ከጥቂት ወራት በፊት ጥቃትን ያስተናገደችው አጣዬ ከተማ በተቃጠሉና በፈራረሱ ቤቶች ተሞልታለች።
በአንድ ወቅት የንግድ መናኸሪያ የነበረችውና በድምቀቷ የምትታወቀው ከተማ አሁን ያለችበት ሁኔታ ከጉዳቷ እንዳላገገመች መስካሪ ነው። በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ህይወታቸው ተቀጥፏል፤ በርካቶችም ከቤታቸውና ከመንደራቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል። በርካታ ከተሞች ኢትዮጵያ ላደረገችው ስድስተኛ ብሔራዊ ምርጫ ሽር ጉድ ሲሉ የነበሩ ቢሆንም በፀጥታ ችግር ምክንያት የዚህ ተቋዳሽ ያልሆነችው አጣዬ ምርጫው ከተራዘመባቸው ስፍራዎች መካከል ናት።
የቢቢሲ አፍሪካ ዘጋቢ ካትሪን ቢያሩሃንጋ ከሰሞኑ ወደ አጣዬ ሄዳ የአካባቢውን ነዋሪዎች ያሉበትን ሁኔታ ዳስሳለች፤ ስላልሻረው ህመማቸውም ነግረዋታል። በአጣዬ ከተማ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ለመገንባት ዓመታትን፣ በርካታ ትውልድን ያስቆጠሩ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ተቃጥለዋል። ከተማዋም በቀናት ውስጥ በሚያስደነግጥ ሁኔታ ወድማለች። የአካባቢው ነዋሪዎችም ከጉዳታቸው አላገገሙም።
ወደ ከተማው ገና ሲገቡ የሚታዩ ህንፃዎች ፈራርሰዋል፣ ተቃጥለዋል ወይም ተዘርፈው ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ህይወትን እንደገና ለመቀጠል ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። የ34 ዓመቱ ጁዋር መሐመድ በትንሿ ሱቁ ውስጥ ሻይ ወደመሸጡ ተመልሷል። ከቆርቆሮ የተሰራችው ትንሿ ሱቁ በሚያዝያ ወር በደረሰባት ቃጠሎ ምክንያት ቀለሟ ተቀይሯል።
ይህች ትንሽ ሱቅ ሚያዝያ ወር ላይ በደረሰው ጥቃት ቃጠሎ ደርሶባት የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅትም ሱቁን በተወሰነ በኩል መልሶ ጠጋግኖ እየሰራባት ነው ያለው። “ሱቃችን ሲቃጠል በሰዓቱ እዚህ ነበርን። እሳቱ የጀመረው የሆነ ስፍራ ነው እየተያያዘም ወደኛ ደረሰ። እኛ ጋር ሲደርስ ከቧንቧው እየቀዳን በውሃ የማጥፋት ሙከራ አድርገን ነበር። “እሳቱን ለማጥፋት ብንሞክርም ከአቅማችን በላይ ሆነ። በጣም እየተያያዘ ሄደ። ላሜራው በሚግልበት ጊዜ እኛንም አላስጠጋን አለ። እናም አይናችን እያየ ሱቃችን ወደመ” ይላል።
በአጣዬ ከሚያዝያ 6/2013 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በከባድ መሳሪያ ታግዞ በተፈጸመው ጥቃት በርካታ ሰዎች ሞተዋል፣ ንብረት ወድሟል እንዲሁም ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አስታውቆ ነበር።
ከጥቃቱ ቀደም ባሉት ተከታታይ ቀናትም እንዲሁ በአጣዬ ዙሪያ ባሉት በማጀቴ፣ ቆሪና ሌሎችም አካባቢዎች በተደራጁና በከባድ ጦር መሳሪያ በታገዙ ታጣቂዎች በማጀቴ በርካታ ነዋሪዎች መገደላቸውን፣ በካራ ቆሬ የጸጥታ ኃይሎች መቁሰላቸውንና በርካታ ነዋሪዎች አካባቢውን ጥለው መሰደዳቸውን በወቅቱ ኢሰመጉ ባወጣው መግለጫ ተጠቅሷል።
ከዚህም በተጨማሪ አጣዬ፣ ቆሪሜዳ፣ ዙጢ፣ ካራቆሬ የተባሉ ከተሞች በከፍተኛ ሁኔታ እንደወደሙ ጉባኤው መረጃዎችን ዋቢ አድርጎ “የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትን በማስቆም አገርን እንታደግ” በሚል ሚያዝያ 13/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው ማስፈሩ ይታወሳል። በአጣዬ የተፈጠረው ሁኔታ በአገሪቱ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ከፍተኛ እንዲሁም መጠነኛ በርካታ ጥቃቶችና የብሔር ግጭቶች ውስጥ አንዱ ነው።
በአጣዬ ጥቃት የደረሰባቸውና መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ብቻ አይደለም። የአጣዬ ሆስፒታልም የጥቃቱ ኢላማ ከሆኑት ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ሆስፒታሉ በቃጠሎው ባዶውን ቀርቷል ማለት ይቻላል። በቀረው ክፍል ውስጥ መስታወቶች ተሰባብረው፣ ሚስማሮችና አመድ ወለሉ ላይ ይታያል። ጣራው በቃጠሎው ወድሟል። ይህ ጥቃት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል።
በዚህም ጥቃት ምክንያት በርካቶች ከቤታቸውና ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች ከአጣዬ ወጣ ብላ በምትገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥም ተጠልለው ይገኛሉ። በአገሪቱ ውስጥ በጦርነትና በግጭት ከተፈናቀሉ ሚሊዮኖች መካከል እነዚህም ተጨማሪ ሆነዋል።
ከነዚህም መካከል ፋጡማ ሁሴን አንዷ ናቸው። በተተኮሰባት ጥይት የተገደለችውን የ15 ዓመቷ ልጃቸው የሶፊያ ሐዘን አሁንም ሰቅዞ እንደያዛቸው ነው፤ ሃዘናቸው ጥልቅ ነው። “በድህነቴ ወጥቼ ወርጄ ለፍቼ ያስተማርኳትን ልጄን ተነጠቅኩኝ። እንዲህ አይነት ነገር ከዬት እንደመጣ አናውቀውም። እኛ ሰርቶ መብላት፣ ቸርችረን መኖርና ልጆቻችንን ማሳደግ እንጂ ምንም አላደረግንም” ይላሉ።

ምንም እንኳን በርካቶች ከተማዋን ለቀው ቢፈናቀሉም እንደ አህመድ ሁሴን ያሉ ጥቂት ነዋሪዎች አሁንም በከተማዋ አሉ። ከተማዋ በፀጥታ ችግር ምክንያት ምርጫ ካልተደረገባቸው ስፍራዎች መካከል አንዷ ናት፤ ይህም ሁኔታ በርካቶችን በተደራረበ መልኩ የአቅመ ቢስነት ስሜት አሳድሮባቸዋል። በንግድ ሥራ የሚተዳደረው አህመድ በምርጫው ባለመሳተፉ የተሰማውን የቁጭት ስሜትም ለቢቢሲዋ ዘጋቢ እንዲህ አጋርቷታል።
“በህይወት ያለን ያህል ስሜት አይሰማንም። ያጋጠመን ሐዘን እንዳለ ሆኖ በምርጫው ባለመሳተፋችን የበለጠ ሐዘናችንን ተደራራቢ ያደርገዋል። መላው አገሪቱ ሕዝብ በምርጫ ሲሳተፍ የእኛ ቀበሌ ባለመምረጣችን ተበሳጭቻለሁ” ብሏል። በአጣዬም ሆነ በሌሎች ግጭቶች ባሉባቸው ቦታዎች የፀጥታው ሁኔታው ስጋት ቢሆንም በበርካታ ቦታዎች ምርጫው በተያዘለት ቀን እንዲካሄድ ተወስኗል።
ሕዝባዊ ተቃውሞን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የመጀመሪያ ምርጫቸውን አካሂደዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህ ምርጫ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጡት ነገር ነው። አገሪቱን በአንድነት ለማስቀጠልና ሕጋዊ ተቀባይነትም ለማግኘት ምርጫውን ማሸነፍ ይኖርባቸዋል።
በፀጥታ ስጋቶችና በሎጂስቲክ ችግር በተወሰነ መልኩ የተሸፈነው ምርጫ አገሪቱን ወደ ትክክለኛ መንገድ ይወስዳት ይሆን? መንግሥት ምርጫውን ማካሄድ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ያምናል። ከአጣዬ የሦስት ሰዓት ርቀት ባላት ደብረ ብርሐን ከተማ ያለው መንፈስ የተለየ ነው። ለምርጫው ዝግጅት ሽር ጉድ እያለች ስለነበር ደስታውም ይስተጋባል።
ነገር ግን በዚህም ውስጥ ቢሆን የብሔር ጉዳዮች ውይይትና ብሔሩም ራሱን በበለጠ ሊያስተዳድር ይገባዋል በሚሉ አንዳንድ ቡድኖችም ጫና ይሰማል። የብልጽግና ዕጩ ተወዳዳሪ የሆነችው የ35 ዓመቷ ገነት ቤተ ጌራዎርቅ በበኩሏ ለቢቢሲ ይህንን ብላለች። “ቤታችን ትልቋ አገራችን ኢትዮጵያ ናት። በዚያው ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ደግሞ ሁሉንም ባከበረና ባካተተ መልኩ መከበር መቻል አለባቸው። ማንነታቸው መከበር አለበት። ስለዚህ ሕብረ ብሔራዊ ለሆነ አንድነት መስራት አለብን። አንድነታችንን ማጠናከር አለብን” ብላለች።
ኢትዮጵያ ለዓመታት ያህል ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የግዛት ይገባኛል ጥያቄና የሀብት ክፍፍል ጉዳይ ራስ ምታት ሆኖባታል። ቀላልም መፍትሔ ያለው አይመስልም። በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከልም በሚነሱ ግጭቶችም ሆነ በሚደርሱ ጥቃቶች እንደ ፋጡማ ሁሴን ያሉ ግለሰቦች የሚወዱትን ማጣት ብቻ አይደለም ለዓመታት ያህል የለፉበት ንብረታቸው ወድሟል፤ ከአካባቢያቸውና ከስፍራቸውም ተፈናቅለዋል።
“እንደ ቤት ያለ ምን አለ። የተወለድንበትና ያደግንበት፤ ልጆቻችንንም ወልደን ያሳደግንበት። ማንስ ይቀበለናል አሁን” ትላለች። ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የኖቤል ሽልማት አሸነፉ። ወጣቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ባላቸው የለውጥ መንፈስ፣ ሙስናን ለመዋጋት እንዲሁም የፖለቲካ እስረኞችን በመፍታት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ሙገሳን አተረፉ።
በአሁኑ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርብ ጊዜ ታሪክ ታይቶ በማያውቅ በሚባል ሁኔታ የተከፋፈለች አገርን እየመሩ ይገኛሉ። የብሔር ግጭት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን አፈናቅሏል። በከፍተኛ ጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ረሃብ ተጋርጦባታል። ምርጫውስ ለብሔር ግጭቱም ሆነ አገሪቱ ለተጋረጠባት ችግሮች መፍትሄ ያበጅለት ይሆን?
ምንጭ – ቢቢሲ