት መድረኩን መጠቀም አስፈላጊ ነው።
  • የአስተያየት ብዝኀነትን ያሳድጉ። ለግጭት አንድ ዓይነት አካሔድ ወይም መፍትሔ ከማስተዋወቅ ይልቅ ቡድኖቹ ተግባራዊ ሊያደርጓቸው የሚችሉ የተለያዩ አማራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ያሳዩ። አቋምዎን መግለጽ እንደሚያስፈልግዎ በሚሰማዎት ጊዜ አድማጮች ለውይይቱ አስተዋፅዖ እያደረጉ መሆኑን እንዲያውቁ እና ተጨማሪ አስተያየቶችን እንደሚያበረታቱ በሚያሳይ መልኩ ያቅርቡ።
  • ጥናት ያድርጉ። ከበድ ያሉ ዜናዎችን አይሠሩም ማለት ጠንካራ ምርምር የለብዎትም ማለት አይደለም። መረጃውን ከየት እንዳገኙት ያብራሩ። ሰዎች የምናቀርባቸውን ሐሳቦች መቀበል እንደሚገባቸው መገምገም እንደሚችሉ ተዓማኒ እና አስተማማኝ የሆነ መረጃ መስጠት አለብን።
  • ምላሹን ያስቡ። የተደራሾችዎን ብዝኀነት ይገንዘቡ። የሚናገሩት ነገር በተለያዩ ከተለያየ ማኅበረሰብ እና ከተለያየ አካባቢ የመጡ ሰዎች ላይ የሚኖረውን ተፅዕኖ ያስቡበት። ይህ ማለት ራስን ሳንሱር ማድረግ ማለት ሳይሆን ባለማወቅ ሌሎችን ላለማስቆጣት ጥንቃቄ ማድረግ ማለት ነው። በተለይም የተወሰኑ አናሳ ቡድኖችን በተመለከተ። ለማስቆጣት ታስቦ ማስቆጣት አዝናኝ ሊሆን ይችላል። በግጭት ሁኔታ ውስጥ ግን ጠቃሚ ነገር አይደለም። ብዙ አምደኞች እና ቶክ ሾው አቅራቢዎች ተደራሾቻቸውን በምርጥ ቋንቋ እና ቀስቃሽ መገለጫዎች ለማስደነቅ ይሞክራሉ። ይህ ግን በጣም ከፋፋይ ሊሆን ይችላል።
  • ራስዎን ያክብሩ። ሥራዎ ስለ እርስዎ ምን እንደሚናገር ያስተውሉ። ፆተኛ፣ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ተፀያፊ፣ መደብ ለዪ እና በብሔር ከፋፋይ ቋንቋ ተጠቅመዋል? በአስተያየት መጣጥፍዎ የሚያሰፍሩት ሐሳብ ከባድ የዜና ታሪኮችን በሚሠሩበት ወቅት፣ የራስዎ ተዓማኒነት እና የሚሠሩለት ተቋም ታማኝነትን በተመለከተ የተደራሾችዎ አመለካከት ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል።
  • ዕይታዎን ያስቀምጡ። በግጭት ጊዜ ለውጥ የሚያመጡ ሰዎች ይፈልጉ እና ስለእነሱ ይጻፉ። ያሳኩትን ተግባር በመግለጽ ሌሎችም ተመሳሳይ አስተዋፅዖዎችን እንዴት ማበርከት እንደሚችሉ አስተያየት ይስጡ። አጋጣሚውን መፍትሔ ያመጣሉ ብለው የሚያስቧቸውን ጉዳዮች ለመናገር እና ሰዎች ምክሮን ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡልዎ ለማበረታታት ይጠቀሙበት። የግድ ትክክል መሆን አይጠበቅብዎትም ነገር ግን አዲስ ሐሳብን በማስተዋወቅ አስተዋፅዖ ማድረግ ይፈልጋሉ።
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *