የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፌደራል መንግሥቱ በክልሉ ውስጥ የተኩስ አቁም እንዲደረግ መጠየቁን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታወቀ።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በወጣው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ግጭት እንዲቆም መንግሥት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከዛሬ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የተኩስ አቁም በተናጠል ማድረጉን ገልጿል። ይህ የፌደራል መንግሥቱ ውሳኔ የተሰማው የትግራይ ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን መቆጣጠራቸውን የዓይን እማኞች ከገለፁ በኋላ ነው።

የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የህወሓት ተዋጊዎች አንዳቸው ሌላኛቸውን በሰብዓዊ መብት ጥሰት እና በጅምላ ግድያ ሲወነጃጀሉ ነበር። የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት ጌታቸው ረዳ ለሮይተርስ የመቀለ ከተማ በአሁን ሰዓት በቁጥጥራቸው ስር መግባቷን የገለጹ ሲሆን የዓይን ምስክሮችም ይህንኑ አረጋግጠዋል። ቢቢሲ በከተማዋ ከሚገኙ ነዋሪዎች እንደተረዳው የፌደራል ወታደሮች ከተማዋን ለቅቀው ወጥተዋል።

የፈረንሳይ ዜና ወኪል ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰዎች ሰማሁ በማለት እንደዘገበው ከሆነ ሁሉም የጊዜያዊው አስተዳደሩ ኃላፊዎች ከተማዋን ለቅቀው ወጥተዋል። በትግራይ ክልል ሲየዓስተዳድር የነበረው ህወሐዓት ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱን ተከትሎ ላለፉት ስምንት ወራት በክልሉ ጦርነት ሲካሄድ ቆይቷል።

በጦርነቱ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ለረሃብ አፋፍ ላይ ሲገኙ ከአምስት ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ አስቸኳይ ምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ ብሏል።

የትግራይ ክልል ጊዜ አስተዳደር ምን አለ?

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የአገሪቱ ፌዴራል መንግሥት “ሰብዓዊነትን መሰረት ባደረገና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል መልኩ” የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲያደርግ ጥያቄ ማቀረቡን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ዶክተር አብርሃም በላይን ጠቅሶ ኢዜአ እንደዘገበው፤ የክረምት ወቅት እየገባ በመሆኑ አርሶ አደሮች ተረጋግተው የግብርና ሥራቸውን እንዲያከናውኑ እንዲሁም የሰብዓዊ ድጋፍ ለተረጂዎች ያለችግር እንዲደርስ ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመስጠት የተኩስ አቁም እንዲያደርግ ጠይቋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በተሰጠው ምላሽም “ገበሬው ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲከውን፣ የእርዳታ ሥራው ከወታደራዊ እንቅቃሴ ነጻ ሆኖ እንዲሠራጭ፣ ሰላምን የሚመርጡ አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ የቀረበውን ጥያቄ መቀበሉን ገልጿል። ጨምሮም “ይህ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ በተናጠል የተኩስ አቁም ከዛሬ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ መንግሥት አውጇል” ብሏል።

በዚህም መሠረት የፌዴራልና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት የተኩስ አቁሙን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ መታዘዛቸውም ተገልጿል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ዘጠኝ ነጥቦችን ያካተተ ጥያቄ ለፌዴራል መንግሥት ማቅረቡን ቀደም ሲል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዶ/ር አብረሃም ተናግረው ነበር። ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጨምረውም ከአማጺያኑ በኩል “የሰላም መንገድን የሚፈልጉ በመኖራቸው ለዚህ ኃይል እድል መስጠት አስፈላጊ መሆኑን” አብራርተዋል ብሏል ኢዜአ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዶ/ር አብርሃም በላይ

በግጭቱ ሳቢያ ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የክልሉ ነዋሪ ለችግር ተጋልጦ የቆየ ሲሆን የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ አዳጋች በመሆኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት እና ሌሎች የረድኤት ድርጅቶች ሲገልጹ ቆይተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ከ350 ሺህ በላይ ሰዎች ለረሃብ አፋፍ ላይ ሲገኙ ከአምስት ሚሊየን በላይ ሰዎች ደግሞ አስቸኳይ ምግብ እርዳታ ይፈልጋሉ ብሏል።

ግጭቱ እየተባባሰ በነበረባቸው ባለፉት ወራት ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ሌሎች አገራት መንግሥት ምላሽ ባይሰጥም የተኩስ አቁም እንዲደረግ በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያርቡ መቆየታቸው አይዘነጋም። ስምንት ወራትን ያስቆጠረው በትግራይ ኃይሎችና በፌደራል መንግሥቱ መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ከሳምንት በፊት በነበሩት ቀናት ተባብሶ ከባድ ውጊያ መካሄዱን ከሁለቱም ወገኖች የሚወጡ መረጃዎች ሲያመለክቱ ነበር።

ህወሓት ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ወታደራዊ ግጭት ጦርነት መግባቱ ይታወሳል። ሁለቱ ኃይሎች ለወራት በጦርነት ማሳለፋቸውን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕወሓትን በሽብርተኝነት ፈርጇል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥያቄ ያቀረበው ከክልሉ የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተወካዮች ጋር ውይይቶችን ካካሄደ በኋላ መሆኑ ተገልጿል።

ቢቢሲ በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለማጣራት ወደ ተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የስልክ ጥሪ ለማድረግ ቢሞክርም ከመቀሌ በስተቀር ስልኮች አልሰሩም። ከቀትር በኋላ በክልሉ መዲና የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ ያናገርናቸው ነዋሪዎች እንደገለጹት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ባንኮች ተዘግተው ከተማዋ ጭር ብላ እንደነበርና የመከላከያ ሠራዊትና የፌደራል ፖሊሶችም እንደማይታዩ ገልጸዋል።

በትግራይ ላለፉት ስምንት ወራት በተካሄደው ጦርነት የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈፀማቸውን የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሲገልፁ ቆይተዋል። በጦርነቱ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሱዳን ሲሰደዱ ከ350 ሺህ የሚበልጡ ነዋሪዎች ደግሞ በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን በቅርቡ የወጣ የተባበሩት መንግሥታት ግምገማ ሪፖርት ያሳያል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ግን በትግራይ ረሃብ የለም ሲሉ አስተባብለው ነበር። በትግራይ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጎን ተሰልፎ እየተዋጋ ያለው የኤርትራ ሠራዊት ረሃብን እንደ ጦር መሳሪያ በመጠቀም እና የተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በመፈፀም ይወነጀላል። የኤርትራ መንግሥት ግን ይሄንን ውንጀላ አይቀበለውም።

ምንጭ – ቢቢሲ