ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ለስምንት ወራት የዘለቀ ጦርነት ውስጥ የገባው ህወሓት በክልሉ የተኩስ አቁም መደረጉን በመርኅ ደራጃ እንደሚስማማና ለዚህም ሰባት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲሟሉ ጠየቀ።

ህወሓት ይህንን ያሳወቀው በዛሬው ዕለት ሰኔ 27/ 2013 ዓ.ም የትግራይ ክልላዊ መንግሥት በሚል ባወጣው መግለጫው ነው ። ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከትግራይ ክልል ሠራዊቱን በማስወጣት ‘ሰብአዊነትን መሠረት ያደረገ’ ያለውን የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ነበር። የመንግሥት ወታደሮች ክልሉን ለቀው የወጡ ሲሆን የትግራይ ኃይሎችም አብዛኛውን የትግራይ አካባቢዎችን መልሰው ተቆጣጥረዋል።

መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ይፋ ካደረገ ከቀናት በኋላ ምላሽ የሰጠው ህወሓት ለተኩስ አቁሙ ተግባራዊነት ዝርዝር ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል። ከቅድመ ሁኔታዎቹ መካከልም በጦርነቱ ውስጥ በከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚከሰሱት የጎረቤት አገር የኤርትራ ወታደሮችና እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎች ወጥተው ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቅ ይገኝበታል።

ከሕግ ውጪ ወደ ትግራይ ክልል ተካተው ቆይተዋል ያላቸውን አካባቢዎች የጦርነቱን መቀስቀስ ተከትሎ በቁጥጥሩ ስር ያስገባው የአማራ ክልል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በተመለከተ ቀደም ሲል አቋሙን ሲገልጽ ቆይቷል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር ባለፈው ቅዳሜ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጥያቄ የተነሳባቸውን ቦታዎች በተመለከተ “ጉዳዩ የተዘጋ መሆኑን እንረጋግጣለን” ብለዋል።

በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት ሁሉም ኃይሎች የተለያዩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸማቸውን በሚመለከት በተደጋጋሚ ክስ ሲቀርብባቸው ቆይቷል። በተጨማሪም ባለፉት ወራት ጦርነቱን ተከትሎ በክልሉ ውስጥ ተፈጽመዋል የተባሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግባቸው ህወሃት የጠየቀ ሲሆን ቴሌኮምና መብራትን ጨምሮ የተቋረጡ አገልግሎቶች መልሰው እንዲጀመሩም ጠይቋል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞም “ያለ ቅድመ ሁኔታ ዓለም አቀፍ በረራዎች በትግራይ ከሚገኙ አየር ማረፊያዎች በቀጥታ ጉዞ እንዲያደርጉ መፈቀድ” ከቅድመ ሁኔታው ውስጥ አካቷል። ህወሓት በቅድመ ሁኔታው ውስጥ ያለምንም ገደብ የሰብአዊ እርዳታ የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻችና ከቤት ንበረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ጠይቋል። የፌደራል ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት እንዲከበርና ይህም ለሚደረጉ ማናቸውም ድርድሮች ዋነኛ መሠረት እንዲሆን ከመጠየቁ በተጨማሪ የዚህ ዓመት የክልሉ በጀት እንዲለቀቅ፣ ነገር ግን የትኛውም የፌደራሉ መንግሥት ወታደራዊና የጸጥታ ኃይል ወደክልሉ እንዳይገባና እንዳይንቀሳቀስ የሚልም የቅድመ ሁኔታው አንድ አካል ነው።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በተግራይ ክልል በነበረው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ ጥቃት መሠንዘራቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል በተካሄደው ግጭት ቁጥሩ በውል የማይታወቅ ሰው ህይወት አልፏል። በተጨማሪም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ግጭቱን በመሸሽ ቤት ንበረታቸውን ጥለው ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል። ሚሊዮኖች ደግሞ የእርዳታ ድጋፍን የሚጠብቁ ሲሆን አስከ 400 ሺህ የሚደርሱት ደግሞ በረሃብ አደጋ አፋፍ ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አመልክተዋል።

የተናጠል ተኩስ አቁም

በህወሓት የሚመራው የክልሉ መንግሥት ከመንበሩ ከተወገደ በኋላ በፌደራል መንግሥቱ የተቋቋመው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የአገሪቱ ፌዴራል መንግሥት “ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ” የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቀረቡ ይታወሳል።

የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ዶክተር አብርሃም በላይ እንደተናገሩት የክረምት ወቅት እየገባ በመሆኑ አርሶ አደሮች ተረጋግተው የግብርና ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ ለተረጂዎች ያለችግር እንዲደርስ በክልሉ ላለው ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የተኩስ አቁም እንዲያደርግ ተጠይቋል። የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ውስጥ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቁን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱም የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት እንዲቆም መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የተኩስ አቁም በተናጠል ማድረጉን ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መከላከያ ኃይሉ የወጣው መቀለ ከዚህ በኋላ “የስበት ማዕከል” ባለመሆኗ ነው ቢሉም ዘግይተው ደግሞ ወታደሮቹ የወጡት ተጨማሪ እልቂትን ለማስወገድ ነው ብለዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ