በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ውስጥ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት በመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ አስር ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።
የምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ዋቁማ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቃቱ በዞኑ ሜታ ወልቂጤ ወረዳ ሎያ ጎዳኔ ቀበሌ ውስጥ ረቡዕ ሰኔ 09/2013 ዓ.ም አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ ነው የተፈጸመው።
አቶ ዲሪርሳ በታጣቂዎቹ ጥቃት የተገደሉት የፌደራልና የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ባለሙያ የሆኑ ዘጠኝ ሰዎች እና የቀበሌው ነዋሪ የሆነች አንዲት ሴት መሆናቸውን ገልጸዋል። ጥቃቱን በተመለከተ ቢቢሲ ያናገራቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ተገኝ በበኩላቸው የባለሥልጣኑ ባልደረቦች የሆኑ አስር ሰዎች በታጣቂዎቹ በተተኮሰ ጥይት መገደላቸው አረጋግጠዋል።
አቶ ሃብታሙ “ችግሩ ተከስቷል፤ ገና ዝርዝር መረጃ የለንም። ነገር ግን ጥቃቱ የተፈጸመው ምዕራብ ሸዋ አካባቢ፣ ሜታ ወልቂጤ በተባለ ቦታ ላይ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ በስልክ ገለጸዋል። ቢቢሲ ከአንድ የባለሥልጣኑ ባልደረባ ለመረዳት እንደቻለው ሠራተኞቹ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የዓለም ገና ዲስትሪክት ባልደረቦች ሲሆኑ የተበላሸ መንገድ ጠግነው አመሻሽ ላይ ሲመለሱ መኪናቸው በታጣቂዎች እንዲቆም መደረጉን ተናግረዋል።
በታጣቂዎቹ ከተገደሉት ሰዎች መካከል መሃንዲስ፣ ሾፌር፣ የቡል ዶዘር ቴክኒሺያንና በተለያዩ ሙያዎች የመንገድ ግባታ ባለሙያዎች መሆናቸውን የባለሥልጣኑ ባልደረባ ገልጸዋል። ጨምረውም በጥቃቱ ወቅት አንድ ሰው ለማምለጥ ባደረገው ሙከራ በአቅራቢያው ወዳለ ገደል ዘሎ መግባቱን እና በህይወት ስለመትረፉ የታወቀ ነገር እንደሌለ ስማቸው እንደጠቀስ ያልፈለጉት ግለሰብ አስረድተዋል።
የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ዲሪርሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደግሞ ጥቃቱ በተፈጸመበት መኪና ውስጥ 11 የመንገድ ሥራ ባለሙያዎች ሲጓዙ የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በሕይወት የተረፉ መኖራቸውንም ተናግረዋል። ጨምረውም “ሠራተኞቹ በዞኑ መኡርጋ በሚባል ወንዝ አካባቢ ያለ መንገድ ሥራ ላይ ውለው ጎሮ ወደሚባል ቦታ እየሄዱ ሳለ ነው በታጣቂዎቹ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉት” ብለዋል።
በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች አስከሬን አዲስ አበባ ወደሚገኘው ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መላኩንና ለቤተሰቦቻቸው መርዶ መነገሩን ጠቅሰው አስከሬናቸው ዛሬ አርብ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። አቶ ዲሪርሳ ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው አስራ አንድ የመንገድ ግንባታ ባለሙያዎች መካከል ከግድያው ያመለጡት ሁለቱ “በአካላቸው ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፤ ደህና ናቸው” ብለዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪው ጥቃቱን የፈጸመው “ኦነግ-ሸኔ” የተባለው ቡድን እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፤ ስለተፈጸመው ግድያ ከቡድኑ በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም። ይህ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ተለይቶ የወጣውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ቡድን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተሰየመ ሲሆን፤ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ከሚፈጸሙ ግድያዎችና ጥቃቶች ጋር ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል።
ምንጭ – ቢቢሲ