የአዲስ አበባ ፖሊስ ከህወሓት ተልዕኮ ተቀብለው በከተማዋ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ ያላቸውን ከ320 በላይ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንና በርካታ ቁጥር ያላቸው የጦር መሳሪያወዎችን መያዙን አስታወቀ።
ኮሚሽነር ጌቱ አርጋውን ጠቅሶ የአዲስ አበባ ፖሊስ በማኅበራዊ ገጹ ላይ በከተማዋ “ብጥብጥና ረብሻ ለማስነሳት ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 325 ግለሰቦች በሕግ አግባብ ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ” አስፍሯል። በተጨማሪም በአንዳንድ መዝናኛና የጭፈራ ቤቶች የአገሪቱን ሰንደቅ አላማ “በሚያዋርድ መልኩ ያልተገባ ድርጊት እየፈፀሙ ሲጨፍሩ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው” የሚገኙ ግለሰቦችም እንዳሉ ተገልጿል።
በዚህም በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች በተጨማሪ በርካታ የጦር መሳሪያዎችና ልዩ ልዩ ወታደራዊ ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር መዋሉን ኮሚሽነር ጌቱ አመልክተዋል። በሂደቱም “ስጋት ናቸው ተብለው በተለዩ 793 ግሮሰሪዎች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ሆቴሎች እና ሌሎች ንግድ ቤቶች” ላይ ፖሊስ ብርበራ እና ፍተሻ ባደረገበት ጊዜ የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችና ሌሎች ቁሶችን መያዙን ኮሚሽኑ ገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ እንዳለው ባካሄደው አሰሳ የተለያዩ አይነት ሽጉጦች እና ጠመንጃዎች በተጨማሪም የአገር መከላከያ ሠራዊት የቀድሞ የደንብ ልብስ፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን፣ የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ፣ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ማዕረጎች እንዲሁም ልዩ ልዩ መለዮዎች እንደተያዙም ኮሚሽነር ጌቱ ተናግረዋል። በተጨማሪም ለፖሊስ ምርመራ የሚረዱ ያላቸውን ላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ ፍላሾች፣ ታብሌት ስልኮች፣ የባንክ የሂሳብ ደብተሮች፣ ሲም ካርድ፣ ሌሎች ሰነዶች መገኘታቸውን ጨምረው አመልክተዋል።
ይህ የፖሊስ መግለጫ የተሰማውባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና (ኢሰመኮ) እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጡት መግለጫ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርና ጥቃት በአፋጣኝ እንዲቆም መጠየቃቸውን ተከትሎ ነው። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾቹ ጨምረውም በሲቪል ሰዎች ላይ እንግልትና እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት ጠቅሰው በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ሰዎች እንዲለቀቁና የተጠረጠሩ ሰዎችም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ እንዲሁም እንግልት ያደረሱና ሌሎች ሕገ ወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ የሕግ አስከባሪዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቀው ነበር።
የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ ጉዳዩን በማስመልከት ለሮይተርስ ዜና ወኪል በሰጡት ምላሽ “ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው ማንነቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ለእስር አልተዳረገም” ብለዋል። ጥቅምት መጨረሻ ላይ የህወሓት ኃይሎች ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የፌደራሉ መንግሥት ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ በርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ማዘዣ መውጣቱ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ በርካታ የቡድኑ ከፍተኛ አመራሮች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ ይታወቃል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ህወሓትን ከሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት የሰረዘው ሲሆን የአገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከጥቂት ወራት በፊት ሽብርተኛ ቡድን ብሎ ሰይሞታል። የፌደራል መንግሥቱ ለስምንት ወራት ያህል በትግራይ ክልል ሲያካሂድ የነበረውን ወታደራዊ ዘመቻን ለመግታት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከክልሉ ሠራዊቱን ካስወጣ ሳምንታት ተቆጥረዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ