የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት ጸጥታው ምክር ቤት የትግራይ መከላከያ ኃይል “በአስቸኳይ እና ሙሉ በሙሉ” የተኩስ አቁም እንዲያደርግ አሳሰበ።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ትናንት በኢትዮጵያ የትግራይ ክልል ውስጥ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ይፋዊ ስብሰባ ላይ ይህ የተነገረው። የተመድ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ሮዝመሪ ዲካርሎ በኤርትራ ሠራዊት እና በአማራ ክልል ኃይሎች በሚደገፈው የፌደራሉ መንግሥት ጦር እና በትግራይ መከላከያ ኃይል መካከል ተጨማሪ ግጭቶች ሊከሰት ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሮዝመሪ “የበለጡ ግጭቶች ሊከሰቱ የሚችሉበት እና የፀጥታው ሁኔታው በፍጥነት ሊያሽቆለቁል የሚችልበት ሁኔታ አለ” ካሉ በኋላ፤ “የትግራይ መከላከያ ኃይል የተኩስ አቁም ስምምነቱን በአፋጣኝ እና ሙሉ በሙሉ እንዲያጸድቅ እንጠይቃለን” ብለዋል። የፌደራሉ መንግሥት መቀለን ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ የትግራይ ኃይሎች ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም የትግራይ መዲና መቀለን መቆጣጠራቸው ይታወሳል።

የፌደራሉ መንግሥት መቀለን ለቅቆ ወጥቶ ግጭቱ እንዲቆም እና የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ በሚል ምክንያት ነበር የተኩስ አቁሙን ያወጀው። የትግራይ አማፂያን መቀለን ከተቆጣጠሩ በኋላ ሌሎች ከተሞችንም መያዝ መጀመራቸው በስፋት ሲዘገብ ቆይቷል። ይህን ተከትሎ የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የዜና ወኪል “ወደ አማራ ክልል መሄድ ካለብን እንሄዳለን፤ ወደ ኤርትራ መዝመት ካለብን እናደርገዋለን” ሲሉ ተናግረው ነበር።

ጌታቸው ረዳ “ዋና ዓላማችን የጠላትን የመዋጋት አቅም ማዳከም ነው” ያሉ ሲሆን፤ “ከኤርትራ፣ ከአማራ ወይም ከአዲስ አበባ በኩል ያሉ ጠላቶች የሕዝባችን የደኅንነት ስጋት የማይሆኑበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የህወሓት ኃይሎችን ዛቻ በዝምታ እንደማያልፈው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በትግራይ ክልል ውስጥ የሚገኘው የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ላይ የህወሓት ኃይሎች ከስምንት ወራት በፊት የፈጸሙትን ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ በዝግ በጉዳዩ ላይ መወያየቱ ይታወሳል።

በዚህም ምክር ቤቱ ጠንካራ የጋራ መግለጫ ለማውጣት ከስምምነት ሳይደረስ የቆ ቢሆንም በጦርነቱ የሚሳተፉ ኃይሎች ሰላም እንዲያወርዱና ውይይት እንዲደረግ ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ አርብ ዕለት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል እንዳሳወቀው በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ በውይይት ለመፍታት ዕቅድ እንዳለው አስታውቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ደመቀ መኮንን የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማኅብረሰብ አባላት ስለወቅታዊው የመንግሥታቸው አቋም በተናገሩበት ጊዜ ነው ለውይይት ዕድል መኖሩን ያመለከቱት።

በዚህም መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታት እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሕጋዊ መንገድ ከተመዘገቡ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ችግሩን ለመፍታት ፍቃደኛ ከሆኑ የህወሓት አባላት፣ ከሲቪል ማኅብረሰቡ እና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር ለመወያየት እቅድ አለው ሲሉ ተናግረዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ