የትግራይ ክልላዊ መንግሥት መናገሻ የሆነችው መቀለ ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ፣ ማኅበራዊ ክንዋኔ የሚዘወተርባትና ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች የሚመነጩባት ከተማ ናት።

በአሁኑ ጊዜ በክልሉ ሰፊ የሥራ አጥ ቁጥር ያለ ሲሆን የማኅበራዊ አገልግሎት እጥረትና የጸጥታ ችግሮችም ይስተዋላሉ። በክልሉ ገዢ ፓርቲ ህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግሥት፣ ከፌደራል መንግሥት ጋር ወደ ጦርነት ከገባ በኋላ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታና የአስተዳደር መዋቅር ሲፈርስ መቀለ አንጻራዊ መረጋጋትና የአስተዳደር ሥራዎች አሏቸው ከሚባሉ ከተሞች ቀዳሚዋ ናት።

ሆኖም አንዳንድ ሕገወጥ ግለሰቦች በቡድን ተደራጅተው በሚፈጽሙት ዝርፊያና በሰዎች ላይ እየደረሰ ባለው አካላዊ ጉዳት መማረራቸውና ስጋት እንደተፈጠረባቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ። የ55 ዓመቱ ጎልማሳ አቶ ባይርኡ ግደይ ላለፉት ሦስትና አራት ወራት “እንደ ቢላ ያሉ ድምጽ አልባ መሳሪያዎች ይዘው ያገኙትን ሰው የሚያጠቁና የሚሰርቁ አሉ፤ በከተማዋ ብዙ ነገር አለ። ሌሊቱን በሙሉ በተለያዩ አካባቢዎች ዘረፋ ሲፈጸም ነው የሚያድረው ብል ማጋነን አይሆንም” ይላሉ።

ዝርፊያ ይሁን ማስፈራራት በየትኛውም ዓለም ውስጥ አለ የሚሉት የመቀለ ጸጥታና አስተዳደር ተወካይ ኃላፊ አቶ ገብረሚካኤል ሓየሎም “የከተማችንን የተለየ የሚያደርገውን ግን ያለውን የጸጥታ ክፍተት በማየት እያጋጠመ ያለ መሆኑ ነው። አሁን ግን የተሻለ መረጋጋት እየታየ ነው” ብለዋል።

አሁን ላይ በመቀለ ከተማ አራት እና ከዚያ በላይ ሆነው በሚንቀሳቀሱ እና የደኅንነት ስጋት የሚፈጥሩ ወጣቶች፣ ከቀላል እስከ ከባድ ወንጀሎች የሚፈጽሙ መሆናቸውን ነዋሪዎችና ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይገልጻሉ። ሰኔ አጋማሽ ላይ የትግራይ ቴሌቪዥን ባሰራጨው በምስል የተደገፈ ሪፖርት 84 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ሁለት ዶዘሮችን ሰሜን ክፍለ ከተማ ከሚገኘው ጋራዥ ወደ ሌላ ቦታ ተወስደው ‘በኦክስጅን’ ተቆራርጠው ወደ ተራ ብረት ተቀይረዋል ሲል ተደምጧል።

በትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ማጣራት ሐላፊ ኢንስፔክተር ጽጋቡ ሳሙኤል በሰጡት ቃል ይህ በመጋቢት ወር መጨረሻ ያጋጠመ እንደሆነ በማስታወስ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተጠርጣሪዎች ሁለቱን ዶዘሮች ወደ ዓይደር ክፍለ ከተማ በመውሰድ “በኦክስጅን ቆራርጠው ወደ ብረት ቀይረዋቸው ተገኝተዋል፤ አሁን ተጠርጣሪዎቹ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ነው” ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎችም ከቀላል እቃ እስከ የግል መኪና፣ የእርዳታ እህል የጫኑ የጭነት መኪኖችን መዝረፍና ማስፈራራት እንደሚያጋጥም ገልጸዋል።

‘. . . ዱላ አለ’

መቀለ በርካታ ካፌዎችና የጀበና ቡና የሚሸጥባቸው ቤቶች አሉ። አብዛኞቹ መንገድ ዳር እንዲሁም እግረኛ በሚተላለፍባቸው ቦታዎች ላይ ሳይቀር ሻይ ቡና የሚባልባቸው ስለሆኑ ‘ማስቲካ አለኝ፤ ጫማ ልጥረግ?’ የሚሉ ታዳጊዎች ማየት የተለመደ ነው። ባለፉት ሦስትና አራት ወራት የታየው ግን ‘ዱላ አለ’ የሚል የጦፈ ንግድ ነው።

ሻይ ወይም ቡና እየጠጣን “. . . ዱላ አለኝ” የሚሉ በዝተዋል የሚለው ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ነዋሪ “ቀደም ሲል ሊስትሮና የቤት መጥረጊያ ይዘው የሚዞሩ ሰዎች ነበር የምናየው። አሁን እኮ በተለየ የተዘጋጀ በትር ‘ትፈልጋለህ?’ እያሉ ዱላ እያዞሩ የሚሸጡ ማየት ጀምረናል” ይላል።

ይህ በከተማዋ ያለው የደኅንነት ስጋትን ተከትሎ የመጣ መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ እራስን ለመከላከል በሚል ብዙ ሰው በትር ይዞ መንቀሳቀስን እንደ አማራጭ መውሰዱን ይናገራሉ። ከሁለት ወር በፊት ጅብሪኽ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ሱቅ እንደዘረፈባቸው የሚናገሩት አቶ ባይርኡ “ሱቄ ከተሰረቀ በኋላ እራሴን ለመከላከል ዱላ ገዝቻለሁ” ይላሉ።

“በትሩ ከ20 እስከ 30 ብር ነው የሚሸጠው፤ 50 ብር የተሸጠበት ጊዜም አለ። ዘራፊዎቹ ቢላና ሌሎች ስለታም ነገሮች ስለሚይዙ ሁሉም ሰው አንድ ሜትር የማትሞላ በትር ይዞ ይንቀሳቀሳል፤ ራሱን ለመከላከል እንጂ ለሌላ አይደለም።”

ሌላ ፍጹም የተባለ ነዋሪ በበኩሉ “በቅርቡ 18ሺህ ብር የሚገመት ንብረት ተዘርፎብኛል” ይላል። “ቢራና ለስላሳ የማከፋፍልበት ሱቅ አለኝ። በአንድ ሌሊት ሁሉም ቤቱ ውስጥ የነበረው አረቄ፣ ውሃ፣ ቢራና ለስላሳ ተወሰደ። ከባድ ነው፤ ሕግና ሥርዓርት ስለሌለ ማን ነው ይህንን የሚፈጽመው የሚለው አይታወቅም” ሲል ይናገራል።

“በእጅጉ የሚያስፈራ የጸጥታ ሁኔታ ነው ያለው” የሚለው በሓድነት ክፍለ ከተማ የሚኖረው ወጣት ኃይለሥላሴ በበኩሉ “በማንኛውም ጊዜ እንደፈለግክ መንቀሳቀስ አይቻልም” የሚል ትዝብት አለው። “ሰብሰብ ብለህ ካልሆነ ለብቻ መንቀሳቀስ አይቻልም። ብዙ ሰው ደግሞ የማይሰበር እየተባለ የሚሸጠውን ብትር ወይም ብረት ይዞ ነው የሚንቀሳቀሰው። ይህ ካለፉት ሦስት እና አራት ወራት ጀምሮ የታየ ነገር ነው። ፖሊስ ወይም ሌላ የጸጥታ አካል በሌለበት ሁኔታ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች አስግተውናል” ሲል ተናግሯል።

የሞባይል ስልክ ቅሚያ፣ ጨለማን ተገን በማድረግ መኖሪያ ቤት መዝረፍና ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረስ፣ የመከላከያ ሠራዊት ልብስ እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ ልብስ በመልበስ ከባድ ወንጀሎች መፈጸም፣ ለሰብአዊ እርዳታ የሚመጣ እህልና ዘይት መዝረፍና መሸጥ የመሳሰሉ ከባድ የዝርፊያ ወንጀሎች እንዳሉ የከተማዋ አስተዳደር ገልጿል።

ይህ በክልሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚገናኘው ችግር መሆኑን የሚገልጹት ነዋሪዎች፤ ሁሉም በየተራ አካባቢውን እየጠበቀ እንደሚያድርና ጸጥታ ለማስከበር የተደራጁ ወጣቶች እንዳሉ ይናራሉ። በከተማዋ እየታየ ያለው የዝርፊያ ወንጀል ቀደም ብሎም የነበረ ሲሆን ሰዎች አካባቢያቸው ላይ ከሚስተዋሉ የሥራ አጥነት ችግር፣ የመጠጥና ሌሎች ሱሶች ተጠቃሚ መብዛትና የመጠት ቤቶች መስፋፋት፣ ገንዘብ አለመኖር ጋር የሚያያዝ ነው የሚል ግምት አላቸው።

በሌላ በኩል አንድን ወንጀል ከተፈጸመ በኋላ የሚሰጠው ቅጣት አስተማሪ ሳይሆን መቅረቱ፣ መንግሥት የሥራ እድል ለመፍጠር የሚሰጠው ትኩረት ማነስና የኅብረተሰቡ የልጅ አስተዳደግ በጉዳዩ ላይ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ይናገራሉ። አሁን ላይ ግን በተለይ በጦርነቱ ምክንያት የቀድሞው የትግራይ አስተዳደር ከመቀለ ተገፍቶ ከወጣ በኋላ በእስር ቤቶች የነበሩ ታራሚዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በመለቀቃቸው የወንጀል ድርጊቶች እንዲጨምሩ እንዳደረገ ይታመናል።

በዚህ የተነሳ ነዋሪዎች የእጅ መብራት፣ ጥሩንባ፣ ዱላና የመሳሰሉ ነገሮችን ይዘው አካባቢያቸው እየጠበቁ እንደሚያድሩ ገልጸዋል።

የከተማዋ አስተዳደር ምን አድርጓል?

የመቀለ ከተማ ጸጥታና አስተዳደር ተወካይ ሃላፊ አቶ ገብረሚካኤል ሓየሎም ከትንሽ ሽጉጥ ጀምሮ እስከ ቢላና ሌሎች ድምጽ አልባ መሳሪያዎች በመያዝ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሲያጋጠሙን ቆይተዋል ይላሉ። በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊት ልብስና የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ ለብሰው በዚህ በትጥቅ በተደገፈው ዝርፊያ የተሰማሩ ነበሩ የሚሉት ኃላፊው አብዛኛዎቹ በሕግ ቁጥጥር ስር ስለሆኑ አንጻራዊ መሻሻል አለ ብለዋል።

“በሦስት ወር ውስጥ ከ45 በላይ ተጠርጣሪዎች እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል። በተለይ ከቀዳማይ ወያነ፣ ዓይደርና ሓወልቲ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በተለምዶ 70 ካሬ በመባል በሚጠራው አካባቢ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል እየተደረገ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

“በተጨማሪም ነዋሪዎቹ ያላቸው የደኅንነት ስጋት ትክልል ቢሆን አሁን ግን አንጻራዊ ሰላም እየመጣ ስለሆነ ከሁለት እና ከሦስት ወራት በፊት የነበረው ሁኔታ ላይ አይደለንም ያለነው” ብለዋል። የነበረው ችግር የእርዳታ እህል የጫኑ መኪኖች እስከ መስረቅ እንደሚደርስ የሚናገሩት አቶ ገብረሚካኤል በኲሓ አካባቢ ትጥቅ የያዙ ግለሰቦች ከጂቡቲ የመጡ መኪኖች የጫኑትን እህል በማውረድ ሲሸጡና ሲደልሉ “ሁለት መኪኖች በቁጥጥር ስር አውለናል” ሲሉም የችግሩን ስፋት አስረድተዋል።

እስከ አሁን “80 በመቶ ወንጀል ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር አውለናል፤ የተወሰኑ የሸሹ አሉ እየተከታተልናቸው ነው” ያሉት ኃላፊው ኅብረተሰቡ አካባቢውን እራሱ እንዲጠብቅ ከ1000 በላይ ወጣቶችን ስልጠና በመስጠት የማኅበረሰብ ፖሊሲንግ ሥራ እንዲሰሩ መደረጉን ገልጸዋል።

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *