ኮረምና አላማጣ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸው የተዘገበ ሲሆን፤ በተጨማሪም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራን በኃይል ለመያዝ ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ሰኞ ምሽት ክልሉ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል። የትግራይ ኃይሎች ኮረም እና አላማጣ መያዛቸው ቀደም ሲል ተዘግቦ ነበር። የትግራይ ኃይሎች ኮረም ከተማን ሰኞ አመሻሸ ስለመያዛቸው የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የተናገሩ ሲሆን፤ አላማጣ ከተማን ደግሞ ሰኞ ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ ስለመያዛቸው የዓይን እማኞች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የአማራ ክልል ብሔራዊ መንግሥት ትናንት ምሽት ባወጣው በመግለጫው፤ “የአማራ ሕዝብ የማንነትና የወሰን ጥያቄ እያነሳ ሲታገልባቸው የቆዩ የራያ አላማጣና ኮረም አካባቢዎችን ዳግም በመውረር እንዲሁም ወልቃይት ጠገዴ ሴቲት ሁመራ በኃይል ለመያዝ በተለይም ጠለምትና አካባቢውን ለመያዝ” እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብሏል። ክልሉ የህወሓት ቡድን ከአማራ ክልል ጋር በሚያዋስኑት ሁሉም አቅጣጫዎች መጠነ ሰፊ ወረራና ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ አመልክቶ፤ “የአማራ ክልል ሕዝብ ጉዳዩን ከህልውናው ጋር በማስተሳሰር እንዲመለከተውና . . . ቀጣይ የምናደርገው ሁሉ አቀፍ ትግል የህልውና ትግል መሆኑን አውቆ በገንዘብ፣ በጉልበትና በህይወት መስዋዕትነት አስፈላጊውን አበርክቶ ለማድረግ ራሱን እንዲያዘጋጅና የመንግሥትን ጥሪ እንዲጠባበቅ” ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም ክልሉ በየትኛውም ዘመን ወታደራዊ ስልጠና ወስደው በማንኛውም የመንግሥት የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ሲያገለግሉ ቆይተው የሙያ ዘርፍ የቀየሩ የክልሉ ነዋሪዎች ‘ለህልውና የሚደረገውን የትግል ጥሪ ተቀብለው’ በየአካባቢው በሚገኙ የሰላምና ደኅንነት ጽ/ቤት እንዲመዘገቡ ጥሪ አስተላለፏል።
ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ በአማራ እና በትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ ከሚነሳባቸው ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

የትግራይ ኃይሎች የሚመሩ አመራሮች እኚህን ስፍራዎች ተመልሰው በትግራይ ቁጥጥር ሥር እስኪያውሉ ድረስ ጦርነቱ ይቀጥላል ሲሉ ቆይተዋል። የአማራ ክልል ብልጽግና ጽ/ቤት ግን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ “ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ፣ ጠለምትና ራያ በራሳቸው መስዋዕትነት ነፃነታቸውን ያስከበሩ የአማራ አካባቢዎች መሆናቸውን በድጋሚ እናሳውቃችኋለን” ብሏል።
የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ የተናጠል የተኩስ አቁም በማወጅ ሠራዊቱን ካስወጣ በኋላ የህወሓት ኃይሎች ዋና ከተማዋን መቀለን ጨምሮ አብዛኛውን የክልሉን አካባቢዎች መቆጣጠሩ ይታወሳል። ባለፉት ጥቂት ቀናትም የአማራ ክልል የተወሰዱብኝ ግዛቶች ናቸው በማለት ከወራት በፊት በቁጥጥሩ ስር አስገብቷቸው በነበሩት አካባቢዎች ላይ የህወሓት ኃይሎች ጥቃት መክፈታቸው ተነግሯል።
ይህንንም ተከትሎ ኮረምና አላማጣ በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባታቸውን ሮይተርስና ኤኤፍፒ የዜና ወኪሎች ዘግበዋል። የአማራ ክልላዊ መንግሥት በኮረምና አላማጣ በኩል ህወሓት ወረራ መክፈቱን ያመለከተ ሲሆን፤ ጉዳዩን በተመለከተ የፌደራል መንግሥቱ እስካሁን ያለው ነገር የለም።
ምንጭ – ቢቢሲ