ፌስቡክ ከኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ጋር ግንኙነት አላቸው ያላቸውን ሐሰተኛና አሳሳች ይዘቶችን የሚያወጡ በርካታ ተያያዥ አካውንቶችን ማገዱን አስታወቀ።
ይህ አካውንቶቹን የማገድ የፌስቡክ ውሳኔ የተገለጸው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ከቀናት በኋላ ለማካሄድ እየተዘጋጀት ባለችበት ጊዜ ነው። ፌስቡክ እንዳለው እነዚህ በደርዘኖች የሚቆጠሩት የታገዱ የማኅበራዊ ትስስር መድረኩ ተገልጋዮች ከኢትዮጵያ የሆኑ አካውንቶች፣ ገጾች እና የፌስቡክ ቡድኖች ሲሆኑ እነሱም ትስስር ያላቸውና በአገር ውስጥ ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው።
አካውንቶቹ አላስፈላጊ በርካታ ተደጋጋሚ መልዕክቶችና አሳሳች ይዘቶችን የሚያወጡ ሲሆን፤ በተጨማሪም ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ግጭት ውስጥ የገባውን ህወሓትንና ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንዲሁም ቡድኖችን የሚተቹ ጽሆፎችን ያወጣሉ ብሏል። ግዙፉ የማኅበራዊ ሚዲያ የትስስር መድረክ በወሰደው እርምጃ 65 የፌስቡክ አካውንቶች፣ 52 ገጾችን፣ 27 ቡድኖችን እና 32 የኢንስታግራም አካውንቶች “ደንቦቻችንን በመተላለፋቸው እንዲታገዱ” ማድረጉን ገልጿል።
እነዚህ ተያያዥነት ያላቸው አካውንቶች መነሻቸውና ትኩረታቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎችን ኢላማ አድርገው ነበረ ብሏል። ፌስቡክ እንዳብራራው እነዚህ ሐሰተኛ አካውንቶችና ተጠቃሚዎቻቸው ከኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደኅንንት ኤጀንሲ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ደርሸቤታለሁ ብሏል። ፌስቡክ በተጠቀሱት አካውንቶች ላይ በገለልተኛ ወገን ባደረገው ምርመራ በቅርቡ ያወጧቸው የተወሰኑ ይዘቶች ሐሰተኛ ከመሆናቸው በተጨማሪ አሳሳች ናቸው ብሏል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም አንዳንዶቹ አካውንቶች በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ለበርካታ ጊዜ በተደጋጋሚ የስም ለውጥ ያደረጉ ሲሆን በተጨማሪም ተመሳሳይ መልዕክቶችን በተከታታይ ግን በተለያዩ ገጾች ላይ በአንድ ጊዜ ያሰራጫሉ ብሏል። እነዚህ አካውንቶች በቀዳሚነት በአማርኛ ቋንቋ በመጠቀም ኢትዮጵያን የተመለከቱ ዜናና ወቅታዊ መረጃዎችን ያወጣሉ ብሏል።
በተቀናጀ ሁኔታ የሚንቀሳቀሱት እነዚህን አካውንቶች የሚያንቀሳቅሱት ሰዎች ምንም እንኳን ማንነታቸውንና ትስስራቸውን ለመደበቅ ቢሞክሩም ፌስቡክ አደረግሁት ባለው ምርመራ ግለሰቦቹ ከመረጃ መረብ ደኅንንት ኤጀንሲ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኤጀንሲው መስራቾችና መሪዎች መካከል አንዱ የነበሩ ሲሆን ድርጅቱ በአገሪቱ ውስጥ ላለው የመረጃ መረብ ደኅንነት መጠበቅ የሚሰራ ነው።
ኢትዮጵያ በመጪው ሰኞ ብሔራዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጀች ባለችበት ጊዜ ነው ፌስቡክ ይህንን እርምጃ መውሰዱን ያስታወቀው። የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንን የፌስቡክ የእግድ ተግባር አስመልክቶ የሰጠው ምላሽ የለም።
ፌስቡክ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ከምርጫው ጋር ተያይዞ ሐተሰኛና ጥላቻን ያዘሉ መልዕክቶች በማኅበራዊ ሚዲያ መድረኩ በኩል እንዳይ ተላለፉ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉ ይታወሳል። በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ተጠቃሚ ካላቸው የማኅበራዊ ትስስር መድረኮች መካከል ፌስቡክ ከቀዳሚዎቹ ውስጥ እንደሆነ ከዚህ በፊት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።