የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በቁም እስር ላይ ከአንድ ወር በላይ መቆየታቸው እንዳሳሰበው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገልጸ።

ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው አቶ ዳውድ ኢብሳ ምንም አይነት ክስ ሳይቀርብባቸው በቁም አስር ላይ የሚገኙት ከሚያዝያ 25/2013 ዓ.ም ጀምሮ ነው።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አንጋፋ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ሲሆን አቶ ዳውድ ኢንብሳም በሊቀመንበርነት ግንባሩን በስደት ለበርካታ ዓመታት ሲመሩ ቆይተው ከሁለት ዓመት በፊት ነበር ወደ አገር ቤት የተመለሱት። በአምንስቲ ኢንተርናሽናል በአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብት አጥኚ የሆኑት አቶ ፍሰሃ ለቢቢሲ እንደገለፁት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚያዚያ ወር ጀምሮ ነው በቁም እስር ላይ የሚገኙት።

ሊቀመንበሩ ከቤት መውጣት የተከለከሉት ፖሊስ ካለፍርድ ቤት ትዕዛዝ መኖሪያቸውን ፈትሾ ኮምፒውተሮችናን የሞባይል ስልኮችን ጨምሮ የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ተከትሎ እንደሆነ ተገልጿል። ከዚያ ቀን በኋላ ፖሊስ ማንም ሰው ከቤቱ እንዳይወጣና ወደ ቤቱም እንዳይገባ የከለከለ ሲሆን አሁን በቤቱ ውስጥ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች አልቀው ወይም እያለቁ ሊሆኑ ስለሚችሉ አቶ ዳውድ ያሉበት ሁኔታና ደኅንነታቸው አሳሳቢ መሆኑን አምነስቲ አመልክቷል።

እንደ አቶ ፍሰሃ ከሆነ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ይህንን መግለጫ ሲያወጣ፣ አቶ ዳውድ ከቤታቸው እንዳይወጡ ሲደረግ በስፍራው የነበሩ ሰዎችን እንዲሁም የፓርቲያቸው አመራሮችን በማናገር መሆኑን ገልፀው፣ በአሁኑ ወቅት በአቶ ዳውድ ዙሪያ የቤት ሠራተኛቸው ብቻ እንደምትገኝ ማጣራታቸውን ገልጸዋል። አስካሁን ባለሥልጣናት በኦነግ ሊቀመንበር ላይ ምንም አይነት ክስ ያላቀረቡ በመሆናቸው በአስቸኳይ ከቁም አስሩ ነጻ እንዲወጡ ጨምሮ ጠይቋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጉዳዩን በማስመልከት ለሠላማ ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ደብዳቤ የጻፈ ሲሆን፤ በዚህም የአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሕግ ውጪ በቁም አስር ላይ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸው እንዳሳሰበው አመልክቷል። የኦነግ ቃል አቀባይን ጠቅሶ አምነስቲ እንዳሰፈረው የአቶ ዳውድ እስር እንዲሁ የተከሰተ ሳይሆን ሌሎች የግንባሩ አባላትና መሪዎች ከሕግ ውጪ በመታሰራቸውእንዲሁም በአዲስ አበባና በሌሎች ቦታዎች የሚገኙ ጽህፈት ቤቶቻቸው በመዘጋታቸው በሚቀጥለው ሳምንት ከሚካሄደው ምርጫ መውጣቱን ጠቅሷል።

አምነስቲ እንዳለው ባለሥልጣናት ለአቶ ዳውድ ኢብሳ የቁም እስር የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካለማቅረባቸው በተጨማሪ ምክንያቱም ምን እንደሆነ አልተገለጸላቸውም። የአቶ ዳውድ ከሕግ ውጪ በተራዘመ የቁም እስር ላይ መሆናቸው በመንቀሳቀስና በመሰባሰብ ነጻነታቸው ላይ እቀባ እንደተጣለ ተገልጿል። አምነስቲ ጉዳዩን በማስመለከት ለሠላም ሚኒስተሯ ለወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በጻፈው ደብዳቤ ላይ ባለስልጣናት ኢትዮጵያ በተቀበለችው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ግዴታ መሠረት ሃሳብን የመግለጽና የመደራጀት መብትን እንዲያከብሩና እንዲጠብቁና ጠይቋል።

አምነስቲ መንግሥትን አቶ ዳውድ ኢብሳን በአስቸኳይ ከቁም አስሩ እንዲለቅ ወይም የፈጸሙት ጥፋት ካለና በቂ ማስረጃ ካለውም በተገቢው ሁኔታ ክስ እንዲመሰርት ጠይቋል። አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዚህ ቀደምም ለተወሰኑ ቀናት ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ በጸጥታ ኃይሎች ተከልክለው እንደነበረ መዘገቡ ይታወሳል። በጉዳዩ ላይ የመንግሥት አካላትን ምላሽ ለማግኘት አምንስቲ መሞከሩን የሚናገሩት አቶ ፍሰሃ፣ ምላሽ ማግኘት መቸገራቸውን አብራርተዋል።

አቶ ፍሰሃ አክለውም በርካታ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ እንደሚገኙ፣ ፍርድ ቤት ነጻ ያላቸውም ቢሆኑ እስካሁን ድረስ ታስረው እንዳሉ ገልጸዋል። ጨምረውም በአሁኑ ጊዜ የባልደራስ አመራር የሆኑት አቶ እስክንድር እንዲሁም በፖለቲካ ንቁ ታሳታፊ የሆኑ በርካታ ሰዎች መታሰራቸውን እንደሚያውቁ በመጥቀስ “የፖለቲካ አመራሮች በበርካታ ችግሮች ውስጥ እያለፉ እንደሚገኙ” ተናግረዋል። አምንስቲ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት እና አመራሮችን የፍርድ ሂደቱ በቅርበት እየተከታተለ እና ማስረጃዎችን በሚገባ እየተመለከተ መሆኑን አክለዋል።

ምንጭ – ቢቢሲ

selegna

By selegna

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *