የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክነድር ነጋ (አራት ተከሳሾች) ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥት ወንጀሎች ችሎት ትዕዛዙን የሰጠው ማክሰኞ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ነው፡፡
የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) አመራሮች የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ፣ አቶ ስንታየሁ ቸኮል፣ ወ/ሮ ቀለብ ሥዩምና ወ/ሮ አስካለ ደምሌ ባለፈው ዓመት ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡00 ሰዓት አካባቢ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ ከተገደለው ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ጋር በተያያዘ፣ በአዲስ አበባ ከተማ ተፈጥሮ በነበረው ብጥብጥ፣ ሁከትና ረብሻ ከጠፋው የሰው ሕይወትና በወደመው ንብረት ሳቢያ መከሰሳቸው ይታወሳል፡፡
ፍርድ ቤቱ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ክሱን ከመሠረተ በኋላ እንደ ክሱ ያስረዱልኛል ያላቸውን ምስክሮች እንዲያሰማ ትዕዛዝ ሲሰጥ፣ ዓቃቤ ሕግ ‹‹ምስክሮቼ ለሕይወታቸው ስለሚያሠጋቸው ምስክርነታቸውን ከመጋረጃ ጀርባ በዝግ ችሎት ይስጡልኝ›› የሚል አቤቱታ አቅርቦ ስለነበር፣ ተከሳሾቹ የዓቃቤ ሕግን አቤቱታ በመቃወም ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀው ነበር፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤት የዓቃቤ ሕግን ክርክር ውድቅ በማድረግ ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡
በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ቅር የተሰኘው ዓቃቤ ሕግ ለፌዴራል ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ይግባኝ ብሎ የነበረ ሲሆን፣ ችሎቱ መዝገቡን መርምሮ፣ ጉዳዩን ሲመለከተው የነበረው ፍርድ ቤት አከራክሮ ውሳኔ እንዲሰጥ መልሶለታል፡፡ ፍርድ ቤቱም በድጋሚ የዓቃቤ ሕግ ጥያቄን ውድቅ በማድረግ ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
በውሳኔው መሠረት ምስክሮቹን ሐምሌ 8፣ 9፣ 14፣ 15 እና 16 ቀን 2013 ዓ.ም. እንዲያሰማ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ምንጭ – ሪፖርተር