ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያወጀችው የተናጠል የተኩስ አቁም ‘ከበባ’ ነው እንዲሁም መንግሥት ረሃብ እየፈጠረ ነው በማለት የአውሮፓ ኮሚሽን ያወጣውን ማስጠንቀቂያ ኢትዮጵያ ውድቅ አደረገችው።

ኢትዮጵያ ያወጀችው “ተኩስ አቁም ሳይሆን ከበባ ነው ረሃብም እንደ ጦር መሳሪያ እያገለገለ ነው” በማለት የአውሮፓ ሕብረት የቀውስ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጃኔዝ ሌናርቺክ ለሕብረቱ ፓርላማ በሰጡት ገለፃ ተችተዋል። በብራስልስ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኮሚሽነሩን ንግግግር አሳዛኝ በማለት ከበባ ነው መባሉንም ውድቅ እንዳደረገው በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ አስፍሯል።

ኮሚሽሩ “የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በማፍረስ፤ መውጫዎችን በመዝጋት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀመበት ነው ማለታቸው መሬት ላይ ያለውን እውነታ ችላ በማለት በመንግሥት ላይ መሰረተ ቢስ ክሶችን መሰንዘርን መርጠዋል” ብሏቸዋል። ኮሚሽነሩ ይህንን የተናገሩት ሰኔ 29/2013 ሲሆን ይህም ንግግራቸው በአውሮፓ ሕብረት መፅሄት ‘ኢዩ ኦብዘርቨር’ “ኢትዮጵያ ክሬቲንግ ፋሚን ኢን ትግራይ፤ ኢዩ ዋርንስ’ (የኢትዮጵያ መንግሥት ሰው ሰራሽ ረሃብ እየፈጠረ ነው) በሚል ርዕስ ታትሟል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በትግራይ ክልል ረሃብ እንዳይከሰት ሲሰራ ቆይቷል በማለት በሁለት ዙርም በተደረገ እርዳታ የረድኤት ድርጅቶች 70 በመቶ የሚሆነውን የችግሩን ገፈት ቀማሾች መደረስ መቻሉን በመግለፅ ያሳለፈችው የአንድ ወገን ሰብዓዊ የተኩስ አቁም አዋጅ እነዚህን ዓላማዎች ለማሳካት የበለጠ ይረዳል ብሏል መግለጫው። የፌደራል መንግሥት ካለው ቁርጠኝነት ጋር ተያይዞ የሰብዓዊ ፍላጎት አገልግሎት ማቅረብ ለሚሹ ወገኖች ሁሉ የበረራ ፈቃድም መስጠቱም በመግለጫው ሰፍሯል።

ኮሚሽነሩ በበኩላቸው መንግሥት እያደረገ ያለው ተግባር ከበባ ነው ሲሉም ማሳያው “የትግራይን ድንበር መዝጋት፣ በረራዎችን ማገድ፣ የመንገድ እና የባቡር መሰረተ ልማቶችን በማውደም፣ የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በማቋረጥ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሠራተኞች እንዳይገቡ መከልከሉን” ጠቅሰዋል። “በትግራይ በአሁኑ ወቅት 900 ሺህ ነዋሪዎች ተርበዋል። ሌላ አንድ ሚሊዮን ነዋሪም በረሃብ ቋፍ ላይ ነው። ረሃቡ ሰው ሰራሽ ነው። ለረሃቡ ተጠያቂ ለሆኑ አካላትም ውርደት ነው” ብለውታል።

ኤምባሲው በማኅበራዊ ትስስር ገፁ እንዲሁም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባጋራው መግለጫ በክረምት ወቅት የክልሉ አርሶ አደሮች እንዲያርሱና ከሰብዓዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ይሁን የሚለውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጥያቄ መልስ ሰጥቷል ብሏል። በትግራይ በነበረው ወታደራዊ ዘመቻ ከጅምሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብን ጨምሮ አጋር ድርጅቶችና የተለያዩ አካላት በትግራይ ክልል የተኩስ አቁም ጥሪ ያደርጉ እንደነበር የጠቆመው መግለጫው የአውሮፓ ኮሚሽንም ትግራይን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ሲጠይቅ እንደነበር አውስቷል።

ኢትዮጵያ የተናጠል ተኩስ አቁም ስታውጅ በአገር ውስጥ ያለውን ጥሪ ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን በአጋሮች በተለይም በአውሮፓ ኮሚሽን ለሚደረጉ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ምላሽ እንደሆነ በመጥቀስ ይህም በትክክለኛው አቅጣጫ አንድ እርምጃ እንደመሆኑ መጠን ሊደነቅ ይገባዋል ብላለች። ሰኔ 14/2013 ብሔራዊ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ ከተጠናቀቀ በኋላ ጳጉሜ 1/2013 ዓ.ም የሚከናወነውን ቀሪ ምርጫ ከግምት ካስገባ በኋላ መንግሥት በትግራይ ውስጥ ላሉት ሕዝቦቹ የመጪው የፖለቲካን አካሄድ በተመለከተ እንዲያስቡበት የጥሞና ጊዜ መስጠቱንም ተመልክቷል።

“ይህ ኃይል ከማሳየት ይልቅ ለሰዎች ቅድሚያ የሰጠ በማንኛውም መስፈርት የላቀ ውሳኔ ነው” በማለትም መግለጫው የአገሪቱን አቋም ያስረዳል። በተፃራሪው ህወሓት የእነዚህን ግቦች ስኬት ለማደናቀፍ የተቻለውን ሁሉ ሲያደርግ ቆይቷል ያለው መግለጫው ለዚህም ዋቢ ያደረገው ሰብዓዊ የተኩስ አቁም ጥሪን ውድቅ ከማድረጉም በላይ በድንበሮችም ላይ ወታደሮቹን እያሰባሰበ ይገኛል ብሏል።

ከዚህም በተጫማሪ ትግራይን ከአጎራባች ክልሎች ጋር የሚያገናኙ ድልድዮችን አፍርሷል እንዲሁም በአማራ ክልል እና በኤርትራ ላይ ጦርነት ለመክፈት ዝቷል ብሎታል። ውግዘቶቹ በእነዚህ የህወሓት ረብሻ ድርጊቶች ላይ መሰንዘር ነበረባቸው ብሏል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) በበኩሉ ጎንደርና ሽረን የሚያገናኘው የተከዜ ድልድይ ሰኔ 25/2013 ዓ.ም በአማራ ልዩ ኃይል ከጥቅም ውጭ እንዳደረጉት የሚጠቁም መረጃ እንዳለው አስታውቋል።

ህወሓት በስምምነት ላይ የተደረሰ የተኩስ አቁም እንደሚቀበል ያስታወቀ ሲሆን ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከል ከክልሉ የኤርትራ ወታደሮችና የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል። ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን እንዲመረመሩ እንዲሁም ቴሌኮም፣ መብራትና የአውሮፕላን በረራን ጨምሮ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲጀመሩም ጠይቋል።

ከኢትዮጵያ በኩል የተሰጠው መግለጫ በሕብረቱ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባው ላይ በኮሚሽነሩ እንዲሁም በቅርቡ በልዩ መልዕክተኛው ፔካ ሃቪስቶ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተሰነዘሩ ክሶች ያለውን ቀውስ ለማቃለል እንደማይጠቅሙም አስምሯል። የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የአውሮፓ ሕብረት ልዩ ልዑክ ፔካ ሃቪስቶ “በየካቲት ወር የኢትዮጵያን ከፍተኛ አመራር ባገኘሁበት ወቅት ይጠቀሙበት የነበረው ቋንቋ የትግራይን ሕዝብ እንደሚያጠፉት፤ የትግራይን ሕዝብ ሙሉ በሙሉ በሚቀጥሉት 100 ዓመታት እንደሚጠራርጉት የመሳሰሉትን ነው” በማለት መናገራቸው ይታወሳል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ በወቅቱ “ይህ ኃላፊነት የጎደለው ነው፣ ፈፅሞ ሐሰት ነው፣ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ መንገድን የተከተለ አይደለም” በማለት የልዑኩ መግለጫ የተደበቀ አላማ ያለው ሲሆን በተለይም ከፍተኛ የኢትዮጵያ አመራሮች የትግራይን ሕዝብ ማጥፋት ይፈልጋሉ የሚለውም ጉዳይ ልዑኩ በምናባቸው ወይም በሆነ መንገድ ትውስታቸው ተዛብቶ ይሆናል ብሏል።

የኢትዮጵያ አጋሮች ሁኔታውን በትክክለኛው አኳኋን ለመመልከትና መሞከርና አገሪቱ ለመፍታት እየሞከረቻቸውን ያሉ ተግዳሮች መጠን ተገንዝበው የተወሰዱትን አዎንታዊ እርምጃዎች እውቅና ሊሰጡ ይገባል ብሏል መግለጫው በማጠቃለያው። ሕብረቱ በበኩሉ የሰላም ስምምነት እንዲደረስና ሰብዓዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲሻሻል ልዩ መልዕክተኛውንና የፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፔካ ሃቪስቶን እንደላከ አስታውሶ የልዩ መልዕክተኛው ጉብኝት ምንም ፍሬ አላፈራም ብሎታል።

ኮሚሽነሩ በግጭቱ የጦር ወንጀሎች ወይም በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የሚቆጠሩ መዋቅራዊ የሆነ መደፈር፣ የዘፈቀደ ግድያ ጥሰቶችን መመልከታቸውንም አስምረዋል። በአሁኑ ወቅት ጦርነት በክልሉ መቀነሱን የገለፁት ሌላኛው የሕብረቱ አባልና የስሎቬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንዜ ሎጋር የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል ከበርካታ ግዛቶች እንደወጣና የኤርትራም ኃይል ወደ ኤርትራ ድንበር አካባቢ መመለሱን አስምረዋል።

በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግሥቱና የአማራ ሚሊሻ ጥምር ኃይል በምዕራብ ትግራይ እንደሚገኝም ተናግረዋል። ነገር ግን ከስምንት ወራት ጦርነት በኋላም 91 በመቶ የክልሉ ሕዝብ “አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልገዋል” በማለት “ሁሉም አካላት ሙሉ የተኩስ አቁም ሊያደርጉ ይገባል” ብለዋል። የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ቀጥተኛ የበጀት እርዳታን ያገደ ሲሆን የእርዳታ ሠራተኞችንም የሚያደናቅፉ ባለስልጣናትንም ጥቁር መዝገብ ውስጥ አካትታለሁ በሚል ማስጠንቀቁን ‘ኢዩ ኦብዘርቨር’ ባወጣው ዘገባ ጠቅሷል።

ሕብረቱ ድንበሩን አቋርጠው ወደ ደቡብ ሱዳን ለገቡ ስደተኞችም 118 ሚሊዮን ፓውንድ ወጪ መደረጉንም ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሓት ከጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ተዋጊዎች ተገድለዋል። ባለፈው ሳምንት የፌደራሉ መንግሥት ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሃት በበኩሉ መቀለን በኃይል እንደተቆጣጠሩ ተናግሯል።

የፌደራል መንግሥት ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱን ማስወጣቱንና የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል። በሌላ በኩል ህወሓት በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ቢያስቀምጥም ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *