አምበሳደር ሬድዋን ሁሴን

በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ ከማቅረብ ይልቅ በሌሎች ተግባራት ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን ከአገር እስከማስወጣት የሚደርስ ውሳኔ ሊውስድ እንደሚችል መንግሥት አስታወቀ።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ድኤታ አምባሳደር ሬድዋን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እርዳታ ለመስጠት ወይም ለማስተባበር ከሚፈልጉ አካላት መካከል “ከእርዳታ ይልቅ ፕሮፓጋንዳ የማስተባበር፣ የኢትዮጵያን መንግሥት የማዋከብ፣ የማጠልሸት ዘመቻ ላይ ያሉ” እንዳሉ ጠቅሰዋል። መንግሥት እነዚህ አካሎች እንዳስጠነቀቀ ተናግረው፤ “ጉዳዩ በዚህ ከቀጠለ መንግሥት አገር የማዳን ኃላፊነት ስለሚወጣ ከአንዳንዶቹ ጋር አብሮ የመሥራት ሁኔታውን እንደገና እንደሚቃኝ፣ አንዳንዶቹንም ከአገር ለማስወጣት እንደሚገደድ” ገልጸዋል።

ይህንን ማሳሰቢያ የሰጡት ለተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም ለሌሎች እርዳታ አቅራቢ እና አስተባባሪ አካሎች ነው። መንግሥት የተኩስ አቁም አውጆ ሳለ፤ “በሌላኛው ወገን የሚደረገው ትንኮሳ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ መንግሥት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደገና ለማጤን ይገደዳል። በዚህም ምክንያት ሁሉን አቀፍ እርምጃ ለመውሰድ ይገደዳል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ “በሌላኛው ወገን የሚደረገውን ትንኮሳ አንዲያጋልጥ፣ እንደዲኮንን” የፌደራል መንግሥቱ ይጠይቃል ሲሉም በመግለጫው አስታውቀዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔውን አልደገፈም

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ድኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ መንግሥት በትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ቢወስድም፤ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን “አፍራሽ ዝንባሌ አሳይቷል” ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበተሰብ ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ መንግሥት ተኩስ እንዲያቆም ሲጠይቅ ቢቆይም፤ የፌደራል መንግሥት የተኩስ አቁም ከወሰነ በኋላ ግን ውሳኔውን በአዎንታዊ መንገድ እንዳላየው ወቅሰዋል።

አምባሳደር ሬድዋን፤ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ሲጠይቁ የነበሩ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ወገኖች “አዎንታዊ ውሳኔውን ተከትሎ አዎንታዊ ድጋፍ ለማድረግ ሳይሆን፤ ብዙዎች ሲንቀሳቀሱለት የነበረወን ውሳኔ መንግሥት ወስኖም እያለ ይህንን ከማደነቅ፣ የጎደለውን ከመሙላትና ከማሳሰብ ይልቅ ለዚህ አፍራሽና አሉታዊ ምክንያት በመደርደር የውሳኔውን አነስተኛነት ለማሳየት ተንቀሳቅሰዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።

መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው፤ “ተጨማሪ እልቂትን ለማስቀረት ያለመ፣ የምጣኔ ሀብትና ፖለቲካዊ አመክንዮም ያለው” እንደሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። የትግራይ ሀይሎች በበኩላቸው የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ድል እንደተቀዳጁ ገልጸው፤ የፌደራል መንግሥት የተኩስ አቁም ለመቀበል ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጉዳይ

የተለያዩ የረድኤት ድርጅቶች የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል እርዳታ እንዲዳረስ ተገቢውን ድጋፍ እያደረገ እንዳልሆነ ወቅሰዋል። አምባሳደር ሬድዋን ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ “የሰብዓዊ እርዳታ እናቀርባለን ወይም እናስተባብራለን ያሉ አካላት ሲጠይቋቸው የነበሩ ነገሮች በአጠቃላይ ተመልሰው እያለም አሁንም መንግሥት በአካባቢው በነበረበትና ግጭት ይካሄድ በነበረበት ወቅት ያሰሟቸው የነበሩ ወቀሳዎችና ስሞታዎች እያሰሙ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ከሳምንታት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወደ ትግራይ ክልል የምግብ እርዳታ ጭኖ ሲሄድ መሰናክል ገጥሞት እንደነበረ ከቀናት በኋላ ግን እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎቹን ወደ ክልሉ ማስገባት መቻሉን ገልጿል።

በአውሮፓ ሕብረት አቅራቢነት የጸደቀውን የውሳኔ ሐሳብ በተመለከተ

በ47ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የአውሮፓ ሕብረት ከትግራዩ ግጭት ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደሚያሳስበውና የኤርትራ ሠራዊት አባላት ከትግራይ በአስቸኳይ እንዲውጡ በመጠየቅ ያቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ይህ የሕብረቱ የውሳኔ ሐሳብ “ጊዜውያን ያልጠበቀ እና በፖለቲካ ፍላጎት የተላለፈ” ነው ሲል ተቃውሟል። አምባሳደር ሬድዋን ይህንኑ ጉዳይ አንስተው የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን “ስሞታ ሳያሰማ፣ መንግሥት አልተባበረንም ሳይል፤ አንዳንድ አገራትን በማስፈራራት፣ አንዳንዶቹን በማባበል የውሳኔ ሐሳብ ቀርቦ ኢትዮጵያ ላያ አቋም እንዲወጣ መደረጉ” የመንግሥትን አዎንታዊ እርምጃ ከግምት ያላስገባ እንደሆነ ተናግረዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *