የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ያወጀው የተናጠል የትኩስ አቁም ጥሪን የተለያዩ ወገኖች ግጭቱን ለማስቆም በአወንታዊ እርምጃ መሆኑን ገለጹ።

አምስት በኢትዮጵያ የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደሮች፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአፍሪካ ሕብረት የፌደራሉ መንግሥቱ ያወጀው ተኩስ አቁም በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት እንዲከበር ጥሪ ሲያቀርቡ፤ ቻይና እና ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ ውሳኔን ተገቢ እርምጃ ሲሉ አድንቀዋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የፌደራል መንግሥቱን መጠየቁን ተከትሎ የፌደራሉ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ሰኞ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ማወጁ ይታወሳል።

አምስቱ አምባሳደሮች በፌደራሉ መንግሥት የቀረበው የተኩስ አቁም ጥሪ ግጭትን አስቁሞ የሰላም ተስፋን የሚያጭር ነው ብለዋል። የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሰብሳቢ ሙሳ ፋኪ ማሐማት በበኩላቸው ግጭቱን ለማስቆም የተኩስ አቁም ማወጁ ትክክለኛ እርምጃ ነው ብለዋል። የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ግጭትን ለማቆም ብቸኛው አማራጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው ሲል፤ የቻይና በበኩሏ መንግሥት ጦርነቱን ለማስቆም የተኩስ አቁም ማወጁ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ነው ብላለች።

ዩናይትድ ኪንግደምም በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተቀባይነት ያለው ነው በማለት፤ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉም አካላት ለዚህ ተገዢ ሆነው ችግር ለገጠማቸው ሰዎች ሕይወት አድን የሆነ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርስ መፍቀድ አለባቸው ብላለች።

በተባባሩት መንግሥታት የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በበኩላቸው ለወራት ደም ያፋሰሰው ግጭት እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል። አምባሳደሯ ጨምረውም በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት የእርዳታ ድርጅቶች ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ማቅረብ እንዲችሉ መፍቀድ አለባቸው ብለዋል።

የቀድሞ የአሜሪካ አምባሳደሮ ምን አሉ?

በተለያዩ ወቅት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር እና ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ሆነው ያገለገሉት ዴቪድ ሺና፣ ቪኪ ሐድልስተን፣ ፓትሪሺያ ሃስላች፣ ኦውሪሊያ ብራለዚል እና ቲቦር ናዥ የተኩስ አቁም ውሳኔውን ተከትሎ መግለጫ አውጥተዋል። በዚህም በትግራይ ክልል የነበረውን ሁኔታ በቅርበት ሲከታተሉ መቆየታቸውን ገልጸው የፌደራሉ መንግሥት የሰላም አማራጭ ማቅረቡ “ትልቅ እፎይታን ፈጥሮልናል” ብለዋል።

አምባሳደሮቹ ይህ መልካም አጋጣሚ መታለፍ የለበትም ያሉ ሲሆን በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት በሙሉ በመንግሥት የቀረበውን ጥሪ እንዲቀበሉ አሳስበዋል። የሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ስፍራዎች በበጎ አድራጊ ተቋማት ተደራሽ እንዲሆኑ፣ በትግራይ ያሉ የውጭ ኃይሎች ከግጭቱ ክልል ለቀው እንዲወጡ እና የግጭቱ ተሳታፊዎች ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እንዲሁም በትግራይ ቀጣይ ሁኔታ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ውይይት እና ድርድር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋኪ ምን አሉ?

ሙሳ ፋኪ በትግራይ ክልል ውስጥ ሰላም ለማስፈን የታወጀው የተኩስ አቁም ዘላቂ እንዲሆን ሁሉም የመንግሥት አካላት ሁሉን አካታች በሆነ መልኩ እንዲሰሩ ጠይቀዋል። ኮሚሽነር ሙሳ ሁሉም አካላት ዓለም አቀፍ ሕግጋትን በማክበር ንሑሃን ዜጎችን እንዲጠበቁ እና ተጎጂዎች የሰብዓዊ እርዳታ እንዲደርሳቸው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ሙሳ ፋኪ በትግራይ ላለው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሔ ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን ለምታደርገው ጥረት የአፍሪካ ሕብረት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች እና ቻይና ን አሉ?

የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚካሄደውን ጦርነት ለማስቆም የተኩስ አቁም ማወጁ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ነው ብላለች። የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ ግጭትን ለማስቆም ብቸኛው አማራጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ ነው ነው ብሏል።

ቀጣይነት ያለው ሰላም እና መረጋገት ለማረጋገጥ በሕግ የበላይነት እና በሕገ-መንግሥታዊ ማዕቀፍ ውስጥ ገንቢ የሆኑ ውይይቶች ማድረግ ብቸኛው መንገድ ነው ሲልም አክሏል። በቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ክፍል ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት ዉ ፔንግ የኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ተቀባይነት ያለው ነው ብለዋል።

በትግራይ የሚገኙትን ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም፣ መረጋጋት እና ብልጽጋናን ይጎናጸፋሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን ያሉ ሲሆን፤ “ኢትዮጵያውን ውስጣዊ ጉዳያቸውን ለመፍታት አቅሙ እና እውቀቱ አላቸው” ብለዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *