አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት በተናጠል ያሳለፈውን የተኩስ አቁም ውሳኔ አዎንታዊ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል ገለጸች።
አገሪቱ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ትናንትና ምሽት ሰኔ 23/2013 ዓ.ም ባወጣችው መግለጫ የተኩስ አቁሙ አዎንታዊ እርምጃ የሚሆነው ግን መሬት ላይ ያለውን ግጭት ማስቆም ከቻለ፣ ጥሰቶች የሚቆሙ ከሆነና ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ ሲደርስ እንደሆነ አትቷል። ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት ጦሩን ከክልሉ መዲናዋ መቀለ እንዳስወጣና በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል የተናጥል ተኩስ አቁም ማወጁን አስታውቋል። የተኩስ አቁሙ አርሶ አደሩ በዚህ ክረምት ወቅት ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲያርስ መሆኑን ከቀናት በፊት አሳውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በትናንትናው ዕለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ጫና መደረግ የለበትም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም እንዲሁ ወታደራዊው ዘመቻ ተሳክቷል ካሉ በኋላ የመቀለ ከተማ የወታደራዊ ስበት ማዕከል መሆኗ እንዳቆመ በመግለፅ ጦሩ የወጣበትን ምክንያት አስረድተዋል።
ጦሩ ተገዶ ነው የወጣው በማለት ለሮይተርስ የተናገሩት የህወሓት ቃለ አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ መላው ክልሉ በቁጥጥሩ ውስጥ እስኪገባ ድረስ ውጊያው እንደማይቆም ነው። ከዚህም በተጨማሪ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያቋረጣቸውን የኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮምዩኒኬሽን፣ ትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶች ሳይለቅ ድርድር አይኖርም ማለታቸውንም ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የአሜሪካ መንግሥትም በመግለጫው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የተቋረጠውን የቴሌኮም አገልግሎት በአስቸኳይ እንዲመልስ ጥሪ ቀርቧል። ጨምሮም በክልሉ ላይ ያሉትን አዳዲስ ለውጦችም በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ብሏል የአሜሪካ መንግሥት በመግለጫው። ሁሉም አካላት አስቸኳይ፣ ዘለቄታዊና ድርድርን ማዕከል ያደረገ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስም ጥሪ ቀርቧል።
በዚህም ያለውን ግጭት የሚያስቆም፣ በትግራይ ላይ መረጋጋትን የሚያሰፍን እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ግዛት የሚያስጠብቅ ሁሉን አቀፍ ውይይት ላይ እንዲደረስም መንገድ ሊመቻች ይገባል ብሏል። ሁሉም አካላት በዋናነት ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ሕጎች በማክበር ያልተገደደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲያመቻቹ ጠይቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በክልሉም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችንና ጭካኔዎችን ለፈፀሙ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበትን ነፃ ዘዴዎችን እንዲቀይሱ ጥሪ አቅርበዋል። አሜሪካ ከዚህ ቀደም እንዳለችው በአስቸኳይና በሚረጋገጥ መንገድ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ክልል ለቀው እንዲወጡ ጠይቃለች። የኤርትራ ወታደሮች ስፍራውን ለቀው መውጣት አስፈላጊ እርምጃ እንደሆነ ያሰመረው መግለጫው ይህም የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰነውን የተኩስ አቁም ውጤታማና ዘለቄታዊ ያደርገዋል ብሏል።
አሜሪካ በዚህ መግለጫው ላይ ዋነኛና ቀዳሚ ትኩረቴ ብላ የገለፀችው በክልሉ ውስጥ ያለውን አስከፊ የሰብዓዊ ሁኔታን ነው። በክልሉ ውስጥ በረሃብ አፋፍ ላይ ያሉትን 900 ሺህ ሕዝብ ጨምሮ ህይወት አዳኝ ምግቦችና እርዳታ ለማድረስ ከአጋሮች ጋር ለመስራት ዝግጁ ነኝ ብላለች። በዚህም ከኢትዮጵያ መንግሥት፣ ከትግራይ ባለስልጣናት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ለመስራት ያላትን አቋምም ገልፃለች።
ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲኖርና የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞች ደኅንነትና ፀጥታንም ማስጠበቅ ይገባል ብሏል። ከዚህም በተጨማሪ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት አስመልክቶ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ በትግራይ ያለውን አስከፊ ሁኔታ ዳስሷል። የምክር ቤት አባሉ ሚካኤል ማክ ካውል ረሃብና ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በክልሉ ሰላማዊ ዜጎች እየተፈፀሙ ነው ብለዋል።
“በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መስረት አንድ ሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ እየተራቡ ነው። መዋቅራዊ የሆነ መደፈርና ፆታዊ ጥቃቶች በሰፊው ተፈፅመዋል። በእኔ ግምገማ መሰረት የጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀም ወንጀል እንዲሁም የዘር ጭፍጨፋ ድርጊቶች በትግራይ ሕዝብ ላይ ተፈፅሟል” ብለዋል። በትግራይ ጦርነት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወታደሮች እና ንጹሑሃን ዜጎች መገደላቸውንም አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በትናንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ 30 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት የሞት አደጋ እንደተጋረጠባቸውና ከዚህም አደጋም ለመታደግ አስፈላጊ ቁሶች ሊደርሱ ይገባል ብሏል። ይህንንም ለማድረስ መንገዶች መከፈት አለባቸው እንዲሁም ሰብዓዊ ተኮር በረራዎች መፈቀድ አለባቸው በማለት በመግለጫው ጥሪ አቅርቧል።
“የቴሌኮም አገልግሎት ሊመለስ ይገባል፣ የመብራት አገልግሎትም እንዲሁ መቀጠል አለበት። በተጨማሪም የሰብዓዊ እርዳታን ለማቅረብ ሕዝቡን ልንደርስ ይገባዋል” በማለት የዩኒሴፍ ተወካይ አዴሌ ክዶር ለቢቢሲ ተናግረዋል።