በትግራይ ክልል ውስጥ ከዋና ከተማዋ መቀለ 25 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገነው ቶጎጋ ከተማ የተፈፀመው የአየር ጥቃት በንፁሃን ላይ ያነጣጠረ ነው መባሉን የኢትዮጵያ ጦር አስተባበለ።
በጥቃቱ ንፁሃን ተገድለዋል የሚባለውንም ሪፖርት አልተቀበለውም። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ዛሬ ሐሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአየር ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የሰማዕታትን ቀን ሊያከብሩ የተሰባሰቡ “የአማፂውን ታጣቂዎች ነው” ብለዋል። የዓይን እማኞችና የሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአየር ጥቃቱ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ተጎድተዋል።
የአየር ጥቃቱ የተፈፀመው ከመቀለ ወጣ ብላ በምትገኘው ቶጎጋ በምትባለው ከተማ ውስጥ እዳጋ ሰሉስ በሚባል የገበያ ስፍራ መሆኑን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ገልጸዋል። በገበያ ስፍራ በደረሰው የአየር ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 60 እንዲሁም የተጎዱ ደግሞ ከአርባ በላይ መሆናቸውን በአይደር ሆስፒታል የሚሰራ አንድ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግሯል። ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበርም በበኩሉ በጥቃቱ የቆሰሉ ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማውጣት ወደ ህክምና ማዕከል መውሰዱን አስፍሯል።
ኮሎኔል ጌትነት በበኩላቸው “በገበያ ቦታ ላይ ፈጽሞ የአየር ጥቃት አልፈጸምንም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሠራዊቱ ኢላማውን በትክክል የመምታት አቅም አለው” ብለዋል ለቢቢሲ። ኮሎኔል ጌትነት በዛሬው መግለጫቸው ከሰሞኑ የትግራይ ኃይሎች ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን መቆጣጠራቸውን የሚገልፀውንም ዜና አጣጥለውታል። ኮሎኔሉ “ህወሓት ሐሰተኛ መረጃ በመንዛት ዘመቻ ተጠምዷል” ያሉ ሲሆን ይህም በዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘንድ ጥንካሬ እንዳለው ለማስመሰል የሚደረግና ከመንግሥትም ጋር ድርድር ለመቀመጥ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ተቋማትና መንግሥታት በኩል ተደጋጋሚ የተኩስ አቁም ጥሪዎች ቢቀርቡም መንግሥት አልተቀበለውም። በአሁኑ ወቅት ውጊያዎች እንደ አዲስ መቀጠላቸው በትግራይ ያለውን ሰብዓዊ ቀውስ የከፋ እንዳያደርገውም ስጋት አለ። በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች የምግብ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።
ምንጭ – ቢቢሲ