ፌስቡክን የመሳሰሉ ማህበራዊ ሚዲያዎች ለታፈኑት ድምፅ ሆነዋል፤ በርካቶች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ሳያፈሱ መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያስተላልፉ አስችሏቸዋል።

ለዘመናት በጋዜጦች፣ በቴሌቪዥን፣ በሬድዮዎች በበላይነት ተይዞ የነበረውንም የመረጃም ሆነ የዜና ምንጭነት ቀይረውታል። በግለሰብ ደረጃ የተለያዩ ዜናና መረጃዎችን በጽሑፍ፣ በምስልና በቪዲዮ ለበርካታ ሰዎች ለማድረስ ዕድልን ፈጥረዋል። በዚህም መረጃዎች በቀላሉና በአጭር ጊዜ አገራትን ብቻ ሳይሆን አህጉራትን አቆራርጠው ከበርካቶች ዘንድ ይደርሳሉ።

ነገር ግን በዚህ ሂደት ይህንን የግንኙነት ዘዴ ለዕውቀትና ለበርካታ መልካም ነገሮች ከሚያውሉ ሰዎች ባሻገር ሐሰተኛ ወሬን፣ ጥላቻን፣ ጥርጣሬና ፍርሃትን እንዲሁም ለሥነ ምግባር ተቃራኒና ለሰዎች ደኅንነት አደገኛ የሆኑ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ቡድኖችና ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው።

ይህንንም ለመከላከል የማኅበራዊ መገናኛ መድረኮቹ ባለቤት የሆኑት ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ የመገናኛ ዘዴዎቻቸውን ከእንዲህ አይነቶቹ መልዕክቶች በተቻለ መጠን ነጻ ለማድረግ የአጠቃቀም ደንቦችን በማውጣት ቁጥጥር እያደረጉ ነው። በዚህም ሳቢያ ለሰዎች ደኅንነት ጎጂ የሆኑና ሐሰተኛ ወሬዎችን በሚያሰራጩ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎች ለመውሰድ እየተገደዱ ነው።

ፌስቡክ

ፌስቡክ ከጥቂት ወራቶች በፊት የጥላቻ ንግግር ወይንም ሐሰተኛ ንግግሮች ናቸው ያላቸውን 22 ሚሊዮን በላይ መረጃዎችን አጥፍቷል። ድርጅቱም ይህንን የሚያደርገው በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ባቋቋማቸው ማዕከላት ነው። ይህንንም አማርኛንና ኦሮምኛን ጨምሮ ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ቋንቋዎች ላይ ክትትል የሚደረገው ኬንያ ባለው ቢሮ በኩል ነው።

የ’ዊ አር ሶሻል’ እና ፌስቡክ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ በወር አንዴ ፌስቡክን የሚጠቀሙት ሰዎች ቁጥር ከስድስት ሚሊዮን በላይ ነው። የፌስቡክ የምስራቅ አፍሪካ የማህበራዊ ጉዳዮች ፖሊሲ ኃላፊ የሆነችው ሜርሲ ኢንዴጊዋ “ለፌስቡክ ኢትዮጵያ የማሕበራዊ ሚዲያ ገበያ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላት አገር ናት” ትላለች።

ፌስቡክ በአካባቢው ብዙ ስራዎች እየሰራ ነው የምትለው ሜርሲ፣ ኢትዮጵያ የሚገኙት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች አብዛኞቻቸው ዜናንና ሌሎች ክስተቶችን ለማግኘት ወደ ገጻቸው እንደሚመጡ ትናገራለች። “በተጨማሪም በኢትዮጵያ የእኛ ትኩረት ሰዎች በኛ ፕላትፎርም (መድረክ) እንዴት ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ፣ ከዚያን በኋላ ደግሞ ኢንተርኔት በማይጠቀሙበት ጊዜ በሚያሳዩት ባህሪ ላይም ትኩረት እንሰጣለን” ብላለች።

ይህም ማለት የጥላቻ ንግግር፣ የሐሰተኛ መረጃ እና ሌሎች ይዘቶችን ለመቆጣጠር እንዲሁም መፍትሔ ለመስጠት እየሰሩ መሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ወቅት ተናግራለች። የፌስቡክ ማሕበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች፣ በተለይ ደግሞ ከኢትዮጵያ የሚጠቀሙ ግለሰቦች፣ በተደጋጋሚ የሚለጥፏቸው መረጃዎች መሰረዙን በመጥቀስ ቅሬታ ያቀርባሉ።

የተወሰኑ ግለሰቦች ፌስቡክ የአንድ አካል መሳሪያ ነው በማለት ሲተቹ፣ ሌሎች ደግሞ በማንነታቸው ምክንያት ትኩረት ውስጥ እንደገቡ ያምናሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ እንዲሁም የአንድ ቋንቋ ቡድን አንድ ላይ በመደራጀት ሌሎች ላይ ትኩረት ሲያደርጉ ተስተውሏል።

ፌስቡክ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የሐሰተኛ መረጃዎች፣ የጥላቻ ንግግሮች፣ እንዲሁም በማንነት ላይ ያተኮሩ መረጃዎች በሚለጠፉበት ወቅት እንዴት ይቆጣጠራል?

በድርጅቱ የይዘት ጉዳዮች ኃላፊ (ኮንቴንት ፕሪንሲፕል) ኃላፊ የሆነችው ፈድዛይ ማድዚንጊራ አንድ መረጃ ከፌስቡክ ላይ የሚሰረዘው የተቀመጠውን የማህበረሰብ መስፈርት (ኮሚውኒቲ ስታንዳርድ) ተላልፎ ሲገኝ ነው በማለት ታስረዳለች። ይህም ፖሊስ በፌስቡክ ገጽ ላይ በግልጽ የሚገኝ በመሆኑ ማንኛውም ሰው አግኝቶ ማንበብ ይችላል የምትለው ፈድዛይ፣ በዚህ መስፈርት ስር በድርጅቱ መተግበሪያ ላይ የሚፈቀዱ እና የማይፈቀዱ ነገሮች በግልጽ መቀመጣቸውን ታስታውሳለች።

“እነርሱም በ26 አበይት ርዕሶች ተከፋፍለው የሚገኙ ናቸው፣ ለዕይታ የሚረብሹ (ግራፊክ ኮንቴንት) የሆኑ ምስሎች ከተለጠፈው ነገር ጋር ሲጋጩ እንዲሁም መልካም ያልሆነ ባህሪ፣ እስከ ጥላቻ ንግግር ድረስ በዝርዝር ይዟል። የፌስቡክ የጥላቻ ንግግር ፖሊሲ ዓላማ ሰዎች በማንነታቸው ምክንያት ትኩረት ተደርጎ የሚለጠፉ መረጃዎችን ማጥፋት ነው” ትላለች።

በተጨማሪም ሰዎች በማንነታቸው ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ የሚደርስባቸው ከሆነ በሚል ይህ ፖሊሲ ማስፈለጉን ታብራራለች። አንድ መረጃ ከፌስ ቡክ ላይ የሚሰረዝበት ቅድመ ሁኔታ ስታነሳ፣ “ለምሳሌ እኔ የዚምባብዌ ዜጋ ነኝ። እና አንድ መረጃ፣ እኔ ከዚምባብዌ ስለመጣሁ አልያም ጥቁር ስለሆንኩ፣ ወይንም ሴት በመሆኔ እኔ ላይ ትኩረት አድርጎ ያስፈራራኛል ወይንም የጥላቻ ንግግር ይለጥፋል ከሆነ ይህንን እናጠፋለን።”

ማንኛውም ሰው ማመልከት ይችላል

ማንኛውም የፌስቡክ ተጠቃሚ ስለ አንድ የፌስቡክ መረጃ ሪፖርት ማድረግ ወይንም ማመልከት ይችላል። “አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ይህንን ማድረግ እንደማንችል ነው የሚወስዱት” የምትለው ኃላፊዋ፣ አንድ መረጃን ብቻ የተመለከተ ጉዳይ ሪፖርት ማድረግ፣ የግለሰብ ወይንም ገጽን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሪፖርት ማድረግ እንደሚቻል ለቢቢሲ አስረድታለች።።

ይህንን ማድረግ የሚቻለው በቀኝ የሚገኙ ሶስት ነጥቦች ስር በመሄድ ነው። እነርሱ ሲነኩ ማመልከት ወደ ሚቻልባቸው ሂደቶች ይወስዳል። ከዚያ በዚህ ደረጃ ውስጥ አልፈው ሲጨርሱ ማመልከቻው ወደ ፌስቡክ ይደርሳል።ያ መረጃ የፌስቡክ የኮሙኒቲ ስታንደርድ ተላልፎ ሲገኝ፣ ይሰረዛል ማለት ነው። ያመለከተው ግለሰብ እንዲሰረዝ የጠየቀው መረጃ መሰረዙ መልዕክት ይደርሰዋል።

ፌስቡክ በመላው ዓለም ስራቸው ይህ የሆነ ሰዎች ‘ሪቪወርስ’ የተባለ ቡድን ያለው ሲሆን በዚህ ቡድን ስር 30 ሺህ ያህል ሰራተኞች ይገኛሉ። “ከእነዚህ ከ30ሺህ ሰዎች አንድ ሰው፣ አንድ መረጃ ጥያቄ ሲነሳበት ከኮሙኒቲ ስታንደርድ ፖሊሲ (ከማህበራዊ አደረጃጀት ፖሊሱ) ጋር ጎን ለጎን በማመሳከር ተላልፎ ከተገኘ ይሰረዛል” ትላለች ፈድዛይ ማድዚንጊራ።

ፌስቡክ እንደ ምስራቅ አፍሪካ ይህንን የሚቆጣጠር ቢሮ ናይሮቢ ውስጥ አለው። ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ስዋሂሊ፣ እንዲሁም ሶማልኛ ተናጋሪ የሆኑ ሰዎች ቀጥሮ እንደሚያሰራም አብራርተዋል።

ለመሰረዝ አንድ ማመልከቻ ብቻ በቂ ነው

በፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች የሚነሳው ሌላው ጉዳይ አንድ በፌስቡክ ላይ የሚለጠፍ መረጃ ማመልከቻ ባስገቡ ሰዎች ቁጥር ብዛት ነው ወይንስ ሕጉን ተላልፈው ስለሚገኙ ነው የሚሰረዘው የሚል ነው።

ፈድዛይ ማድዚንጊራ እንዲህ በማለት ትገልጻለች። ከዚህ ጉዳይ ጀርባ ያለው ነገር እንዲህ ነው በማለት አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ተከታዮቻቸውን ወይንም የፌስቡክ ማህበረሰባቸውን አንድ የፌስቡክን እሴት የማይተላለፍን ጽሑፍ እንዲሰረዝ እንዲያመለክቱ ጥሪ ያቀርባሉ። ከዚህም ጋር ተያይዞ አንዳንድ ጊዜ ብዙ ሪፖርቶች እናገኛለን። ይህም ደግሞ ውጤቱን አይቀይረውም። ይህንን ‘የኮሙኒቲ ስታንደርድ’ ተላልፎ የሚገኝ መረጃ ላይ አንድ ማመልከቻ ብቻ ነው የምንፈልገው በማለት ያስረዳሉ።

አንድ መረጃ የሚሰረዘው የድርጅቱን ኮሙኒቲ ስታንደርድ ስለሚተላለፍ ነው። ይህ ሳይሆን ሳይቀርና አንድ መረጃ በስህተት ቢጠፋ፣ ተጠቃሚዎቻችን ይህንን ውሳኔ ይግባኝ እንዲሉ እድል እንደሚሰጣቸው ጨምረው አስረድተዋል። የአንተ/ ወይንም የአንቺ መረጃ ተሰርዟል የሚል መልዕክት ይደርሳቸዋል። አይ እኔ የለጠፍኩት ነገር ትክክል ነው ብለው የሚቃወሙ ከሆነ ደግሞ በድጋሚ ማመልከቻ ማስገባት ይቻላል።

የአመልካቹ ማመልከቻ ከዚህ በፊት መረጃውን ያጠፋው የፌስቡክ ሰራተኛ ጋር ሳይሆን ለሌላ ሰራተኛ ይሰጣል። ይህም ሰው የፌስ ቡክ ፖሊሲንና የአመልካቹን ማመልከቻ ጎን ለጎን በማስተያየት ችግር ተፈጥሮ ከሆነ መረጃው ዳግም በፌስቡክ ላይ እንዲለጠፍ ያደረጋል ስትል ታብራራለች።