የፌደራሉ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይደርስ የህወሓት አማጺያን መንገድ እየዘጉ ነው አለ።

የፌደራሉ መንግሥት የወቅታዊ ሁኔታ መረጃ ማጣሪያ በትዊተር ገጹ ላይ ይፋ እንዳደረገው፤ የህወሓት አማጺያን ባለፉት ሦስት ቀናት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶችን ይዘው ወደ ትግራይ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 189 የደረቅ ጭነት መኪኖች ላይ መንገድ በመዝጋት “የሽብር ጥቃት ፈጽመዋል” ብሏል። የህወሓት አማጺያን በአፋር ክልል ዞን አራት፤ ያሎ ወረዳ ፈረንቲሱ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ጥቃት መሰንዘራቸውንም መንግሥት አስታውቋል።

በተመሳሳይ ወደ ትግራይ እርዳታ ጭነው ሲጓዙ በነበሩ አስር ተሽከርካሪዎቼ ላይ ጥቃት ደረሰ ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትናንት መግለጹ ይታወሳል። ይህ ጥቃት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት የበለጠ አዳጋች ያደርገዋል ሲል የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመልክቷል። ጥቃቱ የደረሰው በአፋር ክልል ከሰመራ ከተማ 115 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ስፍራ እሁድ ዕለት መሆኑን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በመግለጫው አስታውቋል።

ቅዳሜ ዕለት ደግሞ የህወሓት አማጺያን በአፋር እና በትግራይ አዋሳኝ ድንበር ላይ በፌደራሉ መንግሥት ጎን በተሰለፉ ኃይሎች ላይ ተኩስ ስለመክፈታቸው መገለጹ ይታወሳል። የፌደራሉ መንግሥት እና የአፋር ክልል መንግሥት ከቀናት በፊት ባወጡት መግለጫ የህወሓት አማጺያን በአፋር ክልል በኩል ተኩስ ከፍተዋል። የአፋር ክልል የሰላምና ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ቅዳሜ ዕለት ጋዜጠኞችን ሰብስበው ፈንቲ ረሱ ዞን በያሎ ወረዳ በኩል ጦርነት መከፈቱን አመልክተው፤ የህወሓት አማጺያን በክልሉ ሊያደርሱት ከሚችሉት ጥቃት ሕዝቡ ራሱን በንቃት መጠበቅ አለበት በማለት አሳስበዋል።

የህውሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው በአፋር ክልል በኩል በነበሩ ለፌደራሉ መንግሥት በወገኑ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ ርምጃ ወስደናል ሲሉ ከትናንት በስቲያ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል። አቶ ጌታቸው ረዳ “የተገደበ” ያሉት ወታደራዊ እርምጃ በአፋር በኩል ተሰልፎ በነበረው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል ላይ ያነጣጠረ ነበረ ብለዋል።

ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት ከባድ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዳደረሰ ቢነገርም አስካሁን ከየትኛውም ወገን ይህ ነው የሚባል ዝርዝር መረጃ አልወጣም። ለስምንት ወራት የተካሄደውን ጦርነት ለማብቃት የፌደራል መንግሥቱ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል። አማጺው ኃይል በበኩሉ በድርድር ላይ የተመሰረተ የተኩስ አቁም ለማድረግ ሰባት ነጥቦችን የያዘ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርቧል።

በህወሓት አማጺ በኩል እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጡ ጉዳዮች መካከል አንዱ በትግራይ እና አማራ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎች ይለቀቁ የሚለው ይገኘበታል። የአማራ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት ከዚህ ቀደም ባወጣው መግለጫ የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው ስፍራዎች የክልሉ መንግሥት ለቅቆ እንደማይወጣ አስታውቋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *