ግጭቶች እያደጉ ሲመጡ እና ሲስፋፉ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉትን ቡድኖች ጨምሮ ተደራሾቻችን ምን እየተከናወነ እንዳለ በደንብ እንዲረዱት የሚያግዙ በርካታ ጠቃሚ ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን። የሚከተሉት ሶስት ነጥቦች በግጭት እና በግጭት ተለዋዋጭነት ላይ ከነበረን ውይይት ላይ የተወሰዱ ናቸው።
5.1 ግጭቶችን በተመለከተ ያለ አቀራረብ
በክፍል አንድ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት የግጭት አቀራረባቸውን በተመለከተ የተለያዩ መንገዶችን መርምረናል እንዲሁም አምስት የተለያዩ ስልቶችን ለይተናል። እነሱም፦
- ሽሽት
- ድል ማድረግ
- ድርድር
- የችኮላ መፍትሔዎች
- ትብብር
ከትብብር አቀራረብ ውጪ ያሉት ሌሎቹ ስልቶች አሉታዊ ውጤቶች እንዳላቸው አይተናል። በብዙ አጋጣሚዎች እነዚህ አቀራረቦች የአንዱ መሸነፍ የሌላው ማሸነፍ በሆነው በአሸናፊ እና ተሸናፊ ወይም በዜሮ ድምር ውጤት ይጠናቀቃሉ። ይህ ውጤትም በቡድኖች መካከል ሰላማዊ ግንኙነትን ለማሻሻል ምንም ዓይነት አስተዋፅዖ አያደርግም። በተጨማሪም በሰብአዊ ፍላጎቶች ላይ ባደረግነው ውይይት እንዳየነው መሠረታዊ የሰዎች ፍላጎትን የሚመለከቱ ግጭቶች በቀላሉ ድርድር ሊደረግባቸው አይችሉም።
ቡድኖች በግጭት ላይ የሚኖራቸውን አቀራረብ በተመለከተ ከወሰድነው ግንዛቤ በመነሳት ጋዜጠኞች የተወሰኑ ጠቃሚ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እንችላለን። ለምሳሌ አንድ ቡድን ወደ ኋላ በመመለስ ግጭትን ለመሸሽ እንደሚፈልግ ከተረጋገጠ፣ ጋዜጠኞች የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳት ይችላሉ:
- ግጭቱን ለመሸሽ እየሞከራችሁ ያላችሁ ይመስለኛል፤ ምንም እንኳን አሁን ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ በመሆን የጉዳቱን ዋጋ ብትከፍሉም፣ ውጤቱ ለወደፊቱ ፍትሐዊ እና ትክክለኛ ይሆናል ብለው ያምናሉ? ካልሆነ ታዲያ ግጭቱ ሌላ ጊዜ ሲያገረሽ ምን ይባላል?
- አሁን ላይ ይህን ሥምምነት ካደረጉ ወደፊት ተጨማሪ ሥምምነቶችን እንዲቀበሉ ጥያቄ እንደማይቀርብልዎ እንዴት እርግጠኛ ሆኑ?
- ይህን ጉዳይ የፈቱበት አቀራረብ ከዚህ ቡድን ጋር ወደፊት የሚነሱ ግጭቶችን ለመፍታት ያልዎት አቅም ላይ ምን ተፅዕኖ ያሳድራል? በመተማመን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ለመመሥረት ምን አስተዋፅዖ አድርጓል? የተሻሉ የግንኙነቶች መንገዶችን እንዲከፈት አድርጓል?
- የወደፊት ግጭቶችን ለመቅረፍ የሚያስችል ምን ዓይነት ትምህርት ከሌላኛው ቡድን አገኙ? እነርሱስ ስለ እናንተ ምን የተማሩ ይመስላችኋል?
- በሌላ በኩል አንድ ወገን በግጭቱ የበላይነትን ለማግኘት ኃይሉን የሚጠቀም ከሆነ እና ሌላው ወገን የሚያፍርበት ሥምምነት እንዲያደርግ ካስገደደ፣ ጋዜጠኞች ቡድኖቹ ስለ ሥምምነቱ የሚሰማቸውን ስሜት ለመቀለጃነት መጠየቅ ይፈልጋሉ። ልንጠይቃቸው የሚገቡ የተወሰኑት ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው።
- ከውጪ ለሚመለከት የሌላውን ወገን ፍላጎቶች ለማስተናገድ ማንኛውንም ሥምምነት ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑ ይመስላል። እውነታው ይህ ነው?
- ይህ ከቡድኑ ጋር በሚኖርዎ የወደፊት ግንኙነት ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለው ይጠብቃሉ?
- በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል ማምጣት የሚችሉ ይመስላል። ነገር ግን ይህ ለወደፊቱ እንዴት ይቀጥላል ብለው ያስባሉ? ለወደፊቱ ሌላኛው አካል እንደገና ጥያቄውን ይዞ እንደማይመለስ እርግጠኛ ነዎት?
- ጥያቄ፦ በሌላው ወገን ቦታ ቢሆኑ ምን ዓይነት ምላሽ ይኖሮታል?
5.2 የሰላም ሒደቶችን ሽፋን መስጠት
ቡድኖች በሰላማዊ ሒደቶች ውስጥ ሲሳተፉ ተደራሾቻቸውን ለመረጃ ቅርብ እንዲሆኑ ለማድረግ እኛ ጋዜጠኞች በሒደቱ ውስጥ ጣልቃ ሳንገባ ማድረግ የምንችላቸው የተለያዩ ነገሮች አሉ። የመጀመሪያው ነጥብ ግጭት ውስጥ የገቡ ወገኖች ግጭቶችን ለመፍታት የእውነታቸውን ቢሞክሩም፥ የሚጠቀሙባቸው ሒደቶች ሁሌም በጥሩ ሁኔታ የተቀረፁ ወይም ተገቢ ላይሆኑ ይችላሉ። በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን የሚደግፉ እና የተወሰኑ ቡድኖችን ፍላጎት የሚያናንቁ መስለው ይታዩ ይሆናል። ንቁዎች ሆነን ሒደቶችን በጥንቃቄ መከታተል አለብን። የሰላም ሒደቶችን በምንሸፍንበት ጊዜ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ዘላቂ ሥምምነቶች እንዲደርሱ ለመርዳት የምናከናውናቸው በርካታ ነገሮች አሉ። ከነዚህም ውስጥ፦
- ሰዎች በውይይት ውስጥ ስለተሳተፉ የእውነት መፍትሔ ፈልገው ነው ብለው በአንድ ጊዜ አይቀበሉ። ቡድኖች እንደገና ለመደራጀት፣ ጊዜ ለመግዛት እና ራሳቸውን ለበለጠ ፀብ ለማዘጋጀት የሰላም ድርድር ውስጥ የገቡባቸው ግጭቶች ነበሩ። በድርድሩ ጠረጴዛ ላይ በሚሆነው ነገር ላይ ትኩረት ማድረጋችን አስፈላጊ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እያከናወኑ እንደሚገኝ ማጤን አለብን።
- ድርድሮች በሒደት እያሉ ቡድኖች የተገኘውን መሻሻል ይፋ ሲያደርጉ፥ ይህንኑ ከድርድሩ ውጪ ላሉ ሰዎች በማሳወቅ በመሬት ላይ ካሉ ሰዎች አስተያየት መቀበል አለብን። ይህንን በማድረግ በድርድር ውስጥ የተሳተፉ ቡድኖች ሌሎች አካላት በሥምምነቱ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት እንዲያውቁ እንረዳቸዋለን።
- ትኩረትዎን በጠረጴዛው ላይ ያሉ ቡድኖች በሚለቁት መረጃ ላይ ብቻ አያድርጉ፤ ለድርድር ከሚወክሏቸው ሰዎች ጋር ለመነጋገርም ጊዜ ይውሰዱ። በተለይም በቡድኑ ውስጥ ከሥር ያሉ ሰዎችን ያናግሩ። ለልኂቃኑ ምላሸ እንዲሰጡና የነሱ ሐሳብም መካተቱን ያረጋግጡላቸው።
- ድርድሮች በጣም አደገኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ እና ቡድኖች የመጨረሻ ሥምምነቶች ላይ እስከሚደርሱ ድረስ ምን እየተደረገ እንዳለ ለሕዝብ ማሳወቅ የማይችሉባቸው ሁኔታዎች መኖራቸውን ልብ ይበሉ። ድርድሩ አደገኛ በሆነበት ወቅት ጋዜጠኞች ከውስጥ አዋቂዎች ባገኙት መረጃ ዘገባ ሰርተው በመታተሙ እና አየር ላይ በመዋሉ ድርድሩ በአደገኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ የገባበት አጋጣሚ አለ።
- የተተዉ ሰዎችን መለየት እና “ቀጥሎ ምን ይሆናል?” የሚለውን ጥያቄ ይጠይቁ።
- ሰላም መፍጠር ጊዜ ይወስዳል እና ቡድኖች በጥቂት ሰዓታት ወይም በጥቂት ቀናት ውስጥ ሥምምነት ላይ መድረስ እንደማይችሉ ይገንዘቡ።
የሰላም ኃይሎች ስለሚጠቀሙባቸው ሒደቶች ምንጊዜም ትኩረት ይስጡ። በግጭቱ ተሳታፊዎች መፍትሔ ባለመፈለጋቸው ብቻ ሳይሆን በመጥፎ ሁኔታ በተቀረፁ የሰላም ሒደቶች ምክንያትም የሰላም ሒደቶች ይከሽፋሉ። በጉዳዩ ላይ አስተያየት ለመስጠት የሚያበቃ ዕውቀትና ሙያው ከሌለን ባለሙያዎችን ማነጋገር ይሻለል።
5.3 ስለ ሰላም ምክረ ሐሳቦች እና ሥምምነቶች የሚጠየቁ ጥያቄዎች
ዮሃን ጋልቱንግ የሰላም ዕቅዶችን እና ሥምምነቶችን አስመልክቶ ዘገባ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች የሚከተሉትን ጥያቄዎች እንዲያነሱ ይመክራል።1 ስለ ሰላም ሥምምነቶች ዘገባዎች የሚሠሩበት መንገድ እና ቡድኖችን ልንጠይቃቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን በተመለከተ ጋዜጠኞችን አቅጣጫ ለማስያዝ በጣም ጠቃሚ መነሻ ነጥብ ይሰጣሉ። እነዚህ ሁሉም ጥያቄዎች የሰላም ሥምምነቱ ዘላቂ የመሆን ዕድሉ ዙሪያ ላይ ያጠነጥናሉ፦
ጥያቄዎቹም:
- ምን ዓይነት ዘዴ ተጠቅማችሁ ዕቅዱን ሠራችሁት? በውይይቱ ሁሉም አካላት ተሳትፈዋል?
- ዕቅዱ በሁሉም ቡድኖች ተቀባይነት አለው? ከሌለው፣ ምን ማድረግ ይቻላል?
- ዕቅዱ የሚተገበር ከሆነ በራሱ ሊቆም የሚችል ነው? ካልሆነ፣ ምን ማድረግ ይቻላል?
- ዕቅዱ ግጭት ውስጥ የገቡ አካላት በራሳቸው ውሳኔ መስጠት መብት ላይ የተመሠረተ ነው ወይስ በውጭ ሰዎች ላይ የተመረኮዘ?
- ዕቅዱ ውስጥ ያለው ሒደት ምን ያህል ይዘልቃል? ማን፣ መቼ፣ እንዴት እና የት ምን ማድረግ እንዳለበት ይገልጻል?
- ዕቅዱ ልኂቃኑ በሚሠሩት ሥራ ላይ የተመሠረተው ምን ድረስ ነው?
- ዕቅዱ ቀጣይነት ያለው የግጭት አፈታት ሒደት ነው ወይስ ለአንድ ጊዜ የሚሆን ሥምምነት? ለምን?
- ነውጥ ከነበረ፣ ዕቅዱ የመልሶ ማቋቋም/የመልሶ ግንባታ፣ የዕርቅ እና የፍትሕ ጉዳዮችን ምን ድረስ ይይዛል?
- ዕቅዱ ካልሠራ ሊቀለበስ ይችላል?
- ዕቅዱ ለዚህ ግጭት ባይሠራም አዲስ ግጭት ወይም ችግር ይፈጥራል? ለተሳታፊ አካላት ጥሩ ነው?
5.4 ከተለመዱ ተጠርጣሪዎች ባሻገር ተመልከቱ
በክፍል አንድ ላይ ስለ ግጭት መባባስ በተደረገው ውይይት ግጭቶች እየተባባሱ ሲሔዱ ብዛት ያላቸው የታጠቁ እና ኃይለኛ መሪዎች ወደ ፊት የመውጣት አዝማሚያ እንዳለ አይተናል። ምንም እንኳን ደጋፊዎቻቸው እንደዚህ ያሉ ሰዎች ጠንካራ አመራር ይሰጣሉ ብለው ቢጠብቁም፣ ግጭቶችን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ፈጠራ የተመላበት ሐሳብ ያላቸው ሰዎች ላይሆኑ ይችላሉ። የቡድኑን ሰፊ ክፍል የያዙ አባላትን በማናገር የመፍትሔ አማራጮችን በተመለከተ አጠቃላይ የሆነ ምስል ማግኘት እንችላለን።
ሰዎች የሆነ ቡድን አባል ስለሆኑ ብቻ አንድ ማኅበራዊ ማንነት አላቸው ማለት አለመሆኑን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። በአንድ ግጭት ውስጥ ከተነሱት ጉዳዮች ጋር የማይገናኙ ፍላጎቶች የሚያጋሯቸው ሌሎች ሰዎች በሌሎች አካባቢዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ መመሳሰሎችን ማወቅ አስደሳች ነገር ሲሆን ወዲያውኑ የማይታዩ የተሻሻለ መግባባት እና የግንኙነት ተስፋ ሊኖር እንደሚችል ለማሳየት ሊያገለግል ይችላል። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ምሳሌዎች እጅግ በጣም አሳማኝ የዜና ታሪኮች ስለሚወጣቸው ተመሳሳይ መረጃዎችን መፈለግ የሚያዋጣን ይሆናል።
በቡድኖች ውስጥ በየደረጃው ያሉ ሰዎች ግጭቶች እንዴት እንደሚፈቱ በጣም የተለያዩ ሐሳቦች ሊኖራቸው ይችላል፤ እንዲሁም በግጭቱ ውስጥ በጣም የተለያዩ ተሞክሮዎች ሊኖሯቸው ይችላል። በግጭት ጊዜ በብዛት የሚሠቃዩት ሰዎች መጀመሪያ ላይ አነስተኛ ድምፅ የነበራቸው መሆናቸው በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እውነት ነው ማለት ይቻላል። እነዚህ ሰዎች ደግሞ የመሰማት መብት አላቸው።
በየቡድኑ በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ ሰዎችን በማነጋገር የሁኔታውን አጠቃላይ ምስል እና ሰዎች ግጭቱን እንዴት እንደሚረዱት ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎች እርስ በርስ እንዴት እንደሚተያዩ፣ ያላቸውን ጭፍን እና የተዛቡ አረዳዶች እንዲሁም በጋራ ስላሏቸው ነገሮች ያለንን ዕውቀት ማስፋት እንችላለን።