የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ ኢዜማ ከምርጫው ጋር ተያይዘው ያስተዋልኳቸው ተግዳሮቶችን በቦርዱ ምላሽ የማይሰጥባቸው ከሆኑ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካል እወስደዋለሁ አለ።

ፓርቲው ዛሬ ረፋድ በዋና ጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ በቅድመ ምርጫ እና ምርጫ ወቅት ኢዜማ በተወዳዳረባቸው በርካታ የምርጫ ክልሎች ያጋጠሙት ችግሮች ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ገልጿል። ሰኞ ዕለት ፕሮፌሰር ብርሃኑ በአማራ እና ደቡብ ክልል በተለያዩ ምርጫ ክልል የኢዜማ ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ ተከልክለዋል ብለዋል። እንዲገቡ የተደረጉ ታዛቢዎችም ከገቡ በኋላም እንዲወጡ መደረጋቸውን አክለው ተናግረው ነበር።

የምርጫውን የመጨረሻ ውጤት እስኪገለጽ እንደሚጠብቅ ያስታወሰው ኢዜማ፣ ምርጫ ቦርድ የቀረቡትን አቤቱታዎች “በአጽንኦት ተመልክቶ ውሳኔ የማይሰጥበት ከሆነ ጉዳዩን ወደ ፍትሕ አካላት ይዘን የምንሄድበትን ሁኔታ ቀድመን ለሕዝብ የምናሳወቅ ይሆናል” ብሏል። የኢዜማ ፓርቲ ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ የፓርቲውን መግለጫ በጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ በመግለጫቸው ኢዜማ ጊዜያዊ ፓርቲ አይደለም ብለዋል።

“ኢዜማ ጊዜያዊ ፓርቲ ሳይሆን ገና ከመነሻው . . . ሩቅ ተጓዥ እና ዘመን ተሻጋሪ ሆኖ ነው” ያሉ ሲሆን ከምርጫው በኋላ የፓርቲውን መዋቅር ለማጠናከር ወደ ሥራ የገባን መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን” ኢዜማ ከየትኛውም ተፎካካሪ ፓርቲ በበለጠ መልኩ በመላው አገሪቱ 455 የምርጫው ወረዳ መዋቅሮችን አደራጅቶ ሲንቀሳቀስ የነበረ እና በዘንድሮ ምርጫው ገዢውን ፓርቲ የሞገተ ነው ብለዋል።

“በጸሃይ እና በዝናብ ውስጥ ቀን እና ለሊት ተሰልፋችሁ በብርቱ ጫና እና መዋከብ ውስጥ ሆናችሁ ድምጻችሁን ለኢዜማ የሰጣችሁ ከልብ እያመሰገንን፤ ያልመረጣችሁንም ውሳኔያችሁን የምናከብር መሆኑን እንገልጻለን” ብለዋል።

የኢዜማ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ በበኩላቸው የመግለጫው ዓላማ፤ ፓርቲው የትኛውንም አይነት ውጤት ያስመዝግብ ኢዜማ “ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ፓርቲ መሆኑን እና የጀመራቸው እንቅስቃሴዎች ቀጣይ መሆናቸውን” ለደጋፊዎች እና ለመላው ሕዝብ ለመግለጽ ነው ብለዋል። አቶ የሺዋስ ኢዜማ በአዲስ አበባ፣ አማራ እና ደቡብ ክልል አጋጠሙኝ ያላቸውን ከ400 በላይ ችግሮች ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁን አስታውሰው ቦርዱ ሥራውን እስኪጨርስ መጠበቅ አለብን ብለዋል።

የኢዜማ ምክትል መሪ አንዷለም አራጌ በምርጫው ዕለት እና ከምርጫው በፊት በፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ላይ የተለያየ ጫና ሲደርስ ቆይቷል ካሉ በኋላ፤ “ሕዝብ ካልመረጠን የሕዝብን ውሳኔ በጸጋ እንቀበላለን” ሲል አክለዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ