ትግራይ ውስጥ በሚገኝ አንድ የገበያ ስፍራ በተፈፀመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል እንዲሁም ቆስለዋል የሚለውን ሪፖርት ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካ ጥቃቱን አውግዘዋል።

የአየር ጥቃቱ የተፈፀመው ከመቀለ 25 ኪሎሜትር ርቀት በምትገኘው ቶጎጋ በምትባለው ከተማ ውስጥ እዳጋ ሰሉስ በምትባል የገበያ ስፍራ መሆኑን ቢቢሲ ከአይን እማኞች ተረድቷል። በገበያ ስፍራ በደረሰው የአየር ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 60 እንዲሁም የተጎዱ ደግሞ ከአርባ በላይ መሆናቸውን በአይደር ሆስፒታል የሚሰራ ዶክተር ለቢቢሲ ተናግሯል።

የተጎጂዎች ቁጥር ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል እየተነገረ ነው። ዶክተሮች የሁለት ዓመት ህፃንን ጨምሮ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ህሙማን እያከሙ እንደሆነም አስረድተዋል። በአይደር ሆስፒታል እየታከመ ያለና በጥቃቱ ጉዳት የደረሰበት አንድ የ16 ዓመት ልጅ ለቢቢሲ በርካታ ሰዎች መሬት ላይ ወድቀው ማየቱን ተናግሯል።

በአየር ጥቃቱም አንድ የሚያውቀው ሰው እንደተገደለም ገልጿል። የአካባቢው ዓይን እማኞች ጥቃቱን የፈፀመው የኢትዮጵያ አየር ኃይል መሆኑን ለቢቢሲ ቢናገሩም የኢትዮጵያ ጦር በበኩሉ ንፁሃን ዜጎችን ኢላማ እንዳላደረገና ጥቃቱ ያነጣጠረው “ሽብርተኞች” ላይ ነው ብሏል።

የአውሮፓ ብረትና የአሜሪካ መግለጫ ይዘት

ጥቃቱን ተከትሎ በትናንትናው ዕለት የአውሮፓ ሕብረት ባወጣው መግለጫ ንፁሃንን ሆን ብሎ ኢላማ ያደረገ ጥቃት እንደሚያወግዝ ገልጿል። የንፁሃን ዜጎች ጥቃት በማንኛውም መንገድ ምክንያት ሊሰጠው የሚገባ አይደለም ከዓለም አቀፍ ሕጎችም ጋር ይጣረሳል ብሏል።

በክልሉ የሚፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ጋር የተያዙ ናቸው የሚሉ መከራከሪያዎች ሊቀርብባቸው አይገባም በማለት መግለጫው አስፍሯል። የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የአውሮፓ ሕብረት፣ አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን ከትግራይ ጋር ተያይዞ የሚወጡ መግለጫዎች እንደ ጣልቃ ገብነት የሚያዩት ሲሆን የአገሪቱን ሉዓላዊነት የሚፃረር ተግባርም ነው በማለትም ይኮንናሉ።

የአሜሪካ መንግሥትም በበኩሉ በጥቃቱ በርካታ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል እንዲሁም ተጎድተዋል የሚለው ሪፖርት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳሰበው ገልፆ ጥቃቱን አውግዟል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት በበኩላቸው “በገበያ ቦታ ላይ ፈጽሞ የአየር ጥቃት አልፈጸምንም። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሠራዊቱ ኢላማውን በትክክል የመምታት አቅም አለው” ብለዋል።

ጨምረውም “የአየር ጥቃቶችን ፈጽመናል ነገር ግን በተመረጡ ውስን ኢላማዎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። ስለዚህ በገበያ ስፍራ ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የተባለው ሙሉ ለሙሉ ውሸት ነው” ሲሉ ክሱን ውድቅ አድርገውታል። ከዚህም በተጨማሪ የህክምና ባለሙያዎች ለሮይተርስ እንደተናገሩት ጥቃት የደረሰበት ቦታ ላይ ደርሰው ለተጠቂዎች እርዳታ ማድረግ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንደከለከሏቸው ነው።

የህክምና ባለሙያዎች ለጥቃቱ ተጎጂዎች እርዳታ እንዳያደርጉ በፀጥታ ኃይሎች መታገዳቸውንም ከታማኝ ሪፖርቶች አንደሰማ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ በመግለጫው አስፍሯል። “አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልጋቸውን ተጠቂዎች መከልከል ጭካኔና በፍፁም ተቀባይነት የሌለው ነው” ብሏል።

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለነዚህ ተጠቂዎች አስቸኳይና ያልተገደበ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ ማድረግ አለባቸው ሲልም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ መልዕክቱን አስተላልፏል። የአውሮፓ ሕብረትም የህክምና እርዳታ የሚሰጡ አምቡላንሶች ታግደዋል የሚለው ሪፖርት ከተረጋገጠ የዓለም አቀፉ ሕግ የሚያዘውን የጄኔቫ ኮንቬንሸንን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጥስ እንደሆነም አስፍሯል።

ጥቃቱን በክልሉ እስካሁን ድረስ የሚፈፀሙ ረሃብንና ወሲባዊ ጥቃትን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል የሚሉ ክሶችና ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ ሕግና መብቶች ከሚጥሱ እንደ አንዱ ይቆጠራል ብሎታል የአውሮፓ ሕብረት በመግለጫው። በትግራይ እየተፈፀመ ያለው አሳሳቢ ነው ያለው የአውሮፓ ሕብረት መግለጫ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ነቅቶ ወደ ተግባር የሚገባበት ወቅትም ነው ብሏል።

በአይደር ሆስፒታል ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ድርጅት የቆሰሉ ሰዎችን ከአካባቢው አውጥቶ ወደ ህክምና ማዕከላት እንደወሰደም ገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአየር ጥቃቱ ላይ ኢትዮጵያ ምርመራ እንድትከፍት ጥሪ አድርጓል። በተመሳሳይም በጥቃቱ ላይ አስቸኳይና ነፃ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ ያቀረበው የአሜሪካ መንግሥት በጥቃቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትም ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።

የአሜሪካ መንግሥትና የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ አስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ፣ ያልተገደበ እርዳታና ንፁሃን ዜጎች እንዲጠበቁ በዚህኛው መግለጫቸው አስፍረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በጎረቤት አገር ኤርትራ በመታገዝ በወቅቱ የክልሉ አስተዳዳሪ የነበረውን ህወሓትን ከስልጣን ለማስወገድ ወታደራዊ ዘመቻ አካሂዶ፤ በወሩም ውስጥ ዘመቻው በድል እንደተጠናቀቀ የፌደራል መንግሥቱ አውጆ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሚያደርጓቸው የፖለቲካ ማሻሻያዎች ጋር ተያይዞ ከህወሓት ጋር ያለው ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ የሻከረ ሲሆን ግጭቱንም ያቀጣጠለው የህወሓት የፌደራል መከላከያ ዕዝን መቆጣጠሩን ተከትሎ ነው። ህወሓት በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ጋር በመጣመር የትግራይ መከላከያ ኃይል የሚል አማፂ ቡድን መስርቷል። ይህ ቡድን በቅርቡ በርካታ ግዛቶችን ተቆጣጥሬያለሁ ቢልም የኢትዮጵያ መንግሥት አስተባብሏል።

ስምንት ወራት ባስቆጠረው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ በሚሊዮኖችም ተፈናቅለዋል። ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ድምፃቸውን በትውልድ ስፍራቸው ድምፃቸውን ከሰጡ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል መቼ እንደሚወጡ በቢቢሲ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ “ገፍተን አናስወጣቸውም በሰላም ነው እንዲወጡ የምንፈልገው። ይሄም እርግጠኛ ነኝ ይሆናል” ብለዋል።

“ከኤርትራ ጋር ጉዳዩን በሰላም ለመቋጨት አብረን እየሰራን ነው” በማለትም አክለዋል። የኤርትራ ወታደሮች ጭፍጨፋዎችን፣ የጅምላ ወሲባዊ ጥቃቶችን በመፈፀምና ሰብዓዊ እርዳታ ይከለክላሉ ቢባልም ኤርትራ ይህንን አትቀበለውም።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *