ባለፈው ረቡዕ ትግራይ ውስጥ የወደቀው ወታደራዊ አውሮፕላን በአማጺያን ጥቃት ደርሶበት ሳይሆን ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት መሆኑን የኢትዮጵያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናገሩ።

አማጺው ህወሓት ግን የጦር መሳሪያና የኤርትራ ሠራዊትን የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮችን የጫነ ነው ያለውን አውሮፕላን ኃይሎቹ መትተው መታላቸውን ገልጾ ነበር። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ግን አውሮፕላኑ የወደቀው ባጋጠመው የቴክኒክ ችግር ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል። አማጺኑ እንዳሉት ሳይሆን “በሌሎችም አውሮፕላኖች ላይ እንሚያጋጥመው ሁሉ አውሮፕላኑ በቴክኑክ ችግር ምክንያት ነው የወደቀው” ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

ጨምረውም ከወደቀው አውሮፕላን ጋር በተያያዘ የደረሱ ጉዳት ካለ በቅርቡ እንደሚገለጽ በመጥቀስ ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥበዋል። ባለፈው ሳምንት በትግራይ ክልል ውስጥ የተጠናከረ ውጊያ መካሄዱ የተነገረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በገበያ ቦታ ላይ ጥቃት ፈጽሞ በርካታ ሠላማዊ ሰዎችን ገድሏል እንዲሁም አቁስሏል በሚል ተከሷል። ነገር ግን ሠራዊቱ ጥቃቱም በገበያ ቦታ ላይ ሳይሆን ኢላማ ያደረገው የአማጺውን ኃይሎች ላይ መሆኑን በመግለጽ ክሱን ውድቅ አድርጎታል።

ሔርኩለስ ሲ-130 የተባለው የማጓጓዣ አውሮፕላን ወድቆበታል ከተባለ ስፍራ የአውሮፕላኑ ስብርባሪ ነው ተባለ ምስልን የሚያሳይ በትግራይ አማጺያን ከቀናት በፊት ሲጋራ ነበር። ቢቢሲም የአውሮፕላኑን ስብርባሪ የያዙ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን የመረመረ ሲሆን፤ በቪዲዮው ላይ የሚነጋገሩ ሰዎች እንደሚሉት ቦታው ከመቀለ ደቡብ ምዕራብ 25 ኪሎ ሜትሮችን ርቃ የምትገኘው አዲ ቃአላ እንደሆነች ያመለክታሉ።

ህወሓት ኃይሎቹ ከመንግሥት ሠራዊት ጋር በሚያደርጉት ፀረ ማጥቃት ዘመቻ ኃይሎቹ አውሮፕላኑን በፀረ አውሮፕላን መትተው እንደጣሉ የገለጸ ቢሆንም ጦር ኃይሉ ግን ለአውሮፕላኑ መውደቅ ምክንያቱ ቴክኒካዊ ችግር መሆኑን በመጥቀስ የአማጺያኑን ምክንያት ውድቅ አድርጎታል። ነገር ግን በአውሮፕላኑ ውስጥ ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ የተገለጸ ነገር የለም።

በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ሁሉም ኃይሎች በጅምላ ግድያና በሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየተከሰሱ ባሉበት ጊዜ በክልሉ ውጊያ መልሶ እንዳየገረሽ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከፍ ያለ ስጋትን ፈጥሯል። ከወራት በፊት ግጭት በተቀሰቀሰበት ሰሜናዊ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ውስጥ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በአማጺያን መካከል ከባድ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት የወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

እራሱን የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ የሚጠራው ኃይል በርካታ የክልሉን ከተሞችን መያዙን የገለጸ ሲሆን፣ የአይን እማኞችም ተዋጊዎቹ በአካባቢያቸው ሲንቀሳቀሱ ማየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት ግን ቡድኑ አገኘሁ ያለውን ድል ሐሰተኛ ዜና ሲል አጣጥሎታል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ የሆኑት ኮሎኔል ጌትነት አዳነም ከባድ ውጊያ እንደነበረ አረጋግጠው፤ የተካሄደው ዘመቻ የአማጺውን ቡድን መሪዎች ለመያዝ ነው ብለዋል። ቃል አቀባዩ ጨምረውም አማጺያኑ ከተሞችን፣ የጦር መሳሪያዎችን ወይም ወታደሮችን ማርከናል ያሉትን ሐሰት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

በባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ትግራይ ውስጥ በሚገኘው የኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ መንግሥት ከኤርትራ ወታደሮች ጋር በመሆን በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ፣ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የነበረውን ህወሓት ከስልጣኑ አስወግዶ አሸናፊ መሆኑን ማወጁ ይታወሳል።

ከወታደራዊ ግጭቱ ቀደም ብሎ ህወሓት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያካሂዱት የፖለቲካ ለውጥ አንጻር ከፍተኛ አለመግባባት ውስጥ ገብቶ የነበረ ሲሆን በሰሜን ዕዝ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ለግጭቱ መጀመር ምክንያት ሆኗል።

ከስምንት ወራት በፊት በተቀሰቀሰው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ሚሊዮኖች ደግሞ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን የረድኤት ድርጅቶች ሪፖርት ያመለክታል።

ጦርነቱን ተከትሎ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች የምግብ እርዳታን ለመጠበቅ የተገደዱ ሲሆን ከ350,000 ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ በረሃብ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት ባለፈው ሳምንት ገልጾ ነበር።

 

ምንጭ – ቢቢሲ
selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *