የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ማቅረብ ለሚፈልጉ አካላት ሁሉ ወደ ትግራይ የሚደረጉ በራራዎችን ከሰኞ ሰኔ 28/ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ፍቃድ መስጠቱን አስታውቋል።
የአስቸኳይ ጊዜ መረጃ ማጣሪያ በትዊተር ገፁ ወደ ትግራይ ለሚደረጉ የሰብኣዊ እርዳታዎች በረራ ፈቃድን በተመለከተ ይፋ ቢያደርግም የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን እስካሁን ድረስ በረራ አለመጀመሩን ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል። ሮይተርስ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛውን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎች እስካሁን አልተደረጉም።
“ፈቃዱ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል አልፎ ወደኛ መምጣት አለበት። እስካሁን ድረስ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል የመጣ የለም” ብለዋል። አክለውም “ከአዲስ አበባ ወደ መቀለ የሄደ በረራ የለም። በረራ ቢኖር እኔ አውቃለሁ” ብለዋል። ከሰሞኑ የተቋረጠው ወደ መቀለ የሚደረጉ በረራዎች ባይጀመሩም ከመቀለ እስከ አዲስ አበባ በአፋር በኩል ከሰኔ 24 እስከ ሰኔ 29 ድረስ ለሰራተኞች ክፍት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ዩኤን ኦቻ) አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ መንገዱ ለሰራተኞቹ ክፍት ቢሆንም የእርዳታ አቅርቦቶች እግድ የቀጠለ መሆኑን ገልጿል። ነገር ግን በአጠቃላይ የትግራይ ክልል ተደራሽነቱ መሻሻሉን ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫው አስታውቋል። ድርጅቱ እንደሚለው በክልሉ ያሉ በርካታ አካባቢዎች ክፍት በመሆናቸው የሰብዓዊ እርዳታ ድርጅቶች የምግብ ስርጭት፣ የውሃ ማመላለስ፣ የህክምና አቅርቦቶችና የእርሻ ዘሮችን የማከፋፈል ስራ ቀስ በቀስ መጀመር እንዲጀምሩ ያሰችላቸዋል ብሏል።
ሆኖም የሰብዓዊ እርዳታ ቁሶች አሁንም አስፈላጊ እንደሆኑና የሰብዓዊ እርዳታ ዘመቻዎችን ለማስኬድ የሚያስችሉ እንደ ነዳጅ ያሉ ግብዓቶች በአስቸኳይ ሁኔታ እንደሚያስፈልጉ አስምሯል። ኦቻ በመቀለ ከተማ የውሃ ፓምፖችን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ነዳጅ ባለመኖሩ በ23 የተፈናቃዮች መጠለያዎች ላይ ውሃ አለመኖሩን ገልጿል። የነዳጅ እጥረት እንዲሁ በክልሉ ውስጥ የሰብዓዊ እና የንግድ አቅርቦቶች መጓጓዣ ላይ ተፅእኖ እያሳደረ እንደሆነና በርካታ አጋሮችም የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንዳልቻሉም አስምሯል።
ተጨማሪ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሰራተኞችን እና ሰብዓዊ እና የንግድ አቅርቦቶችን ወደ ክልሉ ማስገባት፣ የኤሌክትሪክ እና ቴሌኮሙኒኬሽንን የመሳሰሉ አገልግሎቶችን መመለስ እና ለሰብዓዊ እርዳታ ቀጣይነት ገንዘብ እና ነዳጅ በክልሉ ሁሉ መገኘት ወሳኝ ነው ብሏል። የፈረንሳዩ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ኤምኤስኤፍ በበኩሉ ሶስት ሰራተኞቹ መገደሉን ተከትሎ በአቢ፣ አዲግራት፣ አክሱምና በመካከለኛውና በምስራቅ ትግራይ የሚከናወኑ የዕርዳታ ተግባራቶቹን ማቋረጡን አስታውቋል።
ድርጅቱ በተለያዩ አካባቢዎች ስራውን እንደሚቀጥል አስታውቆ ባልታወቁ ታጣቂዎች የተገደሉ ሰራተኞቹንም ግድያ ምርመራ እንዲደረግም ተጠይቋል። የተባበሩት መንግሥታት በክልሉ ያለው የምግብ እጥረት እንደተባባሰና 400 ሺህ የሚገመት የክልሉ ነዋሪ እንደተራበና 1.8 ሚሊዮን የሚሆን ነዋሪም በረሃብ ቋፍ ላይ እንደሆነም አርብ እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በዚሁ እለትም የኢትዮጵያ መንግሥት አስቸኳይ እርዳታን አግዷል የሚለውን ክስ እንደማይቀበለው ተናግሯል።
“የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን በማገድ የትግራይን ሕዝብ ለማፈን እየሞከራችሁ ነው እንዲሁም ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ እየተጠቀማባችሁት ነው የሚሉ አስተያየቶች ተቀባይነት የሌላቸውና ከእውነታው የሚቃረን ነው” በማለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ ተቀማጭ ለሆኑ ዲፕሎማቶች ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በበከሉላቸው ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት መንግሥታቸው የተባበሩት መንግሥታት እርዳታ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ ትግራይ ሁለት አየር ማረፊያዎች እንዲደርሱ ለማድረግ ለማሳለጥ ፍቃደኛ ነው ብለዋል።
ነገር ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክልሉ ውስጥ ከገባ በኋላ ለሚፈጠሩ ነገሮች መንግሥት ኃላፊነቱን አይወስድም ብለዋል። የህወሃት ቃለ አቀባይ በበኩላቸው ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግሥት ያደረገውን የበረራ ጨምሮ ሌሎች አገልግሎት ማቋረጥ አውግዘው እንደ ጦር መሳሪያነት እየተጠቀመው ነው በማለት ከሰዋል። የኢትዮጵያ መንግሥትና ህወሃት ከጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ባደረጉት ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጎችና ቁጥራቸው የማይታወቅ ወታደሮች ተገድለዋል።
ባለፈው ሳምንት መንግሥት ወታደሮቹን ከመዲናዋ መቀለ እንዳስወጣ ቢገልፅም ህወሃት በበኩሉ መቀለን በሃይል እንደተቆጣጠሩ ተናግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅና ሰራዊቱ ከመቀለ የወጡበት ምክንያት ስጋቶች በሌሎች አካባቢዎች ስላሉና መቀለም የስበት ማዕከል ባለመሆኗ ነው ብለዋል። የፌደራል መንግሥት ባለፈው ሳምንት ከትግራይ ክልል አካባቢዎች መከላከያ ሠራዊቱን ማስወጣቱንና የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል። በሌላ በኩል ህወሓት በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሰባት ቅድመ ሁኔታዎችን ቢያስቀምጥም ከመንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።
ምንጭ – ቢቢሲ