የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከትግራይ ግጭት ጋር ተያይዞ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርስ እንግልት፣ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርና ጥቃት በአፋጣኝ ሊቆም ይገባል አለ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልም በተመሳሳይ የትግራይ ተወላጆች፣ የአክቲቪስቶች እና የጋዜጠኞች ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር እንዲቆም ጠይቋል። ፌደራል ፖሊሰ በበኩሉ ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረተው ሊታሰሩ ይችላሉ እንጂ “ማንም ሰው ማንነቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ሊታሰር አይችልም” ይላል። ኢሰመኮ በሲቪል ሰዎች ላይ እንግልትና እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት፣ ብሎም በሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መከሰቱንና ሕይወት መጥፋቱን ገልጿል።
አያይዞም በእስረኞችና በምርኮኞች ላይ የሚደርስ ኢሰብዓዊ አያያዝ፣ በስደተኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ሕጻናትን ለውትድርና መጠቀምን የሚያመላክቱ መረጃዎች እጅግ የሚያሳስበው መሆኑን ገልጿል። ኮሚሽኑ ሐምሌ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን፣ ፎገራ ወረዳ፣ ወረታ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሦስት የትግራይ ተወላጆች በድንገት በተሰባሰቡ ነዋሪዎች በደረሰባቸው ድብደባ መገደላቸው ጥቆማዎች ደርሰውኛል ብሏል።
በሦስቱ ሰዎች ላይ ይህ ጥቃት የደረሰው የትግራይ ኃይሎች በወሰዱት የጥቃት እርምጃ የፎገራ ወረዳ ነዋሪዎች የሆኑ የሚሊሻ ቡድን አባላትና የወረዳው የሰላምና ፀጥታ ኃላፊ መገደላቸው ከተነገረ በኋላ ነው ብሏል ኢሰመኮ። ኢሰመኮ በደቡብ ጎንደር የተከሰተው ሁኔታ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች እንዳይዛመት የሚያሰጋ ነው ብሏል።
“በትግራይ ክልል በሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ላይና የህወሓት/ትግራይ መከላከያ ኃይሎች ተቃዋሚ ናቸው በሚል በሲቪል ሰዎች ላይ እንደተወሰዱ የሚነገሩ የግድያና የአፈና እርምጃዎች የሚያሳስቡ ናቸው” ብሏል። ኮሚሽኑ አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርስ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስር፣ የንግድ ቤት መዘጋት እና የእንግልት መረጃዎችን እየተከታተለ እንደሚገኝ ጠቁሟል።
ኮሚሽኑ ከሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ ክስተትና እስር መበራከቱን ጠቅሶ የሚድያ ሠራተኞችን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ወደ ሌሎች ቦታዎች እየተወሰዱ ስለመሆናቸው ጥቆማ ደርሶኛል ብሏል። “በየትኛውም አካባቢ ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቀቁና የፌዴራል መንግሥትም ሆነ የክልል መስተዳድሮች በነዚህ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ያደረሱና ሌሎች ሕገ ወጥ ድርጊቶች የፈጸሙ የሕግ አስከባሪ አካላትን ሕግ ፊት ሊያቀርቡ ይገባል” ብሏል ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ መንግሥት ተጋላጭ ለሆነው የማኅበረሰብ ክፍል ከፍተኛ ጥበቃ የማድረግ ኃላፊነት አለበት ያሉ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በእስር ላይ ያሉ ሰዎችን ጨምሮ አጠቃላይ ሁኔታውን በተመለከተ የሚያደርገውን የክትትል ሥራ ይቀጥላል ብለዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽል በበኩሉ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ የትግራይ ተወላጆችን ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መልኩ አስሯል ብሏል።
አምነስቲ፤ የትግራይ ተወላጆች ለእስር የተዳረጉት የትግራይ ኃይሎች የትግራይ መዲና መቀለን መያዛቸው ከተሰማ በኋላ ነው ያለ ሲሆን እስሩም ማንነትን መሠረት ያደረገ ይመስላል ብሏል።
የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ መውጣቱን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች መታሰራቸውን እንዲሁም ለአምስቲ ቃላቸውን የሰጡ ከእስር የወጡ የትግራይ ተወላጆች እስር ቤቶች ትግርኛ ቋንቋ በሚናገሩ ሰዎች እንደሞሉ ለአምንስቲ መጠቆማቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ዳይሬክተር ዲፕሮስ ሙሽን።
አምነስቲ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ታስረው ይገኛሉ ያለ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግሥት ከሕግ አግባብ ውጪ የሆነ እስርን እንዲያቆም ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ በአፋጣኝ ከእስር እንዲለቁ ጠይቋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ቃል አቀባይ ፋሲካ ፈንታ የታሰሩም ሆነ የተዘጉ የንግድ ተቋማት ስለመኖራቸው “የማውቀው የለም” ሲሉ ለሮይተርስ ተናግረዋል። የፌደራል ፖሊስ ቃል አቀባይ ጄይላን አብዲ በበኩላቸው፤ “ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ይችላሉ፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው ማንነቱን መሠረት ባደረገ መልኩ ለእስር አልተዳረገም” ሲሉ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ